ኦፕራ እና ዘ ሮክ ለሀዋይ ነዋሪዎች በየወሩ 1200 ዶላር ለመስጠት ቃል ገቡ

ድዌይን “ዘ ሮክ” ጆንሰን እና ኦፕራህ ዊንፍሬይ

የፎቶው ባለመብት, INSTAGRAM

ድዌይን “ዘ ሮክ” ጆንሰን እና ኦፕራ ዊንፍሬይ በማዊ ሰደድ እሣት ለተጎዱ የሀዋይ ነዋሪዎች ወርሃዊ ክፍያ ለመስጠት ፈንድ አቋቋሙ።

የማዊ ሕዝቦች ፈንድ የተሰኘው ተቋም በሺዎች ለሚቆጠሩ የሰደድ እሣት ተጎጂዎች በየወሩ 1200 ዶላር ወርሃዊ ክፍያ ለመስጠት አልሟል።

ሁለቱ ጉምቱ የሆሊውድ ፈርጦች ፈንዱን ለማስጀመር 10 ሚሊዮን ዶላር የለገሱ ሲሆን ተጨማሪ እርዳታ እንዲደረግ እየጠየቁም ይገኛሉ።

እሣት አደጋው ሶስት ሳምንት ቢያልፈውም በይፋ 115 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች አሁንም አድራሻቸው አይታወቅም።

ገንዘቡ የሚሰጠው ማዊ በተሰኘችው ደሴት በላይሃና እና ኩላ ግዛቶች በሰደድ እሣቱ ቤት ንብረታቸው ለወደመ ነዋሪዎች ነው።

ወርሃዊው ክፍያ ቤት ላላቸውና ለሚያከራዩ ቢሆንም ሕንፃ ኖሯቸው ለሚያከራዩ ነገር ግን ሌላ ቦታ ለሚኖሩ በጀት አልተመደበም።

“ከአማካሪ ቦርድ እና ከአካባቢው ማሕበረሰብ እንዲሁም ከተከበሩ ሃገር መሪዎች ጋር በመሆን ይህ ፈንድ በአደጋው ለተጎዱ ቀጥተኛ ድጋፍ ለማድረግ ይሞክራል” ሲል ፈንዱ ያወጣው መግለጫው ይጠቁማል።

ኦፕራ “ሰዎች የራሳቸው ኤጀንሲ ኖሯቸው የራሳቸውን ውሳኔ አሳልፈው ገንዘቡን ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው እንዲጠቀሙበት ማድረግ ነው ዕቅዳችን” ስትል ዘ ሮክ ኢንስታግራም ላይ በለጠፈው ቪድዮ ስትናገር ተደምጣለች።

ዘ ሮክ ደግሞ “በከባድ ጊዜ እንኳ የማዊ ሰዎች አንድ ላይ መሆንን ያውቁበታል፤ አብረን ነው የምንነሳው፤ እሱ ነው ጠንካራ የሚያደርገን” ይላል።

የአሜሪካው የፌዴራል አደጋ ጊዜ አስተዳደር ለአስቸኳይ ፍላጎቶች ማሟያ የሚሆን 700 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ አድርጓል።

ነገር ግን ብዙዎች ይህ ገንዘብ ረዥም ጊዜ ለሚወስደው መልሶ ማቋቋም ይህ ነው የሚባል ፋይዳ የለውም ይላሉ።

ታዋቂዋ ‘ቶክ ሾው’ አቅራቢ ኦፕራ ዊንፍሬይ ትርፍ ጊዜዋን ማዊ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቷ በመሄድ ታሳልፋለች።

ዘ ሮክ በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ድዌይን ጆንሰን ደግሞ የልጀነት ጊዜውን በሀዋይ ደሴት ነው ያሳለፈው፤ አልፎም በእናቱ የሀዋይ ደሴት ጥንታዊ ነዋሪዎች የሆኑት ሳሞዋን ጎሳ ነው።