ባይደን ሩሲያ በአሜሪካ ላይ የሳይበር ጥቃት ለመሰንዘር ያሏትን አማራጮች እያጤነች ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, SARAH SILBIGER
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አገራቸው ላይ በሩሲያ አማካይነት የሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃት ስጋቶች መጨመራቸውን የደህንነት ምርመራዎች እንደሚያሳዩ ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ አሜሪካ ላይ የሳይበር ጥቃት ለመፈጸም ያሏትን አማራጮች እያጤነች ነው ያሉ ሲሆን፤ አገራቸው ግን ይህንን ለመከላከል በእጇ ያሉ ሁሉንም መንገዶች እንደምትጠቀምና ምላሽ እንደምትሰጥ ገልጸዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የተጣሉባትን በርካታ ማዕቀቦች ተከትሎ የአጸፋ እርምጃዎችን ልትወስድ እንደምትች ባይደን ገልጸዋል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ያለው ሁለትዮሽ ግንኙነት ለመበጠስ ጫፍ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ትናንት ሰኞ በሰጡት መግለጫ በሳይበር ጥቃት ዙሪያ በርካታ ነገሮች እየተከናወኑ እንደሆነ እና ሩሲያ ያሏትን አማራጮች በሙሉ እየሞከረች እንደሆነ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የአሜሪካ ትልልቅ ኩባንያዎች የዲጂታል በሮቻቸውን በአግባቡ እንዲቆልፉና እራሳቸውን በሚገባ እንዲከላከሉ አሳስበዋል።
"አሜሪካ በእጅጉ የምትተማመንባቸው ወሳኝ አገልግሎቶችን የምታቀርቡ ድርጅቶች የሳይበር ደህንነታችሁን የመጠበቅና የማጠናከር ኃላፊነት አለባችሁ'' ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ እንደሚሉት ሩሲያ ይህንን እያደረገች ያለችው ከሁሉም አቅጣጫ የተጣለባትን ከባድ ማዕቀብ መቋቋም ባለመቻሏ እና ምጣኔ ሃብቷ እየደቀቀ በመሆኑን ነው።
በአውሮፓውያኑ 2017 የሩሲያ መረጃ በርባሪዎች በሰነዘሩት ጥቃት በመላው ዓለም የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ስራዎች የከሰሩ ሲሆን አጠቃላይ ኪሳራው እስከ 10 ቢሊየን ዶላር ይገመታል።
ምንም እንኳን ፕሬዝዳንት ባይደን በግልጽ ባይናገሩትም ምናልባት የሩሲያ የሳይበር ጥቃት ቁልፍ የአሜሪካ መሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ሊሆን ይችላል።
ባሳለፍነው ዓመት ወንጀለኛ የመረጃ ሰርሳሪዎች አንድ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ስራውን እንዲያቆም ማድረጋቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩም የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል ከሬምሊን ከዚህ በኋላ ምን አይነት አካሄድ እንደምትከተልና ምን አይነት እርምጃዎችን እንደምትወስድ መገመት ለምዕራቡ ዓለም አገራት ከባድ ፈተነ ሆኖባቸዋል።












