ሩሲያ በህልውናዋ ላይ አደጋ ከተደቀነ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም እንደምትችል ገለጸች

የኒክሊየር ጦር መሳሪያ የታጠቀች የሩሲያ ስርጓች መርከብ።

የፎቶው ባለመብት, Russian Defence Ministry

የምስሉ መግለጫ, የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ የታጠቀች የሩሲያ ስርጓች መርከብ

ሞስኮ በህልውናዋ ላይ ከፍተኛ የሆነ የደኅንነት ስጋት ከተደቀነ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም እንደምትችል የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተናገሩ።

ቃል አቀባዩ ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ፕሬዝደንት ፑቲን የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ መጠቀምን ከግምት ሊያገቡ ይችላሉ ወይ? ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ነው ይህንን የተናገሩት።

"ሕዝብ እና የአገር ውስጥ ደኅንነትን የማረጋገጥ መርኅ አለን፤ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ በምን አይነት ሁኔታዎች ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላሉ የሚለውን መረዳት ይቻላል። በአገራችን ላይ ከፍተኛ የህልውና የደኅንነት ስጋት ካለ፤ የኒክሊየር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል" ብለዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ይህን አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታጎን ሞስኮ በዩክሬን ጦርነት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንደማትጠቀም ማረጋገጫ አለመስጠቷ ስህተት ነው ሲል አጥብቆ ኮንኗል።

የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፤ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት "አደገኛ ነው" ብለዋል።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ይህ ኃላፊነት ካለበት የኒክሊየር ጦር መሳሪያ ባለቤት የሚጠበቅ አይደለም ብለዋል።

ቃል አቀባዩ የአሜሪካ መንግሥት የሞስኮን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንደሚከታተልም ገልጸዋል።

የቀድሞ የአሜሪካ መከላከያ ኃላፊ ሊዮን ፓኔታ በተመሳሳይ የክሬምሊን ቃል አቀባይ አስተያየትን አጥብቀው ተችተዋል።

የቀድሞ የአሜሪካ ከፍተኛ የመከላከያ ባለሥልጣን እንዳሉት "ሩሲያ በዚህ ጦርነት አነስተኛ መጠን የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ለመጠቀም ምክንያት ስትፈልግ ማየት ከአደገኛነቱ ውጪ ሌላ አይታየኝም።"

ሊዮን ፓኔታ ሩሲያ እውነተኛ ያልሆነ ከፍተኛ ስጋት ተደቅኖብኛል ካለች የኒውክሊየር ጦር መሳሪያን ጥቅም ላይ ልታውል ትችላለች ሲሉ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።

"ይህ ሊፈጠር እንደሚችል አላውቅም። [ይህ የሚሆን ከሆነ] ፑቲን አሜሪካ ምን አይነት ምላሽ ልትሰጥ እንደምትችል እና እራሱን ማትረፍ ስለማቻሉ ማሰብ አለበት" ብለዋል።

በርካታ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ክምችት በመያዝ የዓለማችን ቁጥር አንድ አገር ሩሲያ ስትሆን፤ ከዩክሬን ጦርነት መቀስቀስ በኋላ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ማዘዛቸው ይታወሳል።

ፑቲን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ "ተገቢ ያልሆነ" እርምጃ እና "ሕገ-ወጥ ማዕቀብ" ጥለዋል በማለት ለከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት የሞስኮ የኑክሌር ኃይል 'በተለየ ሁኔታ በተጠንቀቅ' እንዲቆም ትዕዛዝ መስጠታቸው ሰጥተዋል።