አኖኒመስ፡ መረጃ ጠላፊዎች ፑቲንን ለማዳከም እየሞከሩ ያሉት እንዴት ነው?

የስኳድ 303/አኖኒምስ የመረጃ ጠላፊ ቡድን አባል
የምስሉ መግለጫ, የስኳድ 303/አኖኒምስ የመረጃ ጠላፊ ቡድን አባል

አኖኒመስ የዩክሬንን ወረራ ለመበቀል በሚል በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ "የሳይበር ጦርነት" ካወጀ በኋላ ሩሲያን በመረጃ መረብ ጥቃት እያጣደፈ ነው።

በዚህ ቡድን ስር የሚንቀሳቀሱ በርካታ ግለሰቦች ዓላማቸውን፣ ስልታቸውን እና ዕቅዶቻቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዩክሬን ግጭት ከተጀመረ በኋላ ከተደረጉት የመረጃ መረብ ጥቃቶች መካከል ቡድኑ በሩሲያ የቴሌቭዥን ኔትወርኮች ላይ ያደረሰው ጠለፋ በጉልህ ይጠቀሳል።

ጠለፋውን በሚያሳየው አጭር ቪዲዮ ላይ በዩክሬን የሚፈነዱ ቦምቦችን እና ወታደሮች ስለግጭቱ አስከፊነት ሲናገሩ በሚያሳየው ምስል መደበኛ ፕሮግራሞችን ሲቋረጥ ይታያል።

ቪዲዮው ከሦስት ሳምንታት ገደማ በፊት መዘዋወር የጀመረ ሲሆን ሚሊዮን ተከታዮች ባሉት የአኖኒመስ ማኅበራዊ ድር አምባዎች ላይ ተለቋል።

"አሁናዊ መረጃ፣ የሩሲያ መንግሥት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በዩክሬን ስለሚሆነው ነገር እውነቱን ለማሰራጨት በአኖኒመስ ተጠልፈዋል" ይላል አንዱ ጽሁፍ።

በፍጥነትም በሚሊዮኖች ጊዜ ለዕይታ በቅቷል።

ትዕይንቱ በሙሉ የአኖኒመስን ጠለፋ ምልክቶች አሉት- ድራማዊ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ለማጋራትም ቀላል ነው። እንደሌሎች የቡድኑ የመረጃ መረብ ጥቃቶች ለማረጋገጥም በጣም ከባድ ነበር።

ከአኖኒመስ አነስተኛ ቡድኖች አንዱ ለጠለፋው ተጠያቂ መሆኑን እና ለ12 ደቂቃዎች የቴሌቪዥን አገልግሎቶቹን መቆጣጠራቸውን ተናግሯል።

መጀመሪያ ላይ ቪዲዮውን የለጠፈው ግለሰብም እውነት መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል።

ኤሊዛ ነዋሪነቷ አሜሪካ ነው። አባቷ ሩሲያዊ ሲሆን የቴሌቭዥን ዝግጅቶቹ ሲስተጓጎሉ ደውሎላታል። "አባቴ ደውሎ 'አምላኬ ሆይ እውነትን እያሳዩ ነው!' አለኝ። እኔም እንዲቀርጸው ነግሬ ቪዲዮውን ለጥፍኩት። አንድ ጓደኛውም ሁኔታውን ሲከሰት እንዳየው ተናግሯል" ብላለች።

ሮስቴሌኮም የተጠለፉትን አገልግሎቶች የሚያስተዳድር የሩሲያ ኩባንያ ሲሆን ለቀረቡለት ጥያቄዎች ግን ምላሽ አልሰጠም።

መረጃ ጠላፊዎቹ ንፁሀን ዩክሬናውያን እየተጨፈጨፉ ነው ሲሉ ለድርጊታቸው ማሳመኛ አቅርበዋል። "የዩክሬንን ሠላም ለመመለስ ምንም ካልተደረገ በክሬምሊን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እናጠናክራለን" ሲሉም ዝተዋል።

