ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Social media
ኢትዮጵያ ብሪክስ በመባል የሚታወቀውን የአምስት አገራት ጥምረት ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ።
15ኛውን ጉባኤ በደቡብ አፍሪካዋ የንግድ መዲና ጆሃንስበርግ እያካሄደ የሚገኘው የፈጣን አዳጊ አገራት ጉባኤ ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀብሏታል።
በዘንድሮው ጉባዔ ቡድኑ በዋነኝነት አድማሱን ለማስፋት እንዳለመ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ በተጨማሪም ሌሎች አገራትም አባል ይሆናሉ።
በሚቀጥለው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመትም ከአምስቱ መስራቾች በተጨማሪ ኢትዮጵያ፣ግብጽ፣ አርጀንቲና፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ የቡድኑ አባላት ይሆናሉ።
ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን ያቀፈው የጥምረቱ ነሐሴ 16/ 2015 ዓ.ም ጉባዔውን የጀመረ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ነሐሴ 18/ 2015 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
በዚህ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጆሃንስበርግ በሚካሄደው የ‘ብሪክስ አፍሪካ አውት ሪች’ እና ‘ብሪክስ ፕላስ’ ስብሰባ ተሳትፈዋል።
ከእነዚህም ስብሰባዎች በፊት ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት በማካሄድ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎት መግለጻቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በጋራ ማዕቀፍ ስምምነት መሠረት ቻይና ለኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2023/2024 ጊዜ ውስጥ ለደረሰው የዕዳ ክፍያ እፎይታ እንደምትሰጥ መጠቆማቸውንም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ረቡዕ ነሐሴ 17/ 2015 ዓ.ም ያወጣው መረጃ ያስረዳል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረቧን አስመልክቶም የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መሥራቷን እንደምትቀጥል እና ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧን ከጥቂት ወራት በፊት አሳውቀው ነበር።
“አሁን እየተለወጠ ባለው የዓለማችን ሁኔታ እና ከዓለም የአሰላለፍ አንጻር ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ የሚረዱ ዓለም አቀፍ ተቋሞች አባል እንድንሆን እንሠራለን። ከእነዚህ አንደኛው ብሪክስ ነው። ጥያቄ ቀርቧል” ብለዋል።
“ብሪክስ ከኢትዮጵያ ለቀረበለት ጥያቄ በጎ ምላሽ እንደሚሰጠን እንጠብቃለን” ብለው የነበሩት አምባሳደር መለስ፤ “ከሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞችን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ተቋማት ጋርም መሥራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ብሪክስ በአውሮፓውያኑ 2009 የፖለቲካ ስብሰባ በማድረግ የተጀመረ ነው። ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና በኋላ ላይ ቡድኑን የተቀላቀለችው ደቡብ አፍሪካን በአባልነት ያቀፈው ስብስብ ነው።
ብሪክስ የሚለው መጠሪያ የእነዚህን አገራት ስም የመጀመሪያ ፊደል በመጠቀም የተፈጠረ ሲሆን፣ የጎልድማን ሳክስ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጂም ኦ’ኔል ናቸው ቃሉን ያስተዋወቁት።
መጀመሪያ ላይ አፍሪካዊቷ ደቡብ አፍሪካ የስብስቡ አባል አገር አልነበረችም። በወቅቱ ስያሜው አንዳንዴ ‘ብሪክ’ አንዳንዴም ‘ብሪክስ’ እየተባለ ይጠራ ነበር። በስተመጨረሻ የምትገኘው ኤስ (S) ፊደል የአባል አገራቱን ብዛት ለማመልከት የገባች ነበረች።
በዚህም ሳቢያ የመጀመሪያው የአገራቱ ስብስብ ከአፍሪካ የሚሳተፍ አባል አገር አልነበረውም። በቀጣዩ ስብሰባ ላይ ግን ደቡብ አፍሪካ ተጨምራ ብሪክስ የሚባለውን ስም ሙሉ አደረገችው።
የብሪክስ አባል አገራት 40 በመቶውን የዓለም ሕዝብ ይይዛሉ። አምስቱ አገራት በጋራ ያላቸው ምጣኔ ሃብታዊ አቅም ደግሞ የዓለምን 26 በመቶ ይሸፍናል።
ይህ ምጣኔ ሃብታቸውም በየጊዜው እየጨመረ በዓለም የንግድ ልውውጥ ላይ ተጽዕኗቸው እያደገ ነው።












