አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚያሸልመውን ሩሲያዊ 'ማፊያ' ፍለጋ

ጆ ታይዲ እባላለሁ። በቢቢሲ የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች ጉዳይ መርማሪ ጋዜጠኛ ነኝ።
ሩሲያ ሄድኩኝ።
ዓለም የሚፈልጋቸው እጅግ አደገኛ የበይነ መረብ ማፊያዎች ሩሲያ ተንቀባረው በነጻነት ይኖራሉ ሲባል ጊዜ ሄድኩኝ።
እነሱን ፍለጋ።
በተለይ ደግሞ ኢጎር ቱራሼቭን ፍለጋ። በተለይም ደግሞ ማክሲምን ፍለጋ።
ሁለቱ ወጣቶች የ'ኢቭል ኮርፖሬሽን' ባልደረቦች ናቸው። ኢቭል ኮርፖሬሽን ከሩሲያ የሚነሳ አደገኛ የበይነ መረብ ዘራፊዎች ቡድን ነው።
ባንክ አይቀረው፣ ኩባንያ ሙልጭ አድርጎ ይዘርፋል። በይነ መረብ ሰርስሮ ነው ታዲያ።
መጀመርያ ቱራሼቭን እንፈልግ።
ይሄ ወጣት ያለበትን የጠቆመ የአሜሪካ መንግሥት 5 ሚሊዮን ዶላር ነገ ዛሬ ሳይል ይሸልማል።
ይህ ወጣት በሩሲያ አለ ብለውኝ ነው ወደዚህ ወደ ሞስኮ የሄድኩት።
በኋላ ግን ተጸጸትኩ።
እንዲያውም ጊዜዬን እያባከንኩ መሆኔ ተሰማኝ።
ከሞስኮ በ700 ኪሎ ሜትር ርቀት የሆነ ካፌ ደጅ ቁጭ ብለናል።
ካሜራ ባለሙያውና አስተርጓሚዬ አብረውኝ አሉ።
የቆሻሻ ገንዳ ራቅ ብሎ ይታያል። አንዲት ድመት ከቆሻሻው መሀል አንድ የተጣለ የዶሮ ሥጋ ጎትታ ስታወጣ ይታየኛል።
"እናንተ ሰዎች ዝም ብላችሁ ነው ጊዜዬን የምታቃጥሉት" አልኳቸው።
ተቃወሙኝ። እመነን ቱራሼቭ እዚህ ነው ያለው ሲሉ ገሰጹኝ። እነሱ እንድታገስ ነው የሚጠይቁኝ። እኔ ደግሞ ነገሩ የማይመስል ሆኖብኛል።
"እንዴት ነው ከዚህ ቆሻሻ ሥፍራ ከሚገኝ አፓርትመንት ያን የሚያህል ሚሊዮነር የበይነ መረብ ሰርሳሪ ይኖራል የምትሉኝ? ኤዲያ የማይመስል ነገር…" አልኳቸው።
ተነስተን የበይነ መረብ ሰርሳሪው ማፊያ ቱራሼቭ ይኖርበታል ወደተባለው አፓርትመንት አመራን።
በሩን አንኳኳን።
ከጎረቤት በመስኮት በኩል አንዲት ሴትዮ በአንክሮ እንደሚከታተሉን አየን።
አንድ ወጣት ሰው በሩን ከፈተ።
"ይቅርታ ኢጎር ቱራቼቭ እዚህ ይኖር ይሆን?"
"ማን አላችሁኝ? ቱራቼቭ? ተሳስታችኋል።"
"የቤተሰቡ አድራሻ ይህ እንደሆነ ተነግሮን ነው። አንተን ማን እንበል?"
"ኦህ! ቱራቾቭ የሚባል ሰው አላውቅም። ለመሆኑ እናንተ ከየት ነው የመጣችሁት?"