አኖኒመስ የሩሲያ ድረ-ገጾችን ከማስተጓገጎል ባለፈ መንግሥታዊ መረጃዎችን ወስጃለሁ ብሏል። የመረጃ መረብ ደኅንነት ኩባንያው 'ሬድ ጎት' ባልደረባዋ ሊዛ ፎርቴ ግን የእስካሁኖቹ አብዛኛዎቹ ጥቃቶች "በጣም መሠረታዊ" የሚባሉ ናቸው ይላሉ።

ጠላፊዎቹ በአብዛኛው መረጃ ሰጪውን በከፍተኛ ደረጃ በማጨናነቅ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ይህን ማድረግ በአንፃራዊነት ቀላል ሲሆን ድረ ገጾችን በጊዜያዊነት ከአገልግሎት ውጪ ያደርጋሉ።

"የቴሌቪዥኑ ጠለፋ ግን የሚያስደንቅ ፈጠራ ነው። ከባድ ይመስለኛል" ብለዋል።

አኖኒስ ማነው?

የመረጃ ጠላፊዎቹ ስብስብ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለው እአአ በ2003 ከ4ቻን ድረ ገጽ ነው።

ቡድኑ አመራር የሌለው ሲሆን መለያውም "እኛ ብዙኃን ነን" የሚል ነው።

ማንም ሰው የቡድኑ አባል ነኝ ብሎ ለፈለገው ዓላማ ጠለፋ ሊያከናውን ቢችልም ትኩረታቸው ሥልጣንን አላግባብ ተጠቅመዋል በተባሉ ድርጅቶች ላይ ነው።

ምልክታቸውም ጭንብል የለበሰ ግለሰብ ነው።

ቡድኑ በርካታ የማኅበራዊ ድር አምባዎች ሲኖሩት በትዊተር ገጹ ብቻ 15.5 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት።

አኖኒመሶች የሩሲያ ድረ-ገጾችንም አበላሽተዋል። ፎርቴ እንደሚለው ይህ ድረ ገጹን ተቆጣጥሮ ይዘቱን መቀየርን ያካትታል።

ጥቃቶቹ እስካሁን መቆራረጥ እና ስም መጥፋትን ቢያስከትሉም የመረጃ መረብ ኤክስፐርቶች ግን ከወረራው በኋላ የሚፈነዳው ለማኅበራዊ ለውጥ አሊያም ፖለቲካዊ አጀንዳ ለማራመድ የሚውለው የመረጃ ጠለፋና አክቲቪስትነት [ሃክቲቪዝም] አሳስቧቸዋል።

ቡድኑ በድንገት የሆስፒታል ኔትወርክ ሊያጠፋው ወይም ወሳኝ የመገናኛ ግንኙነቶችን ሊያቋርጥ ይችላል ብለው ይጨነቃሉ።

ከመረጃ መረብ ደኅንነት ፖሊሲ ጆርናል ኤሚሊ ቴይለር "እንዲህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም" ትላለች።

"ጥቃቶቹ አደጋዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ጥቃቶቹ ሊጠናከሩ ይችላሉ። ወይም አንድ ሰው በአጋጣሚ ለሲቪሎች ወሳኝ በሆነ ተቋም ላይ እውነተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል" ስትል ስጋቷን ትገልጻለች።

አኖኒመስም ለዓመታት እንዲህ ንቁ ሆኖ አያውቅም። ሮማን ዩክሬናዊው የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪ ሲሆን ስታንድ ፎር ዩክሬን (ለዩክሬን እንቁም እንደማለት ነው) የተባለ የመረጃ ጠላፊዎች ቡድን መሪ ነው። ሩሲያ አገሩን እስክትወር ድረስ ከአኖኒመስ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረውም።

አኖኒመስ ታስ የተባለውን የሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል ድረ ገጽን በፀረ-ፑቲን መልዕክት ለአጭር ጊዜ ሲያበላሽ እሱና ቡድኑ የደርጅቱን መለያ እንዳካተቱ ተናግሯል።

ኪዬቭ ከሚገኘው ቢሯቸው የዩክሬንን ጦርነት ለማገዝ ሮማን ቡድኑን እያስተባበረ ድረ-ገጾችን፣ አንድሮይድ መተግበሪያዎችን እና የቴሌግራም ቦቶችን ሲፈጥሩ ይውላሉ።

