"ስለተደፈርኩበት ሁኔታ መፃፌ እፎይታን ፈጥሮልኛል" የፊልም ፀሐፊዋ ሚኬላ

ሚኬላ ኮኤል ተዋናይት፣ ፀሐፊ እንዲሁም የፊልም አዘጋጅ ናት። 'ቺዊንግ ገም' በሚለው ተከታታይ ፊልሟም ከፍተኛ አድናቆትን ተጎናፅፋለች።
ጊዜው ሁለተኛውን ሲዝን (ክፍል) 'ቺዊንግ ገም' እየፃፈች የነበረችበት ወቅት ነበር። በአንደኛው ቀን መሃል ላይ ከመፃፏ እረፍት ወሰደችና ከጓደኛዋ ጋር አንድ ሁለት ሊሉ ሄዱ።
ከዚያም ብዙ ነገሮች ጨለማ ሆኑ።
በነገታው ጥዋት ስትነሳ አንዳንድ ነገሮች እንደ ህልም ትዝ ይሏት ጀመር። መጠጧ ላይ የሚያደነዝዝ ነገር እንደተጨመረበትና እንደተደፈረችም ተረዳች።
ይህ ጨለማና ፈታኝ የሆነው አጋጣሚዋን 'አይ ሜይ ዲስትሮይ ዩ' (ላጠፋህ(ሽ) እችላለሁ) በሚልም ፃፈችው።
ከመፃፍ በተጨማሪ ወደ ፊልም ቀየረችው፤ ራሷም ተውናበታለች፣ ከሌላ ባለሙያም ጋር በመሆን ያዘጋጀችው እሷ ናት።
በቢቢሲም ላይ የቀረበው ክፍል ብቻዋን የምትተውንበት ነው።
"ለመፃፍ ሁለት ዓመት ተኩል ወስዶብኛል። በወቅቱም ተጨማሪ ሥራ እየሰራሁ አልነበረም" በማለት ለሬድዮ ኒውስ ቢት ተናግራለች።
"በጣም ፈታኝና አስቸጋሪ ወቅት ብቻ ሳይሆን ጥቃቱ በአሁኑ ወቅትም እየተፈፀመብኝ እንዳለ ተሰምቶኝ ነበር፤ ነገር ግን መፃፌ እፎይታን ሰጥቶኛል" ብላለች።
ሬፕ ክራይሲስ የተባለው ድርጅት ባወጣው መረጃ ከአስራ ስድስት ዓመት በላይ የሆኑ 20 በመቶ ሴቶችና 4 በመቶ ወንዶች እንደሚደፈሩ ነው።
ይህ መረጃ በእንግሊዝና በዌልስ ያለውን ነው የሚያሳየው።
ቢቢሲ ባደረገው የማጣራት ሥራ በጎርጎሳውያኑ 2015 እና 2019 2 ሺህ 600 የሚሆኑ ሰዎች መጠጣቸው ላይ የሚያደነዝዝ ነገር በመጨመር እንደተደፈሩ ነው። ከእነዚህም ውስጥ 72 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። መረጃው የተጠናቀረው ከእንግሊዝና ከዌልስ ነው።
"ራሳችንን ጥፋተኛ ማድረህ ማንንም አይጠቅምም"
በፊልሙ ላይ ያለችው የሚኬላ ገፀ ባህርይ አራቤላ በተለያዩ የስሜት ምስቅልቅሎች ውስጥ ትመላለሳለች። በተቻለም መጠን ከደረሰባት አደጋም ለማምለጥ ትቀልዳለች፣ ትስቃለች። ፊልሙ ላይ ያለችው ገፀ ባህርይ አራቤላ የሚኬላ የእውነተኛ ህይወቷም ነፀብራቅ ናት።
"እንዲህ አይነት አሰቃቂ ክስተተቶች ሲፈጠሩብን እንዲሁም የሚያስታውሱን ነገሮች ሲበዙ በተለያየ መንገድ ለማለፍ እንሞክራለን፤ እንታገላለን። አንዳንድ ጊዜም በማዘን ብቻ አይደለም" ብላለች።
"አንዳንድ ጊዜም የደረሰብንን ነገር ለመካድም እንሞክራለን። ሰዎች እንዲያምኑን እየለመንን አይደለም ነገር ግን ሰዎች ስለደረሰብን ነገር በመንገር እንድናምናቸው ይፈልጋሉ" ትላለች።
በፊልሙ ላይ ያለችው አራቤላ በጓደኞቿ እርዳታ የት እንደተደፈረችና በማን እንደሆነ ትደርስበታለች።

በፊልሙ ላይ የተሳሉት የጓደኞቿ ገፀ ባህርያትም በፍቅር ግንኙነት ወቅት የሚፈልጉትንና የማይፈልጉትን ነገር ለማለት ድምፃቸውን ከማሰማት ጋር ተያይዞ የራሳቸው የተወሳሰበ ታሪክ አላቸው።
"አጠቃላይ ፊልሙ በወሲብ ግንኙነት ወቅት ፈቃድ ጠቃሚ እንደሆነ ያስረዳል። ምን ያህል ፈቃዳችን እንዴት በሰዎች ጉልበት ሲነጠቅ፤ በራሳችን መወሰን አለመቻላችን የሚፈጥረውን ስሜት ነው የሚያሳየው" ትላለች ሚኬላ።
"በደረሰብን ነገር ወደ ራሳችን መጠቆምና ራሳችንን ጥፋተኛ ማድረግ ማንንም አይጠቅምም" የምትለው ሚኬላ "ለራሳችን ደግ ልንሆን ይገባል። በማንፈልግበት ወቅት ጮክ ብለን 'አይሆንም' ባለማለታችን ልንፀፀት አይገባም። ለራሳችን ይቅርታ ልናደርግ ይገባል።"
ከዚህ ፊልምም ብዙዎችም እንደሚማሩ ተስፋ አላት።

በተውኔቱ ላይ ያለችው አራቤላ በሰላሳዎቹ እድሜ የምትገኝ ሲሆን በትዊተር አማካኝነት ከፍተኛ እውቅናን አተረፈች። መፅሀፍም ለማሳተም ስምምነት ላይ ደረሰች። እንዲህ እውቅና ላይ ብትደርስም ግራ መጋባቷም የበዛ ነው።
"የሚሊኒየሙ የዓለም ገፅታ ነው። በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ሰዎች ህይወታቸውን እንዴት በጥሩ መልኩ እየኖሩ እንደሆነ ማሳየት ይፈልጋሉ።"
"ከስልኩ ወይም ከላፕቶፑ ጀርባ ያለነው ሰዎች ግን ህይወታቸውን የተስተካከለ መልክ ላይኖረው ይችላል። በርካታው የዚህ ዘመን ወጣት በተመሳሳይ መልኩ ነው እየኖረ ያለው፤ እናም ጤነኛ አካሄድም አይመስለኝም። ሁላችንም ቢሆን ህይወታችን ምስቅልቅል ውስጥ እንዳለ ይሰማናል። የተስተካከለ ህይወት አለን ብለን አናስብም" ትላለች።
'አይ ሜይ ዲስትሮይ ዩ' (ላጠፋህ (ሽ) እችላለሁ) የሚለው ፊልሟም ከፍተኛ አደናቆትም እየተቸረው ይገኛል።
አንዲት ሴት ጥቃት ከደረሰባት በኋላ የምታልፍበትን መንገድ በተለየ መልኩ በማቅረቧ ብቻ ሳይሆን መሪ ተዋናይቷ ከተለመደው አሰልቺ ባህርይም ወጣ ማድረግ በመቻሏ ነው።
"የትኛውንም የህይወት ዘዬ ስንመርጥ የራሱ ጥቅምና ጉዳት አለው። ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ የሆነበት የአኗኗር ዘዬ የለም። በተውኔቱ ውስጥ ያሉት ገፀ ባህርያት ደፋር፣ ጠንካራና ጎበዝ ተደርገው ነው የተሳሉት። በራሳቸው ነፃነትን መርጠው ለማንነታቸው ታማኝ ሆነው መኖርን የመረጡ ናቸው" በማለት ሚኬላ ትገልጻቸዋልች።
"ምንም ቢሆን ፍራቻ ህይወቴን እንዲቆጣጠረው አልፈልግም። በእኔ እድሜ የሚገኙ ሰዎችም ጋር የሚያመሳስለንም አንዱ በፍራቻ አለመሸበብን በመምረጣችን ነው" ብላለች።












