የሱዳን መረጃ ጠላፊዎች ‘ትዊተር’ን ያስተጓጎልነው ኤሎን መስክ ትኩረት እንዲሰጠን ነው አሉ

‘አኖኒመስ ሱዳን’ የተሰኘው የመረጃ መንታፊዎች ቡድን
የምስሉ መግለጫ, ‘አኖኒመስ ሱዳን’ የተሰኘው የመረጃ መንታፊዎች ቡድን መለያ

‘አኖኒመስ ሱዳን’ የተሰኘው የመረጃ መንታፊዎች ቡድን አሁን ኤክስ የተባለው (የቀድሞው ትርዊተር) ማኅበራዊ የትስስር መድረክን “ያስተጓጎልነው ሆን ብለን የባለቤቱን ኤሎን መስክን ሙሉ ትኩረት ለማግኘት ነበር” አሉ።

ባለፈው ማክሰኞ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ኤክስ (ትዊተር) የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ለተወሰነ ሰዓት መስተጋብሩ ታውኮ ነበር።

የጠላፊዎቹ ዋነኛ ፍላጎት ታዲያ ኤሎን መስክ በሱዳን ስታርሊንክ እንዲጀምር ነው።

ስታርሊንክ ኢንተርኔት በሚገደብባቸው ቦታዎች የሳተላይት ሽፋን በመስጠት ኢንተርኔትን በቀላሉ ማቅረብ የሚያስችል ነው።

ኤክስ ማኅበራዊ ሚዲያን ካስተጓጎሉ በኋላ የቡድኑ አባላት በቴሌግራም ላይ ባስተላለፉት መልዕክት “ኤሎን መስክ ይስማን፤ ስታርሊንክ በሱዳን ይክፈትልን” ሲሉ ተማጽነዋል።

ቢቢሲ ከእነዚህ ጠላፊዎች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ፍላጎታቸው ኢንተርኔት እንዲቀርብላቸው መሆኑን ተረድቷል።

ራሱን ‘ክራሽ’ ብሎ የሚጠራ የመረጃ መንታፊዎች ቡድን አባል ለቢቢሲ ሲናገር፣ ማክሰኞ ዕለት ኤክስን ከአገልግሎት ውጪ ያደረጉት ከሚጠበው በላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የመረጃ ጎርፍ በኤክስ ላይ በመልቀቅ እንደሆነ አስረድቷል።

ኤክስ እንዳመነው ከ20 ሺህ በላይ በዚህ ጥቃት መስተጓጎል የገጠማቸው በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ ያሉ ተጠቃሚዎቹን ነው።

ሌላው ‘ሆፋ’ የሚባለው የመረጃ መንታፊዎች ቡድን ጥቃቱ የተፈጸመው በሱዳን ስላለው ጦርነት ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ብሏል።

ኤሎን መስክ ለጠላፊዎቹ ጥያቄ በይፋ ያለው ነገር የለም።

ይህ ቡድን የሩሲያ መረጃ መንታፊ ቡድን እንደሆነ በስፋት ሲነገር ነበር።

ይህ እሳቤ የመጣው ቡድኑ በይፋ የፑቲን ደጋፊ መሆኑ ከታወቀ በኋላ ነው።

ነገር ግን ቡድኑ እንዳስታወቀው ከሩሲያ ጋር የሚያዛምደው ምንም ነገር የለም።

‘ክራሽ’ የተባለው የዚህ የመንታፊዎች ቡድን ቃል አቀባይና ዋና አባል ይህን ለቢቢሲ ለማረጋገጥ የቴሌግራም መተግበሪያው አድራሻ ሱዳን እንደሆነ አመላክቷል።

አኖኒመስ ሱዳን

ክራሽ እና ሆፋ ሁለቱም ሱዳናውያን ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ ፓስፖርታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

ቢቢሲ በሦስተኛ ወገን ማጣራት እንደቻለው በእርግጥም ጠላፊ ቡድኑ በሱዳን እንደሚገኝ ማረጋገጥ ችሏል።

“አንዱ ግባችን ሱዳናውያን በተቀረው ዓለም የሚታዩበትን ገጽታ መቀየር ነበር። በተለያዩ ዘርፎች ብቃት እንዳለን ማሳየት ግባችን ነበር” ብሏል ክራሽ የተሰኘው ቡድን አባል።

ይህ ቡድን በሰኔ ወር ለሩሲያ ያለውን ድጋፍ ከገለጸ በኋላ ቫግነር በሱዳን ያለውን ቀውስ እንዲያስቆም ተማጽኖ ነበር።

ይህ የመረጃ መንታፊዎች ቡድን ካለፈው ጥር ጀምሮ ኢንተርኔት በበቂ ሁኔታ በሌለበት ሱዳን ውስጥ በመሆን ፈረንሳይ፣ ናይጄሪያ እስራኤል እና አሜሪካ የሚገኙ የመንግሥት ድረ ገጾችን ሰብሮ መግባት ችሎ እንደነበር ይታወሳል።

ቡድኑ በኬንያም ጥቃት ያደረሰ ሲሆን፣ አገሪቱ በሱዳን ጉዳይ እየዶለተች ስለሆነ ነው ይህን ጥቃት በኬንያ ላይ የሰነዘርነው ብለዋል።

ቡድኑ በኬንያ ‘ኢሲቲዝን’ የተሰኘውን ቁልፍ ድረ ገጽ በማጥቃት ከፍ ያለ ችግር ፈጥሮ ነበር። ኢሲቲዝን ኬንያውያን 5 ሺህ የሚሆኑ አገልግሎቶችን በቀላሉ የሚያገኙበት የድረ ገጽ ግልጋሎት መስጫ ነው።

ይህ ቡድን ከዚህ ቀደም ‘ኦንሊፋንስ’ እና ‘ሬዲት’ የተሰኙ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ሰንዝሮባቸው ነበር። ይህን ያደረግነው የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ስለሚያበረታቱ ነውም ብሏል።

ይኸው የሱዳን መረጃ ጣለፊዎች ቡድን በሰኔ ወር ማይከሮሶፍት የሚሰጣቸውን አውትሉክ እና ዋን ድራይቭን አስተጓጉሎ ነበር።