የቢቢሲ ጋዜጠኞች እንደሆንን ተናገርን።
ቢቢሲ የሚል ቃል ሲሰማ የወጣቱ ፊት ተለዋወጠ።
"ቱራቼቭ የት እንደሚኖር ልነግራችሁ አልችልም። ለማንኛውም እዚህ መምጣት አልነበረባችሁም።"
በሩን ዘጋብን።
ወደ ካፌያችን ተመለስን።
ያን ምሽት እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር ነጋ። እያሰብኩ የነበረው ለምን የማይሆን ሐሳብ አምኜ ወደ ሩሲያ መጣሁ እያልኩ ነበር።
ወደ ሞስኮ መጓዝ ሳስብ መረጃ ሰብስቢያለሁ።
በእርግጥ የደረሱኝ መረጃዎች እርስ በእርስ የሚጣረሱ ነበሩ።
ግማሾቹ ሰዎች "እነዚህ የበይነ መረብ ማፊያዎች በታጣቂዎች የሚጠበቁ ናቸው፣ እንኳንስ እነሱን አግኝቶ ማናገር ይቅርና ቀና ብሎ ማየት ራሱ፣ ራስ ላይ ከባድ አደጋን መጋበዝ ነው። ሬሳህ በነገታው ትቦ ውስጥ ተጥሎ ታገኘዋለህ" አሉኝ።
ሌሎቹ ደግሞ፣ "በጭራሽ! በጭራሽ። በሩሲያ እንደ ወንጀለኛ የሚታዩ ሰዎች አይደሉም። በነጻነት ነው የሚኖሩት። በቃ ወንጀለኞች ሳይሆኑ የሆነ ኮምፒውተር መቦርቦር የሚወዱ ወጣቶች አድርገህ እያቸው" የሚል ነበር።
ሁለተኛውን አምኜ ነበር የመጣሁት።
ከወዲሁ እጅ መስጠትማ አይኖርብኝም።

የፎቶው ባለመብት, US Department of Justice
5 ሚሊዮን ዶላር የሚያሸልመው ማፍያ
ከሁለት ዓመት በፊት ኤፍቢአይ አንድን የሩሲያ የበይነ መረብ ወሮበሎች ቡድንን 'አደገኛ' ሲል በይኖት ነበር።
ይህ ቡድን ያው ቅድም የነገርኳችሁ 'ኢቭል ኮርፕ' የሚባለው ነው።
በዚህ ቡድን ውስጥ ዋናው ማፊያ ደግሞ ይሄ አሁን እኔ እየፈለኩት ያለው ኢጎር ቱራሼቭ ነው።
እንዲያውም የዚህ የበይነ መረብ ወሮበሎች ቡድን አለቃ እሱ ነው። የእሱ አለቃ ደግሞ አለ ማስኪም ያኩቤትስ የሚባል።
ማክሲም በ40 የተለያዩ አገሮች መቶ ሚሊዮን ብር የዘረፈ እውቅ ሰው ነው።
ዘረፋው የበይነ መረብ ዘረፋ ነው። ከትንንሽ ቢዝነሶች እስከ መልቲ ሚሊዮን ዶላር ድርጅቶች በእሱ ተመዝብረዋል።
የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እንደሚለው 'ኢቭል ኮርፕ' በበይነ መረብ የባንክ ዘረፋ የሚያደርጉ አደገኛ ወሮበሎች ናቸው።
የሚገርመው እነዚህ ሩሲያውያን ወጣቶች ናቸው። ማክሲም ያኮቤትስ ለምሳሌ ዕድሜው 32 ነው።
ጉርምስናውን እንኳ በወጉ ያላጠናቀቀ ልጅ ነው። ቅንጡ ላምቡርጊኒ ነው የሚነዳው። የአንበሳ ደቦል አለችው፤ ያላመዳት። ከእሷ ጋር ሲጫወት ይውላል።
ኤፍቢአይ እነዚህን ሁለት የበይነ መረብ ወሮበሎች ያሉበትን ለጠቆመኝ ለእያንዳንዳቸው 5 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ይላል።
እንደሚባለው ግን ወጣቶቹ ሩሲያው ውስጥ ዘና ብለው ነው የሚኖሩት?
