የ16 ዓመቱ ታዳጊ ሚሊየነር የመረጃ መረብ ሰርሳሪ ሊሆን ይችላል ተብሎ ተጠረጠረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ኪንግደም ኦክስፎርድ ውስጥ ከቤተሰቦቹ ጋር የሚኖረው የ16 ዓመቱ ታዳጊ 'ላፕሰስ$' ከተሰኘው የመረጃ መረብ መረጃ መንታፊ ቡድን መሪዎች መካከል አንዱ ሳይሆን እንደማይቀር ተጠርጥሯል።
በመረጃ መረብ የመረጃ ምንተፋ 14 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ሃብት አካብቷል የሚባለው ይህ ታዳጊ በተቀናቃኞቹ እና አጥኚዎች ስሙ ተጥቅሷል።
የለንደን ከተማ ፖሊስ የመረጃ መረብ ወንጀለኞች ናቸው በሚል ጥርጣሬ ሰባት ታዳጊዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለጸ ሲሆን የ16 ዓመቱ ታዳጊ ከተያዙት መካከል ይሁን አይሁን ያለው ነገር የለም።
ኦክስፎርድ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪ የሆነው ይህ ታዳጊ ስሙ በዚህ ዘገባ ውስጥ እንዳይጠቀስ ሕግ ስለሚከለክል ማንነቱ አልተጠቀሰም።
የልጁ አባት ቤተሰቦቹ የታዳጊው ሁኔታ ያሳስባቸው እንደነበረና ከኮምፒውተሮቹ ሊያርቁት ሲሞክሩ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ በልጃቸው ጉዳይ ላይ አስተያየት የጠየቃቸው የታዳጊው እናት ምንም ነገር ማለት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
የኦቲዝም እንዳለበት የተነገረው ይህ ታዳጊ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ እንደሚገኝ ከሚታመነው 'የላፕሰስ$' የመረጃ መረብ ሰርሳሪ ቡድን ውስጥ እንዳለ ይነገራል።
'የላፕሰስ$' በአንጻራዊነት ሲታይ አዲስ የሚባል ነው ነገር ግን እንደ ማይክሮሶፍት ያሉ ታላላቅ ድርጅቶችን የመረጃ መረብ ጥበቃ ሰርስሮ መግባት ከቻለ ብዙ ከሚነገርላቸው እና እጅግ ከሚፈሩ የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች አንዱ ሆኗል።
"ስለዚህ ጉዳይ እስከ ቅርብ ጊዜ ምንም ሰምቼው አላውቅም ነበር። እሱም ቢሆን ስለበይነ መረብ የመረጃ ስርሰራ ተናግሮ አያውቅም። በኮምፒዩተር አጠቃቀም ላይ ጎበዝ እንደሆነ እና እዚያ ላይ ብዙ ጊዜ ያጠፋል። ሁልጊዜ ጌም የሚጨወት ነበር የሚመስለኝ" ሲል የታዳጊው አባት ለቢቢሲ ተናግሯል።
'የላፕሰስ$' የመረጃ መረብ መዝባሪዎች ቡድን ዒላማዎች ታላላቅ ተቋማት ሲሆኑ፣ የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ በሆነው የቴሌግራም ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታዋቂ በመሆን 47,000 ያህል ተከታዮች አሉት።
በቡድኑ የቴሌግራም ቻናል ለመጨረሻ ጊዜ መልዕከት የተላለፈው ባለፈው ረቡዕ ሲሆን የተወሰኑ የብድኑ አባላት ለጥቂት ጊዜያት እረፍት እንደሚወጡ እና በቻናሉ ላይ ምንም አይነት መልዕክት እንደማይተላለፍ የሚገልጽ ነበር።
በዚህ የመረጃ መረብ ሰርሳሪ ቡድን በርካታ ታላላቅ ኩባንያዎች እና ደንበኞቻቸው ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል።