ሮማን በሥራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Roman

የምስሉ መግለጫ, ሮማን በሥራ ላይ: "አንዳንድ ጊዜ ሮኬቶችን በሰማይ ላይ አያለሁ"

"ለዩክሬን ጠብመንጃ ለማንሳት ዝግጁ ነኝ። ለጊዜው ግን በኮምፒውዩተር ክህሎቴ የተሻለ ጥቅም እሰጣለሁ። ስለዚህ ይህንን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጥቃትን መከላከል ለማስተባበር ከሁለት ላፕቶፖቼ ጋር ቤቴ ውስጥ ነኝ" ይላል ሮማን።

ቡድኑ የሩሲያ ክልላዊ የባቡር ትኬት አገልግሎትን ለተወሰኑ ሰዓታት እንደተቆጣጠረ ቢገልጽም ቢቢሲ ግን ይህንን ማረጋገጥ አልቻለም።

"በአንተ ወይም በዘመዶችህ ላይ ስጋት እስከሚፈጠሩ ድረስ እነዚህ ነገሮች ሕገ ወጥ እና የተሳሳቱ ናቸው" ሲልም ድርጊቱን ለማሳመን ይሟገታል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ታዋቂ በነበረው የፖላንድ ተዋጊ ቡድን ስም የተሰየመው 'ስኳድ 303' የተባለ የፖላንድ የመረጃ ጠለፋ ቡድንም ከአኖኒመስ ጋር ተዋህዷል ።

"ከአኖኒመስ ጋር ሁል ጊዜ አብረን እንሠራለን። አሁን ራሴን የአኖኒመስ እንቅስቃሴ አባል አድርጌ እቆጥራለሁ" የሚለው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አብራሪ የነበረውን ያን ዙምባክን ስም የወሰደ ቡድን ነው።

ፎቶግራፉ እንዲታተም ባይፈቅድም ሌላ የቡድኑ አባል የሆነ ዩክሬናዊ ኮፍያ እና ጭንብል ያደረገበትን ፎቶውን ልኳል። ያለበትን ሁኔታም "ቀን ጠመንጃ ይዞ ሌሊት ከአኖኒመስ ቡድን ጋር መጥለፍ" ሲል ይገልጻል።

ስኳድ 303 ኅብረተሰቡ ወደ ሩሲያ ስልክ ቁጥሮች ስለጦርነቱ እውነታ የጽሑፍ መልዕክት እንዲልኩ የሚያስችል ድረ-ገጽ ገንብቷል። ከ20 ሚሊዮን በላይ አጭር የጽሁፍ መልዕክት [ኤስኤምኤስ] እና የዋትስአፕ መልዕክቶችን እንዲላክ አመቻችተናል ይላሉ።

ሁለት የአኖኒመስ ቡድኖች እንደሚሉት ይህ ኅብረቱ እስካሁን ለዩክሬን ካደረገው አስተዋጽኦ ሁሉ የላቀው ነው።

ያን ዙምባክ ቡድኑን ሕገ ወጥ ተግባር አለማከናወኑን እንዴት እንዳረጋገጡት ሲጠየቅ ምንም ዓይነት የግል መረጃ እንዳልሰረቁ ወይም እንዳላጋሩ በመግለጽ በመረጃ ጦርነት ለማሸነፍ ሩሲያውያንን ለማነጋገር እየሞከርን ነው ብሏል።

በሚቀጥሉት ቀናትም የበለጠ ተፅዕኖ ያላቸው ጠለፋዎችን እያቀዱ መሆናቸውንም ተናግሯል።

ሩሲያ ያሉ ቡድኖችም በዩክሬን ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ቢሆንም መጠኑ አነስ ያለ ይመስላል።

ከጥር ጀምሮ በዩክሬን ላይ ሦስት የተቀናጁ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል። አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የዩክሬን የኮምፒውተር ሥርዓቶች ላይ ሦስት ከባድ የ"ዋይፐር" ጥቃቶች ተቃጥተዋል።

ረቡዕ ዕለት ከተደረገ ጠለፋ በኋላ የፕሬዝዳንት ዜለንስኪ በሐሰት የተቀነባበረ ቪዲዮ በዩክሬን 24 የቴሌቪዥን ጣቢያ ድረ-ገጽ ላይ ታይቷል።