እዚህ የመጣሁትም ይህን በዓይኔ በብረቱ ለማየት ነው።
መጀመሪያ ማክሲምን ፍለጋ ሄድን።
ማክሲምን ለማግኘት ጎልፍ ክለብ መሄድ እንዳለብኝ ተነገረኝ። ከሞስኮ 2 ሰዓት መንገድ ላይ ያለ ነው።
ማክሲም ጋብቻውን የፈጸመው በዚህ ጎልፍ ክለብ እንደሆነ ተነገረኝ። ቦታውን ጎበኘሁት። ከሦስት ዓመት በፊት ድል ያለ ሠርግ ደግሶ ነበር።
የእርሱን ሠርግ በርካታ ሚዲያዎች ሲዘግቡት ነበር።
ከባለቤቱ ጋር ሲደንስ በቪዲዮ ይታይ ነበር። በእሱ ሠርግ ያልዘፈነ አንድም ዝነኛ የሩሲያ ሞዛቂ አልነበረም።
የእሱን ሠሰርግ ያሰናዳችለትን ናታሊያን አገኘኋት። የጫጉላ ሽርሽር ያደረገበትን ቦታ ሁሉ ወስዳ አሳየችኝ። አንድ ኮረብታ ላይ ያለ ዋሻ ውስጥ ነው ጫጉላ ሽርሽሩ የነበረው።
በጎልፍ ክለቡ ውስጥ አዟዟረችኝ። እኔ ለዚህ ሠርግ ስንት አውጥቶ ይሁን የሚለውን ሒሳብ በአእምሮዬ እያሰላሁ ነበር።
በትንሹ ሩብ ሚሊዮን ዶላር ወጥቶበታል ነው የምትለኝ። እኔ ግን ነገሩን ሳሰላው ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በፍጹም ሊያንስ እንደማይችል እርግጠኛ ሆንኩ።
ለሠርግ ይህን ያህል ብር ካወጣ ኑሮው ምን ሊመስል እንደሚችል ማሰብ ነው።
ቱራሼቭን ፍለጋ ደግሞ ወደ ሞስኮ ሄድን። ቢሮው በሞስኮ ፌዴሬሽን ታወር ላይ እንደሆነ ተነገረን። ወደዚያው ሄድን።
በሞስኮ የእሱን የመሰለ ውድ ቢሮ የለም። ልክ አሜሪካ ማንሃተን ቢሮ የመከራየት ያህል ነው።
ቢሮው የሚገኝበት ሕንጻ ሄደን ለእንግዳ ተቀባይዋ እሱን ስንጠይቃት ተደናገጠች። ግራ ተጋባች።
አንድ ስልክ ሰጠችን። ስልኩን ደወልን። የፍራንክ ሲንታራ ሙዚቃ ለ5 ደቂቃ ተሰማና ስልኩ ተነሳ። የሆነ ሰው ድምጽ "ሃሎ! ማን ልበል?" አለ። መንገድ ላይ እንደሆነ ያስታውቃል።
ገና የቢቢሲ ጋዜጠኛ መሆኔን ስናገር ስልኩ ጆሮዬ ላይ ተደረገመ።

የፎቶው ባለመብት, National Crime Agency
የአሜሪካ ማፊያዎች፣ የሩሲያ ብርቅዬ ልጆች
ቱራሼቭም ሆነ ማክሲም አሜሪካ እጅግ ተፈላጊ ወንጀለኞች ትበላቸው እንጂ በሩሲያ ውስጥ ውስጡን ጀግኖች ሳይሆኑ አይቀሩም።
ሩሲያ እንዲያውም በትርፍ ሰዓታቸው የደኅንነት ሥራ ታሠራቸው ይሆናል።
በዚያ ላይ የአውሮፓና የአሜሪካንን የፋይናንስ ተቋማት ነው የሚዘርፉላት።
ስለዚህ ለሩሲያ ይሄ መጥፎ ነገር ላይሆን ይችላል።
'ኢቪል ኮርፕ'ን የሚመሩት እነ ቱራሼቭ በርካታ የቢሮ፣ የቤት፣ የስልክ፣ የኢሜይል አድራሻ አላቸው። ችግሩ አንዱም አይመልስም። አድራሻው ይኑር እንጂ ሰው አይኖርበትም።
ማክሲም ለምሳሌ የእናቱን የቡና እርሻ የስተዳድራል ሲባል ነበር። ይሁን እንጂ በአድራሻው የለም።
ለምሳሌ እሱ ያስተዳድረዋል የተባለ የቡና እርሻ ቢሮ ሄደን ያገኘናቸው አባት ማንነታችንን ስንነግራቸው በሳቅ ሞቱ።
"ቢቢሲ እንዴት እዚህ ይመጣል? ማክሲም እኮ ወደዚህ ዝር ካለ 15 ዓመታት አልፎታል።"
"እርስዎ የማክሲም ቤተሰብ ኖት?"
