የፌስቡክ የትዊተርና የኢንስታግራም ማህበራዊ ገጾች ጥቃት ተፈጸመባቸው

ፌስቡክ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፌስቡክ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶች ትናንት አርብ ከሰዓት ላይ ለአጭር ጊዜ በሰርሳሪዎች ተሰብሮ እንደነበር ተነገረ።

"አወርማይን" የተባለው ቡድን የፌስቡክና የሜሴንጀር የኢንስታግራምና የትዊተር ገጾች ላይ "ፌስቡክ እራሱ ተሰብሮ ይገባበታል" በማለት ጽሁፍ አስፍሮ ነበር።

አሁን ግን በሰርሳሪዎች ተሰብረው የነበሩት የፌስቡክ ገጾች ወደነበሩበት መመለሳቸው ተገልጿል።

የበይነ መረብ መረጃ ሰርሳሪ ቡድኑ እንዳለው በፌስቡክ ላይ የሰነዘረው ጥቃት በኢንተርኔት ላይ ያለን ለጥቃት ተጋላጭነት ለማሳየት የተደረገ ሙከራ ነው። በፈረንጆቹ ጥር ወር ላይም ቡድኑ ተመሳሳይ ድርጊትን በአሜሪካ እግር ኳስ ቡድኖች ገጾች ላይ ፈጽሞ ነበር።

ቡድኑ በፌስቡክ የትዊተር ገጽ ላይ "ሰላም፤ አወርማይኖች ነን። ፌስቡክ በደህንነት አስተማማኝነት ከትዊተር የተሻለ ቢሆንም ከመሰበር አያመልጥም" የሚል መልዕክትን አስፍሯል።

በተጨማሪም ፌስቡክና ሜሴንጀር ኢንስታግራም ላይ ያላቸውን ገጾች በመጥለፍ ቡድኑ የእራሱን አርማ ለጥፎባቸው ነበር።

ትዊተር እንዳረጋገጠው ድርጊቱ በሦስተኛ ወገን አማካይነት የተከሰተ መሆኑን ጠቅሶ ችግሩ ማጋጠሙ እንደታወቀ አካውንቶቹ እንዲዘጉ መደረጉን ገልጿል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ፌስቡክ ላይ ያለን ግላዊ መረጃን እንዴት መጠበቅ ይቻላል?

አወርማይን ቀደም ባለው ጊዜ በትልልቅ ተቋማትንና በታዋቂ ግለሰቦች አካውንቶች ላይ ጥቃት በመፈጸም የሚታወቅ መቀመጫው ዱባይ ውስጥ እንደሆነ የሚነገርለት የበይነ መረብ ሰርሳሪ ቡድን ነው።

ከዚህ በፊት የትዊተር መስራች የሆነውን የጃክ ዶርሲን፣ የጉግል ሥራ አስፈጻሚ ሱንዳር ፒቻይን እንዲሁም ከተቋማት ደግሞ የሚዲያ ተቋማት የሆኑትን ኔትፍሊክስንና ኢኤስፒኤንን የማህበራዊ ሚዲያ አካውንትን ቡድኑ ለአጭር ጊዜ ሰብሮ ለመግባት ችሎ ነበር።

ቡድኑ እንደሚለው የሚፈጽማቸው ጥቃቶች በበይነ መረብ ላይ ያለውን ደካማ የደህንነት አጠባበቅን ለማጋለጥ ነው። ጨምሮም የጥቃቱ ሰለባዎች ደህንነታቸውን ለመጠበቅ የቡድኑን አገልግሎቶች እንዲጠቀሙ ያዛል።