በነፍሰጡሯ ላይ የተፈጸመው ግድያ በደቡብ አፍሪካ ቁጣን ቀሰቀሰ

ሟች ፑሌ

የፎቶው ባለመብት, @KEBA99

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የአንዲት የ28 ዓመት ወጣት ዘግናኝ ግድያን ተከትሎ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ቁጣ ተቀስቅሷል።

ከዋና ከተማዋ ጆሃንስበርግ አቅራቢያ በስለት ተወግታና ከአንድ ዛፍ ላይ ተሰቅላ የተገኘችው ጼጎፋሶ ፑሌ የተባለችው ወጣት ግድያ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ፖሊስን ጠቅሰው እንደዘገቡት ሟች የስምንት ወር ነፍሰጡር ነበረች ተብሏል።

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሴቶች ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት የሚፈጸም ሲሆን በዚህም ምክንያት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ባለፈው ዓመት አገራቸውን "ለሴቶች ደህንነት አደገኛ የሆነ ቦታ" ሆናለች በማለት ገልጸዋት ነበር።

ከዚህ ቀደም በወንጀል ድርጊቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ 2,930 አዋቂ ሴቶች ተገድለዋል፤ ይህም በየሦስት ሰዓቱ የአንዲት ሴት ህይወት በነፍሰገዳይ እጅ ይቀጠፋል ማለት ነው።

ሶዌታን የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ፑሌ ባለፈው ሳምንት የደተረሰችበት ሳይታወቅ ጠፍታ የነበረ ሲሆን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ አስከሬኗ ትናንት ሰኞ ነው የተገኘው።

የወጣቷ አስከሬን ከተገኘ በኋላ ፖሊስ በወንጀሉ ዙሪያ ያሉ ክስተቶችን ለማወቅ ምርመራ መጀመሩንም የፖሊስ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።

በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ደቡብ አፍሪካዊያን ፖሊስ የድርጊቱን ፈጻሚዎች በቶሎ እንዲይዝ አጥብቀው እየጠየቁ ሲሆን፤ ነገር ግን ሟች ፍትህን ታገኛለች በሚለው ላይ ጥርጣሬያቸውን እየገለጹ ነው።

ባለፈው ዓመት ተከስተው በነበሩ ተደጋጋሚ የሴቶች ግድያ ሳቢያ የሴቶችን ደህንንት ለማስጠበቅ ተጨማሪ እርምጃዎችን መንግሥት እንዲወስድ የሚጠይቁ ተከታታይ ሰልፎች በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተካሂደው ነበር።

ከዚያ በኋላም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚመለከት ፍርድ ቤት እንዲከፈት ቢደረግም በበጀት ችግር ምክንያት አልፎ አልፎ እንጂ በመደበኛነት ሥራውን ማከናወን ሳይችል ቆይቷል።

በመንግሥትና በተለያዩ ተቋማት አማካይነት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቆም ጥረት ተደርጓል። በዚህም ከጥቃት የተረፉ ሴቶችን ለመደገፍና የጥቃት ፈጻሚ ወንዶችን ትኩረት ያደረጉ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተገልጿል።