የሴቶች ጥቃት፡ በደቡብ አፍሪካ ከ5 ሴቶች ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠረው ራሱን አጠፋ

የፎቶው ባለመብት, Kyla Herrmannsen/BBC
በደቡብ አፍሪካ ክዋዙሉ ናታል ግዛት ከአምስት ሴቶች ግድያ ጋር በተያያዘ ከተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች መካከል አንደኛው በእስር ቤት ክፍል ውስጥ ራሱን መግደሉን ፖሊስ ለቢቢሲ ገለፀ።
ግለሰቦቹ በዚህ ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት ነበር።
ተጠርጣሪዎቹ ዛሬ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ቀጠሮ የነበራቸው ሲሆን ቀሪው ተጠርጣሪ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
የሟቾቹ ሴቶች አስክሬን ከሚያዚያ እስከ ነሐሴ ወር ባሉት ጊዜያት ምትዋሉሜ በተባለ አካባቢ በሸንኮራ አገዳ እርሻ ውስጥ የተገኘ ሲሆን የሁለቱ አስክሬን የተገኘው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።
በአካባቢው የፖሊስ ጥበቃ ደካማ በመሆኑ በተደጋጋሚ በሚፈፀሙ ግድያዎች ሳቢያ ነዋሪዎች በስጋት ውስጥ እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የአገሪቷ ፖሊስ ሚኒስትር ብሄኪ ሴሌ በሰጡት መግለጫ ላይ "እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች አለመፈፀማቸውን ለማረጋጋጥ እና ሴቶች ደህንነታቸው የተጠበቀና ደህንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ እንዲሁም አካባቢውን ተደራሽ ለማድረግ ተንቀሳቃሽ የማህበረሰብ አገልግሎት ማዕከል አቋቁመናል" ብለዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም ፍርድ ቤት አካባቢ በመሰባሰብና የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ ፍትህ ሲጠይቁ ታይተዋል።
ከችሎቱ በኋላ የአገሪቷ ፖሊስ ሚኒስትር በቁጥጥር ሥር እያለ ራሱን ያጠፋው ተጠርጣሪ በገጠራማዋ ክዋዙሉ ናታል በርካታ ሴቶችን መግደሉን አምኖ እንደነበር አስታውቀዋል።
ነዋሪዎቹ የ5ቱ ሴቶች ግድያ በተደጋጋሚ ግድያ ከፈፀሙ ቡድኖች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያመኑ ሲሆን በርካቶችም ዋነኛው ተጠርጣሪ ራሱን እንዳጠፋ ሲነገራቸው ተቆጥተዋል። አንዳንዶች መሞቱን ለማረጋገጥ አስክሬኑን ለማየት ሲጠይቁ ነበር።
ሚኒስትሩ አስክሬናቸው ያልተገኘ በርካታ የተገደሉ ሴቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ እና ሁለተኛው ተጠርጣሪ ከግድያው ጋር መያያዙን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ባለመገኘቱ ፖሊስ መዝገቡን ለመመለስ ተገዷል።












