ምዕራባውያንን እንቅልፍ የሚነሱት ሦስት የሩሲያ የሳይበር ጥቃቶች

የሩሲያ ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሩሲያ በአሜሪካ ላይ የሳይበር ጥቃቶችን ልትሰነዝር ማቀዷን የደኅንነት ምንጮች መጠቆማቸውን በመግለጽ፤ በአገሪቱ ያሉ ኩባንያዎች 'የዲጂታል በሮቻቸውን እንዲቆልፉ' አሳስበዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናትም በተመሳሳይ ሞስኮ ምዕራባውያንን ዒላማ ልታደርግ እንደምትችል በመግለጽ፤ የሳይበር ደኅንነት ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ሩሲያ የሳይበር ጥቃት ለመፈጸም ማቀዷን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አላቀረቡም።

ሩሲያም እነዚህ ክሶች 'ከሩሲያ ጥላቻ' ስሜት የሚመነጩ ናቸው ትላለች።

ይሁን እንጂ ሩሲያ በጦር መሣሪያ ክምችት ብቻ ሳትገደብ በሳይበር ጥቃትም ኃያል ናት ይላሉ የዘረፉ ባለሙያዎች።

ሞስኮ የሳይበር ጥቃቶችን ማድረስ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና ከፍተኛ ጉዳት ማስከተል የሚችሉ የመረጃ ሰርሳሪዎች ባለቤት ናት።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በጦር ሜዳ ከዩክሬን ጋር የተፋጠጠችው ሞስኮ፤ ከዩክሬን አጋሮች ጋር ደግሞ በሳይበር ጥቃት ጦርነት ልትገጥም ትችላለች።

ራፒድ7 ከተሰኘው የሳይበር ደኅንነት ተቋም የሆኑት ጄን ኤሊያ፤ ምዕራባውያን በሞስኮ ላይ መጠነ ሰፊ ማዕቀቦችን መጣላቸውን ትከትሎ የባይደን የሳይበር ጥቃት ማስጠንቀቂ እውነት ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ምዕራባውያንን የሚያሳስቡት የሩሲያ የሳይበር ጥቃቶች የሚከተሉት ናቸው።

ብላክኢነርጂቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ የሚግ ጥቃት

ዩክሬን የሩሲያ የሳይበር ጥቃት 'መለማመጃ ሜዳ' ተደርጋ ትወሰዳለች።

ሩሲያ የሳይበር ጥቃት ስልቶቿን እና መሣሪያዎቿን ለመፈተሽ ዩክሬን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝራለች።

እአአ 2015 ላይ 'ብላክኢነርጂ' በተሰኘው የሩሲያ የሳይበር ጥቃት የዩክሬን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥርዓት እንዳይሆን ሆኖ ነበር።

ለጥቂት ጊዜ በቆየው ጥቃት ከ80ሺህ በላይ የዩክሬን የአሌክትሪክ ደንበኞች በጨለማ ውስጥ ለመቆየት ተገደው ነበር።

የዩክሬን የኤሌክትሪክ ኃይል ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የዩክሬን የኤሌክትሪክ ኃይል ጣቢያ

እአአ 2016 ላይም በተመሳሳይ የሩሲያ ጥቃት የኪዬቭ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸው ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለእነዚህ የሳይበር ጥቃቶች የሩሲያ ጦር መረጃ መንታፊዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

"ሩሲያ ይህን መሰል ጥቃት በምዕራባውያን ላይ ልትሰነዝር ትችላለች" ሲሉ ዩክሬናዊው የሳይበር ደኅንነት ባለሙያ ማሪና ክሮቶፊል ይናገራሉ።

ሩሲያን ይህን የምታደረገው የምዕራባውያን የአጸፋ ምላሽ ቀላል እንደማይሆን በመገንዘብ ነው። ክሮቶፊል ምዕራባውያንም በሩሲያ መሠረተ ልማት ኔትዎርክ ውስጥ እጃቸውን ሳያስገቡ አይቀሩም ይላሉ።

ሩሲያ በዩክሬን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ የሰነዘረቻቸው ጥቃቶች ለረዥም ጊዜ መቆየት አልቻሉም ነበር። ያደረሱትም ጉዳት መጠነ ሲፈ አልነበረም።

