ኢትዮጵያን በአባልነት የተቀበለው ብሪክስ የአሜሪካን ልዕለ ኃያልነት ይገዳደር ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈጣን ዕድገት የሚገኙ የአምስት አገራት ጥምረት የሆነው ብሪክስ በቅርቡ ስድስት አገራትን በአባልነት ለመቀበል ወስኗል።
ብሪክስ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካዋ የንግድ ከተማ ጆሃንስበርግ በነበረው 15ኛው ጉባዔው ኢትዮጵያ እና ሰሜን አፍሪካዊቷ ግብፅ ከአፍሪካ ያቀረቡት የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት እንዳገኘ ተገልጿል።
ከሁለቱ አገራት በተጨማሪም አርጀንቲና፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ በመጪው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት በአባልነት ብሪክስን ይቀላቀላሉ።
ኢትዮጵያ ብሪክስን በአባልነት ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ እንደ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል የቆጠረችው ሲሆን፣ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስገኘቱ ረገድ የጎላ እመርታ ያስገኛል ብላለች።
“በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከማሳደግ በላይ የተለያዩ የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶቿ በቡድኑ የልማት ባንክ በኩል ፋይናንስ እንዲያገኙ በር ይከፍታል፡፡ በብሪክስ አባል አገራት መካከል የሚኖረው የንግድ፣ የባህል እና የፖለቲካ ቁርኝት የላቀ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያም የዚህ ስብስብ አባል መኾኗ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖዋን የበለጠ የሚያሳድግ እንደሚሆን ይጠበቃል” ብሏል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ባወጣው መግለጫ።
ብሪክስ አድማሱን ለማስፋት በማለም አዳዲስ ስድስት አገራትን በአባልነት ለመቀበል መወሰኑን የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ “ታሪካዊ” ሲሉ ጠርተውታል።
የብሪክስ አባል አገራት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ሲሆኑ፣ ፍትሃዊ ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ እንዲኖር በማለም የተመሠረተ እንደሆነም ይነገራል።
ጥምረቱም በምዕራቡ የበላይነት የሚመራውን ዓለም የሚገዳደር እንደሆነ ነው የሚቆጠረው።
በአሁኑ ወቅት ኅብረቱ አዳዲስ አገራትን በአባልነት ለማካተት የወሰነ ሲሆን፣ ይህንንም በዋነኝነት ስትገፋ የቆየችው ቻይና ናት።
ለዚህም የቻይና ምክንያት የምዕራባውያንን የበላይነት ለመመከት የሚል ነው።
ለንደን በሚገኘው ‘ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ’ (ሶዋስ) ዩኒቨርስቲ ውስጥ የቻይና ጥናት ዳይሬክተር ስቲቭ ሳንግ እንደሚያስረዱት የብሪክስ አባል አገራት ከላይ ሲታዩ ምንም እንኳን ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገር ባይኖርም ፕሬዝዳንት ዢ ለጥምረቱ አባል አገራት ማሳየት የፈለጉት ጉዳይ ተመሳሳይ መጪ ዘመንን እንደሚሹ ነው።
መምህሩ እንደሚሉት ዢ ጂንፒንግ ሁሉም አገራት የምዕራቡ ዓለም የበላይነት በተጫነበት ሁኔታ መኖር እንደማይፈልጉ አሳይተዋል።
“ቻይና እያቀረበች ያለው አማራጭ ፈላጭ ቆራጭ መሪዎች በአገራቸው ደኅንነት እንዲሰማቸው እና ያለ ስጋት የሚኖሩበት የዓለም ሥርዓትን ነው” ይላሉ መምህሩ።
“አሜሪካ እና አውሮፓ ኃያላን የሚያቀርቡትን የዲሞክራሲ ቅድመ ሁኔታዎች መቀበል ሳያስፈልጋቸው አማራጭ የእድገት እና ልማትን የሚቀይሱበት መንገድን ነው እየተናገሩ ያሉት” በማለትም ዳይሬክተሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አጋርነትን መገንባት
የብሪክስ ጉባዔ አስተናጋጅ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አዲሶቹ አባል አገራትን በተመለከተ መግለጫ ሲሰጡ በደስታ ተውጠው ነበር።
“ከብሪክስ ጋር አጋርነትን ለመፍጠር የሌሎች አገራትን ፍላጎት ዋጋ የምንሰጠው ጉዳይ ነው” ሲሉም ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ተናግረው ነበር።
የብሪክስ መሥራች አገራት፣ አባል ለመሆን የሚያስፈልገው መስፈርት ላይ መስማማት ከተደረሰ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ በርካታ አገራትን እንደሚቀበሉ ነው ራማፎሳ የተናገሩት።
ሆኖም በዘንድሮው የብሪክስ ጉባኤ ምን ያህል አገራትን በአዲስ አባልነት እንቀበል? እንዲሁም ጊዜውስ መቼ ይሁን? በሚለው ላይ መከፋፈል ነበር።
አምስት አዳዲስ አገራት የኅብረቱ አባል እንደሚሆኑ ወሬዎች መናፈሳቸውን ተከትሎ በጉባዔው ሁለተኛ ቀን ረቡዕ፣ ነሐሴ 17/2015 ዓ.ም ሊካሄድ የነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ተሰርዟል።
የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ በዚያኑ ዕለት ተይዞ በነበረው የመሪዎች የእራት ግብዣ ፕሮግራም ላይ አልተገኙም።
የብራዚሉ መሪ ለምን እንዳልተገኙ ምክንያታቸው በትክክል ባይታወቅም፣ ነገር ግን ከምዕራባውያን አጋሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማስቀጠልን የማስቀጠል ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት መሆኑ እና አዳዲስ አገራትን የመቀበሉን ጉዳይ ላይም ጠንቃቃ ነበሩ።
ረቡዕ ምሽት ላይ ጋዜጠኞች ሐሙስ ጠዋት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚኖር መልዕክት የተላከላቸው ሲሆን ሥነ ሥርዓቱ ሁለት ሰዓት ዘግይቶ ነበር የተጀመረው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እነዚህ ጉዳዮችም እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ውይይቶች መደረጋቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች እንደሆኑ የጠቆሙ ሲሆን፣ በአባልነት ስድስተኛ አገር መጨመሯም አስገራሚ ሆኗል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይም የብሪክስ አባል አገራት መሪዎች የአዳዲሶቹን አገራት መጨመር በተመለከተ የየራሳቸውን ምላሽ ሰጥተዋል።
በዩክሬኑ ጦርነት የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል በሚል በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የወጣባቸው እና ደቡብ አፍሪካ ቢገኙ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የሚችሉበት አጋጣሚም ይኖራል በሚል የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ጉባዔ ላይ በአካል አልተገኙም። የጆሃንስበርጉን ጉባዔ የታደሙትም በቪዲዮ ነው።
የፑቲን ንግግር በየምዕራቡ ዓለም ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ ‘ኒዮ ሊበራሊዝም’ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ላይ ባህላዊ ዕሴቶች ላይ አደጋን ጋርጧል ብለዋል። በተጨማሪም አንድ አገር ወይም ቡድን የማይጫንበት የብዝሃ ዓለም እንዳይፈጠርም ስጋትን ፈጥሯል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ስለማን እንደተናገሩ ስም ባይጠቅሱም ስለ አሜሪካ መሆኑ ግልጽ ነበር።
ምንም እንኳን ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ በጉባኤው ላይ ባትሳተፍም ስሟ በተደጋጋሚ ተጠቃሽ ነበር።
የዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጃክ ሰሊቫን የብሪክስን የማስፋፊያ ዕቅዶች ለማቃለል ሞክረዋል።
የብሪክስ አባል አገራት ወሳኝ እና መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ባላቸው የተለያየ አመለካከት የተነሳ “ጂኦ-ፖለቲካዊ ተገዳዳሪ ቡድን ይሆናሉ ወይም አሜሪካን ይፈታተናል” የሚል እምነት እንደሌላቸው ነው አማካሪው የተናገሩት።
ትክክልም ሊሆኑ ይችላሉ።
ብሪክስን እንዲቀላቀሉ የተመረጡት ስድስቱ አገራት አንዳቸውም ቢሆን እንደ ፀረ- አሜሪካ እንደማይታዩ የሚናገሩት በዋሽንግተን የሚገኘው የኪዊንሲ ተቋም የግሎባል ሳውዝ አጥኚ ሳራንግ ሺዶር ናቸው።
“እኔ እንደማስበው መልዕክቱ ኅብረቱ የተለያዩ አገራት ስብስብ መሆኑ ነው። አንዳቸውም ቢሆን የአሜሪካ የቅርብ አጋሮች አይደሉም። አንዳንዶቹ መደበኛ አጋሮች ናቸው። ሁለቱ ወይም ሦስቱ የአሜሪካ ተቃዋሚዎች ይሆናሉ። ነገር ግን ሰፋ ባለ መልኩ ስናየው ይህ ኅብረት ፀረ-አሜሪካ የሆኑ አገራት ስብስብ አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“አሜሪካ ሁሉንም ተቋማት አታሽከረክርም”
መሠረታዊው ነገር የብሪክስ መስፋፋት የሚመጣውን ለውጥ የሚወክል ነው።
“ከእንግዲህ በኋላ አሜሪካ ሁሉንም ሕጎች የምታወጣበት፣ ሁሉንም ተቋማት የምታሽከረክርበት ዓለም አይደለም። ለዚህ ምንም ዓይነት ጥያቄ አይነሳበትም። ግን የአሜሪካ ምትክ አይሆንም። ከምትክነት ይልቅ ተደጋጋፊነት ሊሆን እንደሚችል ነው የሚታየኝ” ይላሉ ሺዶር።
አንዱ የአንዱን አስተያየት ያከብራል ለሚሉት የብሪክስ አባል አገራት ማንም አሸናፊ ወይም ተሸናፊ አይሮበትም። መስጠት እና መቀበል ያለበት የዲፕሎማሲ ስብስብ ብቻ ነው።
በጉባዔው ላይ ያልተገኙት ፕሬዝዳንት ፑቲንም በቁጥጥር ስር አልዋሉም፣ ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባው እና ሩሲያ አሁንም ተወክላለች።
ቻይና ከብሪክስ መስፋፋት አንጻር ትልቅ ዕቅዷን አሳክታለች። የብራዚል የጋራ መገበያያ ገንዘብም በኅብረቱ አባላት ዘንድ በቁም ነገር ተይዟል። ሕንድ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የወዳጅነት ሚዛንን ለመጠበቅ ስትሞክር ታይቷል። ደቡብ አፍሪካም የተሳካ ጉባዔን አስተናግዳለች።