"እኔማ አባቱ ነኝ።"
ደነገጥን። አባቱ በካሜራ ፊት ለማውራት እንኳ የሚፈሩ ሰው አልሆኑም። ለ20 ደቂቃ ሙሉ በድፍረት አወሩን።
"አሜሪካ በልጄ ላይ ያሳለፈችው ውሳኔ ፍርደ ገምድልነት ነው" ሲሉ ክፉኛ ተቆጥተው ተናገሩ።
የእሳቸውን ልጅ ለጠቆመ 5 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ ማለቷ አንገብግቧቸዋል።
"ታውቃለህ! አሜሪካ በእኔ ቤተሰብ ላይ የሠራችው ሴራ፤ የሠራችው ግፍ። አሁን እንደ ድሮው መኖር አልቻልንም። የአሜሪካ ፍትሕ እንደ ድሮ የሶቪየት ጊዜ ፍትሕ ሆኗል" ሲሉ ተበሳጩ።
"ግን እኮ ልጅዎ ወንጀለኛ ነው" አልኳቸው፤ ፈርጠም ብዬ።
"ማስረጃ አለህ? ምንድነው ማስረጃህ? እስኪ ሰነዱን አሳየኝ" አሉኝ።
"ለምሳሌ ለሠርጉ 250 ሺህ ዶላር ነው ወጪ የሆነው።"
"እና ምን ይጠበስ? በእርግጥ ገንዘቡ ተጋኗል" ብለው ሳቁብኝ።
የማክሲም አባትን፣ በትክክል የልጃቸው ሥራ ምን እንደሆነ እንዲነግሩኝ ጠየቅኳቸው። ደመወዝ ከየት እንደሚያገኝ ጠየቅኳቸው።
እንዲሁ በደፈናው ከአማካይ ከፍ ያለ ጥሩ ደመወዝ እንደሚበላ ነገሩኝ።
"አባት! ምንድነው ግን የልጅዎ ሥራ? እሱን ሊነግሩኝ አይችሉም?" አልኳቸው።
"እናንተ ጋዜጠኞች ስትባሉ! እሱን ለምን እነግርሃለው? ደግሞስ የግል ምሥጢር ብሎ ነገር አታውቅም?" ብለው ሳቁ።
ለማንኛውም ከልጃቸው ጋር ከተገናኙ ረዥም ዘመን እንደሆነ ነግረውን አሰናበቱን።
እነዚህ በአሜሪካ እጅግ የሚፈለጉት እንደነ ማክሲም ያሉ የበይነ መረብ ወሮበሎች በምዕራባውያን ብዙ ዓይነት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል። ነገር ግን ያ ግድ አይሰጣቸውም። በሩሲያ ነጻ ሰዎች ናቸው።
እጅግ ቅንጡ ሕይወትን ይመራሉ። ፕሬዝዳንት ፑቲን እነዚህን የበይነ መረብ ወሮበሎች አሳልፈው እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ሲጠየቁ "ምንድነው የምታወሩት?" እያሉ ነገሩን ያጣጥሉታል።
የሩሲያ ሰላዮች ይሆኑ?
በነ ማክሲም የሚመራው 'ኢቭል ኮርፕ' የወሮበሎች ኩባንያ በርካታ ግዙፍ የዘረፋ ተግባራትን አሳክቷል።
ባለፈው ዓመት የአውሮፓ ሕብረት ማዕቀብ ጥሎበት ነበር። ምክንያቱም የዩክሬንን ጠቅላላ የኤሌክትሪክ መስመር ሰብረው ገብተው አገሪቱ በጨለማ እንድትዋጥ አድርገዋል።
ክሬምሊን እኔ የማውቅላችሁ ነገር የለም ብትልም በነዚህ ግለሰቦች ጀርባ ግን የሩሲያ መንግሥት ስውር እጅ እንዳለ የምዕራቡ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች እርግጠኞች ናቸው።
የሩሲያ የበይነ መረብ ቦርቧሪ ግለሰቦችና ኮርፖሬሽኖች አንድ ሕግ አላቸው።
በፍጹም በሩሲያና በወዳጅ አገራት ላይ ጥቃትና ዘረፋ አይፈጽሙም። በቀድሞ የሶቪየት አገራት ላይም ጥቃት መፈጸም ነውር ነው።
በምዕራባውያንና በአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ጥቃት መፈጸምና ገንዘብ መዝረፍ ግን ምንም አይደለም።
አሜሪካ የምትለው ግን ሌላ ነው። እነ ማክሲም ግለሰብ ይምሰሉ እንጂ በዋናነት የሚሠሩት ለሩሲያ የስለላ መሥሪያ ቤት ነው።
ቢቢሲ ለክሬምሊን ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ዙርያ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም አልተሳካለትም።
በበይነ መረብ ጥቃት ዙርያ ጥናት የሚሠሩ ድርጅቶች እንደሚሉት ደግሞ ከዚህ ወዲያ ከሩሲያ ምድር ከባባድ ጥቃቶች ሊኖሩ ይችላሉ።
እንደ 'ኢቭል ኮርፕ' ዓይነት፣ ወጣቶች የሚዘውሯቸው አደገኛ የበይነ መረብ ሰርሳሪ ድርጅቶች በሩሲያ መክፈት ፋሽን እየሆነ ነው።
ልክ ኮምፒውተር መጎርጎር የሚወዱ ልጆች ተሰባስበው ሥራ ሲጀምሩ የሚከፍቷቸው ሱቆች ሆነዋል።
ሃብታም አገራት ሩሲያንና እነዚህን ቦርቧሪ ልጆቿን ማቆም ካቃታቸው ድሃ አገራት ምን ሊውጣቸው? በምንስ አቅማቸው?
















