አሜሪካ፣ ሰሜን ኮሪያዊ የኮምፒውተር ሊቆች የጎን ውጋት ሆኑብኝ አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ማንነታቸውን ደብቀው በአሜሪካ የበይነ መረብ ገበያ ሥራ አመልክተው የሚቀጠሩ የሰሜን ኮሪያ የኮምፒወተር ቴክኖሎጂ ብልሆች ለደኅንነቴ ሥጋት ሆነዋል አለች።
እነዚህ ሰሜን ኮሪያዊ ወጣቶች ሥራ የሚያመለክቱት ካሉበት ሆነው ነው። ዋንኛው ግባቸውም ሥራ ከተቀጠሩ በኋላ የበይነ መረብ የመረጃ ብርበራና ምዝበራ በመፈጸም ጠቀም ያለ ገንዘብ ለአገራቸው ሰሜን ኮሪያ ማስገኘት ነው።
በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ሦስት የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት እንዳሉት እነዚህ ሰሜን ኮሪያዊያን ሥራ የሚያመለክቱት የሌላ አገር ዜጋ እንደሆኑ አስመስለው በመቅረብ ነው።
ይህን ውስብስብ ስርቆት ደረስንበት ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ የአሜሪካ ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት በጋራ በሠሩት ጥናት ነው።
ሰሜን ኮሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተከታታይ የሚሳኤል ሙከራዎችን ማድረጓ አይዘነጋም።
በማያፈናፍን ማዕቀብ ሥር ሆና ይህን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ የጦር መሣሪያ ማምረትና መሞከር የሚያስችላትን ሃብት የምታገኘው ይህን በመሰሉ ስውር መንገዶች ነው ይላል ጥናቱ።
እንደ አውሮፓዊያኑ መጋቢት ወር 2017 ሰሜን ኮሪያ ለመጀመርያ ጊዜ አህጉር ተሻጋሪ የባሊስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓ ይታወሳል።
ጥናቱን ያደረጉት እነዚህ ተቋማት እንደሚሉት ሰሜን ኮሪያ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ባለሙያዎችን ወደ ገበያው በገፍ በማሰማራት ከእነርሱ የሚሰበሰብን ገንዘብና የሚመነተፈውን መረጃ እንደ አንድ ወሳኝ የገቢ ማግኛ መስክ አድርጋ ወስዳዋለች።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት፣ የአሜሪካ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች በጋራ ባደረጉት በዚህ ጥምር ጥናት ይህ በሰሜን ኮሪያ ተወላጆች በበይነ መረብ የሚደረገው ዘረፋ የተባበሩት መንግሥታትን ማዕቀብ የሚጥስ ነው።
እንደ ምርመራ ጥናቱ ከሆነ የኮምፒውተር ሊቆቹ በብዛት የሚመሽጉት በሰሜን ኮሪያ፣ በቻይናና በሩሲያ ውስጥ ነው።
ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑት ደግሞ በአፍሪካ እና በምሥራቅ እስያ ያደፍጣሉ።
እነዚህ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ አዋቂ ሰሜን ኮሪያዊያን በምዕራቡ ዓለም እጅግ ተፈላጊ የሆነውን የሥራ ዘርፍ አድኖ በመውሰድ ይታወቃሉ።
በተለይም በሶፍትዌር፣ በአዳዲስ ሞባይል መተግበሪያና በኮምፒውተር ቀመር ሽመና (coding) ዙርያ ጊዜያዊ ሥራዎች ላይ በመሠማራት ጠቀም ያለ ገንዘብ ለአገራቸው ያስገኛሉ።
ቀጣሪዎቻቸው ደግሞ የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ ግዙፍ ኩባንያዎች ናቸው።
ችግሩ የሚመነጨው ለሥራ ያገኙትን ዕድል በመጠቀም ከፍተኛ ገንዘብ የማሸሽ፣ ሰባሪና ቦርቧሪ የኮምፒውተር ቫይረሶችን የማዘጋጀትና የመርጨት በዚህም በምዕራብ አገራት መሠረተ ልማት ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ ላይ ናቸው ይላል፣ በአሜሪካ የተሠራው ጥናት።
ባለፈው ወር አንድ በሰሜን ኮሪያ የሚደገፍ የኮምፒውተር መረጃ መንታፊ ቡድን 615 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የክሪፕቶከረንሲ ገንዘብ 'አክሲ ኢንፊኒቲ' ከሚባል የበይነ መረብ ውርርድ አጫዋች ኩባንያ ካዝና ሙልጭ አድርጎ ዘርፏል።
በሚያዝያ ወር ደግሞ አንድ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ቪጂል ግሪፊት የተባለ ዜጋ የአገሪቱን ማዕቀብ ቸል በማለትና ወደ ፒዮንግያንግ በማቅናት የብሎክቼይን ቴክኖሎጂ ሥልጠና በመስጠቱ የአምስት ዓመት እስር ፈርዶበታል።
ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካና በተባበሩት መንግሥታት ተደራራቢና መልከ ብዙ ማዕቀቦች ሥር ሆና ተደጋጋሚ ግዙፍ የጦር መሣሪያ ሙከራዎችን ታደርጋለች።
















