በጅግጅጋ በደቦ ተደፍራ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችው የ11 ዓመት ታዳጊ አባት “ፍትሕን እሻለሁ” አሉ

 የ11 ዓመቷ ታዳጊ ፋጡማ ኡጋስ

የፎቶው ባለመብት, BBC Somali

የምስሉ መግለጫ, የ11 ዓመቷ ታዳጊ ፋጡማ ኡጋስ

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በደቦ ተደፍራ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ የተገኘችው የ11 ዓመት ታዳጊ አባት “ፍትሕን እንደሚሹ” ለቢቢሲ ተናገሩ።

በጅግጅጋ ከተማ ወረዳ 13 ተብሎ በሚጠራው ቦታ ነዋሪ የነበረችው የ11 ዓመቷ ታዳጊ ፋጡማ ኡጋስ፣ በደቦ ከተደፈረች በኋላ በገመድ ታንቃ የተገደለችው ባለፈው እሁድ ነሐሴ 21/ 2015 ዓ.ም. ነው።

በልጃቸው ግድያ ከባድ ሐዘን የገጠማቸው አባት ኡጋስ አረብ፣ ፍትሕን አጥብቀው እንደሚሹም ለቢቢሲ ሶማሊ ተናግረዋል።

“እኔ ተጎጂ ነኝ፤ ፍትሕ እፈልጋለሁ። እለኔ ልጅ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በዚህ መንገድ ሕይወታቸው ለጠፋ ሁሉ ፍትሕ እንዲሰፍን እጠይቃለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።

ታዳጊዋ በቤቷ ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ በከተማዋ በሚገኘው ካራማራ አጠቃላይ ሆስፒታል ለምርመራ በተወሰደችበት ወቅት በገመድ ታንቃ ከመገደሏ በፊት መደፈሯንም ተገልጿል።

የሶማሌ ክልል ፖሊስ በፋጡሞ ኡጋስ አረብ ግድያ እና መደፈር የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አረጋግጧል።

የሶማሌ ክልል ፖሊስ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ “በጅግጅጋ በቡድን የመድፈር እና የግድያ ወንጀል የፈጸሙ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና ምርመራ መከፈቱን” አመልክቷል።

ታዳጊዋ ተደፍራ የተገደለችው በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ ሲሆን፣ አባቷ ለቢቢሲ ሶማሊ ጥቃቱ ሲፈጸም ጩኸት ሰምተው ከእንቅልፋቸው መንቃታቸውን ተናግረዋል።

“በወቅቱ መኝታ ቤቴ ውስጥ ተኝቼ ነበር። ቤት ውስጥም ከእኔ ውጭ ትልልቅ ሰዎች አልነበሩም። ልጄ ጋር ሄጄ ሳያት እየተነፈሰች አልነበረም ደረቷንም በመጫን እንድትተነፍስ ለማድረግ ሞከርኩ። አንገቷንም ሳየው ገመድ ተጠምጥሞባት ታንቃለች። ገመዱን ቆርጬ ወደ ሐኪም ወሰድኳት” ሲሉም አባቷ ኡጋስ አረብ ለቢቢሲ ሶማሊ ተናግረዋል።

ለሕክምና ወደ ሆስፒታል አፋፍሰው ቢወስዷትም ታዳጊዋ ሕይወቷ ማለፉ በሕክምና ባለሙያዎች ተረጋግጧል።

የታዳጊዋ አባት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ልጃቸውን ደፍረው የገደሏት “ሠራተኞቻቸው” እንደሆኑ ነው።

በጅግጅጋ በሚገኘው ሞባይል ጥገና ሱቃቸው ተቀጥረው የሚሠሩ “አራቱ ሠራተኞቼ በድርጊቱ ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል። አንደኛው ሠራተኛዬ ጠፍቷል” ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ታዳጊዋን በቡድን ደፍረው ግድያ ፈጽመዋል በሚል አራት ተጠርጣሪዎች በሕግ ጥላ ሥር እንደሚገኙ አስታውቋል። ኮሚሽኑ ለልጅቷ ቤተሰብም ፍትሕን እንደሚያስገኝ ነው የገለጸው።

 ታዳጊዋ የተገደለችበት ወረዳ 13 ተብሎ የሚጠራው ሰፈር
የምስሉ መግለጫ, ታዳጊዋ የተገደለችበት ወረዳ 13 ተብሎ የሚጠራው ሰፈር

የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጀር ጄኔራል አብዲ አሊ ሲያድ ድርጊቱን የፈጸሙ ሰዎች በሕግ እንደሚጠየቁ ገልጸው፣ ቤተሰቡም ፍትሕ እንደሚያገኝ ነው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ግድያውንም ተከትሎ ባለንበት ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሰኞ ነሐሴ 22/ 2015 ዓ.ም. በጅግጅጋ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር።

ግድያውን የፈጸሙት ግለሰቦች “ከሌላ ብሔር የመጡ ናቸው” መባሉን ተከትሎ ብጥብጥ ተከስተው እንደነበር ተነግሯል።

የሟቿ ታዳጊ ቤተሰብ በሚኖርበት ሰፈር በግድያው በተቆጡ ነዋሪዎች እና በፖሊስ መካከል ግጭት መፈጠሩም ተገልጿል።

ፖሊስ ቁጣቸውን እና ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ነዋሪዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሟል ተብሏል።

በጅግጅጋ ከተማ ማዕከልም ከተነሳው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በርካታ መኪኖች ላይ ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ በታዳጊዋ መደፈር እና ግድያ ምክንያት በተፈጠረው ሁከት እና ግጭት ሃምሳ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ቢቢሲ ሶማሊ ያገኘው መረጃ ያስረዳል።

የፖሊስ ኮሚሽነሩ ሕብረተሰቡ ወደ አለመረጋጋት ሊመራ ወደሚችሉ ሁኔታዎችን እንዲያስወግድ ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ ሁኔታዎች ተረጋግተዋል የተባለ ሲሆን፣ በታዳጊዋ ግድያ ዙሪያ ፖሊስ የሚደረገው ምርመራ እንደቀጠለ እና ሲጠናቀቅም ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።