ኖትፔትይ መቆጣጠር የማይቻል ውድመት

'ኖትፔትይ' በታሪክ ትልቅ ኪሳራ ያደረሰው የሳይበር ጥቃት ነው ይባላል።

አሜሪካ፣ ዩኬ እና የአውሮፓ ሕብረት ለዚህ የሳይበር ጥቃት ተጠያቂዎቹ የሩሲያ ጦር መረጃ መንታፊዎች ናቸው ይላሉ።

ይህ ጥቃት በዩክሬን ለሒሳብ ሥራ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ የኮምፒዩተር መተግበሪያዎችን ዒላማ ያደረገ ቢሆንም፤ ጉዳቱ በመላው ዓለም ተስፋፍቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ኩባንያዎችን አውኮ፤ 10 ቢሊዮን ዶላር ጉዳት አስከትሏል።

የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎችም ተመሳሳይ የሳይበር ጥቃት በመሰንዘር ጉዳት አድርሰው ነበር።

ዋናክራይ የኮምፒውተር ቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, Webroot

የምስሉ መግለጫ, ዋናክራይ የኮምፒውተር ቫይረስ

'ዋናክራይ' በተባለ ቫይረስ ምክንያት በ150 አገራት በሚገኙ 300ሺህ ኮምፒየተሮች ላይ የነበሩ መረጃዎች ተመሰቃቅለዋል።

በዚህም ብዙ ጉዳት ደርሷል። የዩኬ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጤና ቀጠሮዎችን ለመቀየር ተገዶ ነበር።

"እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች ከፍተኛ ቀውስ፣ ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ይፈጥራሉ፣ የሕይወት መጥፋትን ሁሉ ሊያስከትሉ ይችላሉ" ይላሉ ጄን ኤሊስ።

የነዳጅ መስመር የሳይበር ጥቃት

ከአንድ ዓመት በፊት መረጃ መንታፊዎች የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦዎች በመዝጋታቸው በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ነበር።

በዚህ ጥቃት ምክንያት የናፍጣ፣ የቤንዚን እና የአውሮፕላን ነዳጅ አቅርቦት ቀንሶ ትልቅ ቀውስ ፈጥሮ ነበር።

ይህ ጥቃት በሩሲያ መንግሥት ባይፈጸምም መቀመጫቸው ሩሲያ እንደሆነ በሚታመኑት ዳርክሳይድ ቡድን የተፈጸመ ጥቃት ነበር።

የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ የሚቆጣጠሩ ኮምፒውተሮችን መልሶ ለመቆጣጠር ለመረጃ መንታፊ ቡድኑ 4.4 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን ተከፍሏል።

በመረጃ መንታፊ ቡድን ጥቃት በአሜሪካ የነዳጅ እጥረት ተከስቶ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በመረጃ መንታፊ ቡድን ጥቃት በአሜሪካ የነዳጅ እጥረት ተከስቶ ነበር።

በነዳጅ ማስተላለፊ መስመር ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፤ በዓለማችን ቁጥር አንድ ሥጋ አቀነባባሪ ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል።

ጄቢኤስ በተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ ላይ ጥቃት የሰነዘረው ሬቪል መረጃ ሰርሳሪ ቡድን መገኛው ሩሲያ መሆኑ ይታመናል።

ታዲያ ሞስኮ እነዚህ አደገኛ የሳይበር ጥቃት አድራሾች ከፍተኛ ጉዳት እንዲያደርሱ ትዕዛዝ ልትሰጣቸው ትችላለች የሚል ስጋት አለ።

በሳይበር ጥቃት አድራሾች በኩል ጥቃት የመሰንዘሩ አንዱ ጥቅም ሩሲያ በጥቃቶቹ እጄ የለበትም የሚል መከራከሪያ ማቅረብ መቻሏ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ውድዋር።

የአሜሪካ ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?

አንድ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገር ላይ በሚደርስ ጥቃት ሕይወት ቢጠፋ ወይም ከፍተኛ ጉዳት ቢከሰት፤ የኔቶ አንቀጽ 5 ተግባራዊ ይሆናል።

በአንድ አገር ላይ የሚፈጸም ጥቃት በተቀረሩት አባላት ላይ የተቃጣ ጥቃት ተደርጎ ይቆጠራል።

ባለሙያዎች ይህ ኔቶ መግባት ወደማይፈልግበት ጦርነት ይከተዋል ይላሉ። ኔቶ ጦርነት ውስጥ ገባ ማለት ምላሹ የሚሆነው ከአሜሪካ እና ከቅርብ አጋሮቿ ነው።

ፕሬዝደንት ባይደን ቀድመው እንደተናገሩት፤ ሩሲያ በአሜሪካ ላይ ሰፊ ጥቃት ብትሰነዝር፤ "ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል"።