በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ በአንድ ሕንጻ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ73 በላይ ሰዎች ሞቱ

በደቡብ አፍሪካዋ መዲና ጆሃንስበርግ በሚገኝ አንድ ሕንጻ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ቢያንስ 73 ሰዎች መሞታቸውን የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
በአደጋው ከ50 በላይ ነዋሪዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
የከተማዋ ማዕከል ላይ በሚገኘው ባለ 5 ፎቅ ሕንጻ ላይ የተከሰተው እሳት መንስኤ እስካሁን ግልጽ እንዳልሆነ የጆሃንስበርግ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ቃል አቀባይ ሮበርት ሙላውድዚ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የእሳት አደጋ ሠራተኞች የተወሰኑ ነዋሪዎችን ከሕንጻው በማስወጣት ሕይወታቸውን ታድገዋል።
እሳቱ ሕንጻውን ማውደሙ ቢገለጽም በሕይወት ሊኖሩ የሚችሉ ተጎጂዎችን የማፈላለጉ ሥራ መቀጠሉን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ከአደጋ የተረፉ ነዋሪዎችን የሚያስፈልጓቸውን እርዳታዎችም ለመለገስም የአደጋ አስተዳደር ባለሥልጣናት በአካባቢው ተሰማርተዋል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ፍለጋቸውን ካጠናቀቁ በኋላ መንስኤውን እና ሌሎች ጉዳዮችን ለማጣራት የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ይሰማራል ተብሏል።
“በየፎቁ እና በእያንዳንዱ መኖሪያ ቤት እና ክፍል እየገባን በሕይወት ሊኖሩ የሚችሉ ሰዎችን እየፈለግን ነው” ሲሉ ሮበርት ለደቡብ አፍሪካው ሚዲያ ኢኤንሲኤ ተናግረዋል።
ሮበርት ቀድሞ ትዊተር በመባል ይታወቅ በነበረው ኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ባጋሩት ቪዲዮ የእሳት አደጋ ማጥፊያ መኪኖች፣ አምቡላንሶች መስኮቶቹ ተለብልቦ ከሚታየው ሕንጻ ውጪ ቆመውም አሳይቷል።
በተጨማሪም የተቃጠለው ሕንጻ አካባቢ የተሸፈኑ አስከሬኖችም የሚታዩበት ፎቶዎች ወጥተዋል።
አንዲት እናት በሕንጻው ላይ ነዋሪ የሆነችውን የ24 ዓመት ልጃቸውን እየፈለጉ እንደሆነ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ሕንጻው መቃጠሉን ስሰማ ልጄን ለመፈለግ እየሮጥኩ ነው የመጣሁት” ብለዋል።
“እዚህ ከደረስኩ በኋላ ግን ምን እየተፈጠረ እንደሆነ አላወቅኩም። ልጄ በሕይወት ትኑር፣ አትኑር የማውቀው ነገር የለም። ማንም ምንም እያለኝ ይደለም። በጣም ነው የተጨነቅኩት” ሲሉ አስረድተዋል።
ሕንጻው በጆሃንስበርግ ውስጥ የንግድ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ በርካቶችም ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ የሚሰፍሩበት ነው ተብሏል።
‘የተጠለፉ ሕንጻዎች’ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሆነው ይህ ሕንጻ፣ በደቡብ አፍሪካ በሕገወጥ መንገድ የሚያዝ እና በተለይም በአብዛኛው ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው አፍሪካውያን የሚኖሩበትም እንደሆነ ተገልጿል።












