በደቡብ አፍሪካ በስምንት ሴቶች ላይ የተፈጸመው የመደፈር ጥቃት የቀሰቀሰው ሕዝባዊ ቁጣ

ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, SHIRAAZ MOHAMED

በደቡብ አፍሪካ የፈረንጆቹ ነሐሴ ወር የሴቶች ወር ነው። ሴቶች ትግላቸው፣ መስዋዕትነታቸው እና እየከፈሉት ያለው ዋጋ የሚታሰብበት ወር።

በአገሪቱ ያለው እውነታ ግን ለሴቶች የማይመች ነው። በርካቶች ለሕይወታቸው እየሰጉ ይኖራሉ። በቅርቡ በአገሪቱ የሙዚቃ ቪዲዮ ቀረጻ ላይ የነበሩ ስምንት ሴቶች በአስከፊ ሁኔታ በቡድን የተደፈሩበት ክስተት በደቡብ አፍሪካ የሴቶች ጥቃት ምን ያህል ዘግናኝ እንደሆነ አመላክቷል።

በሴቶቹ ላይ የደረሰው ይህንን ጥቃት ተከትሎ የአገሪቱ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ የሚጠይቁ ሰዎችም ተሰምተዋል።

ድርጊቱ የተፈጸመው ክሩጌርስድሮፕ በተሰኘ ከተማ በሚገኝ አገልግሎቱን በጨረሰ የማዕድን ስፍራ ነበር። በስፍራው ከ19 እስከ 35 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የነበሩ ስምንት ሴቶች መሳሪያ በታጠቁ ሰዎች በደቦ ተደፍረዋል።

ይህንንም ተከትሎም ፖሊስ 130 የሚሆኑ ሰዎችን በድርጊቱ እንደተሳተፉ በመጠርጠር አስሯል። አንዳቸውም ግን የመደፍር ወንጀል ክስ አለተመሰረተባቸውም። ምክንያቱ ደግሞ ፖሊስ የዘረመል ምርመራ ውጤት እስኪመጣ እየጠበቅኩ ነው ስላለ ነው።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚሸፍኑት በአሮጌው የማዕድን ስፍራ ያለፍቃድ ማዕድናትን የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በርካቶቹ ከጎረቤት አገራት ተሰደው ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡ ስደተኞች መሆናቸው ተነግሯል።

ይህንንም ተከትሎ በተፈጠረ ቁጣ በርካቶች የደቦ ጥቃት ሰለባ ሲሆኑ፣ በበቀል እርምጃም ቤታቸው ላይ ጥቃት እየደረሰ ይገኛል።

ከተደፈሩት ሴቶች መካከል ሦስቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሲሆን ጥቃቱ ከፍተኛ ሰቀቀን ውስጥ እንደጣላቸው ይናገራሉ።

“ወደ ሞት እየሄድን ነበር የመሰለን” ስትል ከጥቃቱ ሰለባዎች መካከል አንዷ ትናገራለች። “ከማዕድን ማውጫዎቹ ጉድጓድ ውስጥ ብቅ ብለው መሳሪያ እየተኮሱ ዝቅ እንድንል ነገሩን። የተወሰነው ልንሮጥ ሞከርን ነገር ግን በፍጥነት መጥተው ከበቡን” ስትል ታስረዳለች።

ቀጥሎ የመጣው እጅግ አሰቃቂ ነው። ረዘም ላለ ጊዜ ወሲባዊ ጥቃትቶች ተፈጽሞባቸዋል።

“መሬት ላይ ተንጋለልን እና እጅ ለእጅ ተያያዝን...የምንሄደው ወደ ሞት ከሆነም የእህቴን እጅ ይዤ ብሞት ይሽላል ብዬ አሰብኩ...ብዙ ጸሎት ስናደርግ ነበር” ብላለች።

ከጥቃቱ ሰላባዎች መካከል አንዷ በሰውነት መጥኗ ምክንያት ተነጥላ ወጥታለች።

“ቀጭን ነኝ። ሰውነት የለኝም። አልኳቸው። ከዚያ ጉድጓድ ውስጥ ከተው አሸዋ እየደፉ ሊቀብሩኝ ሞከሩ” ትላለች።

እንባዋን ለመግታት እየሞከረች ስለሁኔታው የምትናገረው ሌላኛዋ ሴት፣ ከደፋሪዎቹ ጋር ባለመተባበሯ እንዴት እንደተደበደበች ስትናገር ሰውነቷ ይንቀጠቀጥ ነበር።

“በእርግጫ መታኝ እና ልብሴን እንድለብስ ነገረኝ። ነገር ግን ሌሎች እየደፈሩኝ ነበር ሌላኛው መሳሪያውን ደግኖብኝ ነበር። በዚች ቅጸበት ነበር ተስፋ የቆርጥኩት። አንዳቸውንም የሚገዳደር አቅም አልነበረኝም። ላመልጣቸው አልቻልኩም። በዚህ አገር እየሞቱ እንዳሉት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሴቶች የምሞት ነበር የመሰለኝ” ስትል ሁኔታውን ታስታውሳለች።

ተጠቂዎቹ ፖሊስ ደፋሪዎቻቸውን ለሕግ ለማቅረብ የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

“ወደ እስር ቤት እንዲያስገቧቸው እንፈልጋለን። ለአንዳችም ሰከንድ ሳያቋርጥ ፖሊስ እንዲጠብቀን እንፈልጋለን። ደኅንነቱ የተጠበቀ አካባቢም እንፈልጋለን። ወደ ውጪ ለመውጣት ልንፈራ አይገባም” የሚል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

“ፖሊስ በሚያደርገው ምርመራ ልናግዛው እንፈልጋለን። ያኔ ደፋሪዎቻችን በቀላሉ ሊለዩ እና ለሕግ ሊቀርቡ ይችላሉ። ይህ የጥቃት ሰለባ ለሆኑት ሴቶች በሙሉ እንዲደረግ እንፈልጋለን” ሲሉም አክለዋል።

የደቦ ጥቃት

ተጠርጥረው የታሰሩ ህገወጥ ማዕድን አውጪዎችን ቤት ተቃዋሚዎች እያቀጠሉ ይገኛሉ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ስምንቱ ሴቶች ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ፖሊስ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቁ ኃይል የተሞላባቸው ተቃውሞዎች ከጆሃንስበርግ በስተምዕራብ በሚገኘው እና አገልግሎቱን ባጣናቀቀው የማዕድን ማውጫ ስፍራ አቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች ላይ ተካሄደዋል።

ከተቃዋሚዎቹ መካከል የተወሰኑት በወንጀሉ እንደተሳተፉ በተጠረጠሩት ሕገ ወጥ ማዕድን አውጪዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ፍትህ ለማስፈን እየሞከሩ ነው።

ተቃዋሚዎቹ ለጥቃቱ ‘ዛማ ዛማ’ እየተባለ የሚታወቀው የሕገ ወጥ ማዕድን አውጪዎች ቡድንን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ቡድኑ በከፍተኛ ወንጀሎች የሚከሰስ ሲሆን ለስምንቱ ሴቶች መደፈርም ዋነኛው ተጠያቂ ተደርጓል።

“ዛማ ዛማዎች በመካከላችን እንዲኖሩ እስከፈቀድን ድረስ አንዳችንም ደህና አንሆንም። ስለዚህ በራሳችን እጅ ሕግ ልናስከብር ተነስተናል” ሲል አንድ ተቃዋሚ ተናግሯል።

ፖሊስ መንገድ የዘጉ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ጉዳት የማያደርስ እና ድምጽ ብቻ የሚያሰማ ተኩስ እና የፕላስቲክ ጥይቶችን ተጥቅሟል።

በደቡብ አፍሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጭ ዜጎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። ስምንቱ ሴቶች ላይ የደረሰው ይህ ጥቃት የተፈጠረው ሕዝባዊ ቁጣ፣ በመጤ ጠል ቡድኖች ላልተገባ ዓላማ ሊውል ይችላል የሚል ስጋትንም ፈጥሯል።

ከዚህ ጥቃት በኋላ ፖሊስ ዜጎቹን በሚገባ አልጠበቀም የሚል ወቀሳ የቀረበበት ሲሆን፣ ለሴቶች የተሻለ ጥበቃ ለማድረግ ቃል ገብቷል።

በስፍራው የጦር ሠራዊት እንዲሰማራ እየጠየቀ ላለው ሕብረተሰብ ንግግር ያደረጉት የፖሊስ አገልግሎት ሚኒስትሩ ቤሃኪ ሴላ “መድፈር እጅግ እየተንሰራፋ እና እንደ መዝናኛ እየተቆጠረ መጥቷል” ብለዋል።

“ወንጀሉ እየተስፋፋ በመሆኑ በሴቶች ላይ የሚፈጸምን የመድፈር ጥቃት ብቻ የሚከታተል አካል ሊኖረን ይገባል” ሲሉም አክለዋል።

የሴቶች ወርን እየከበረች ያለችው ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ ከሚደፈሩባቸው እና ጥቃት ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል ብትጠቀስም፣ በሕግ የሚጠየቁ ሰዎች ቁጥር ግን ዝቅ ያለ ነው።