በኢራን "በክብር ግድያ" በአሰቃቂ ሁኔታ ታዳጊ ልጁን የገደለው አባት ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Twitter
በሰሜን ኢራን የሚገኝ አንድ ግለሰብ የአስራ አራት አመት ታዳጊ ልጁን "የክብር ግድያ" በሚባለው መንገድ በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
ግለሰቡንም ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎታል።
በኢራንም ሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ አገራት "ማኅበረሰቡን አዋርደዋል፤ የቤተሰባቸውን ክብር ዝቅ አድርገዋል" ተብለው የሚወነጀሉ ታዳጊ ሴቶች "የክብር ግድያ" (ኦነር ኪሊንግ) ተብሎ በሚጠራው ሁኔታ በቤተሰብ አባላቸው ይገደላሉ።
በጊላን ግዛት ነዋሪ የሆነችው ታዳጊዋ ሮሚና አሽራፊ የሰላሳ አምስት አመት የወንድ ጓደኛ የነበራት ሲሆን፤ አባቷም ግንኙነታቸውን ባለመፍቀዱ ከሰውየው ጋር ጠፍታ እንደነበር የሃገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።
ሮሚናና የወንድ ጓደኛዋ ከተደበቁበት በፖሊስ የተገኙ ሲሆን፤ ፖሊስም ወደ ቤቷ መልሷታል። በወቅቱም ለህይወቷ እንደሚያሰጋት ገልፃ ነበር ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት ሃሙስም አባቷ በመኝታ ክፍሏ ውስጥ እንደገደላትም ተገልጿል።
የጊላን ግዛት ሚዲያዎችም እንደዘገቡት አባትየው በአሰቃቂ ሁኔታ በማጭድ ቀልቶ የገደላት ሲሆን፤ ከሞተች በኋላም ማጭዱን ይዞ ወጥቶ እንደገደላት ተናዟል።
በዛሬውም ዕለት የተለያዩ የሃገሪቱ ሚዲያዎች የሮሚናን ታሪክ በፊት ገፃቸው ይዘው የወጡ ሲሆን፤ የሃገሪቱ የፍትህ ስርአት ምን ያህል ሴቶችንና ታዳጊዎችን መጠበቅ እንዳልቻለ ተችተው ፅፈዋል።
በኢራንም የትዊተር ተጠቃሚዎች ዘንድ ከአምሳ ሺ በላይ ሰዎችም የተገዳይዋን ስም ሮሚና አሽራፍን ሃሽ ታግ በመጠቀም ትዊት በማድረግ ዘክረዋታል።
በኢራን ያለውንም የማህበረሰቡን አባዊ ስርአት ከመተቸት ጀምሮ አገዳደልዋን ብዙዎች አውግዘዋል፤ ቁጣቸውንም ገልፀዋል።
የሴቶችና ቤተሰቦች ጉዳይ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአሁኗ ፀሐፊ የሆኑት ሻሂንዶክት ሞላቬርዲም በበኩላቸው "ሮሚና በክብር ግድያ ስትገደል የመጀመሪያዋም የመጨረሻዋም አትሆንም" በማለት አስፍረዋል።
አክለውም "በሃገሪቱ ውስጥ ያለው ባህል ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት እንዲሁም ህጎቹን መቀየር ካልተቻለ" ግድያዎች ሊቀጥሉ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
የኢራን እስላማዊ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት "በክብር ግድያ" ለተወነጀሉ ወይም ጥቃት ላደረሱ የቤተሰብ አባላት ቅጣቱ ቀለል ያለ ነው።
ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ልጁን በክብር ግደያ ከገደለ የሚፈረድበት ከሶስት እስከ አስር አመት እስር ሲሆን፤ ለሌላ ግድያ ወንጀል እንደሚደረገው የሞት ቅጣትም ሆነ የደም ክፍያ ገንዘብ ቅጣት ተፈፃሚ አይሆንም።
በኢራን ምን ያህል የክብር ግድያዎች እንደሚፈፀሙ መረጃዎች ባይኖሩም የተለያዩ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በገጠር አካካቢ እንዲሁም በአንዳንድ ማህበረሰቦች ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚፈፀም ሪፖርት አድርገዋል።
የ'ክብር ግድያ' ምንድን ነው?
የክብር ግድያ በቤተሰብ ላይ ውርደትን አስከትለዋል የሚባሉ ሴቶች ላይ በቤተሰብ አባል የሚፈፀም ግድያ ነው።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ሂዩማን ራይትስ ዋች ለግድያው ተብለው ከሚሰጡ ምክንያቶች መካከል ከሰበሰቧቸው መረጃዎች፦
- ቤተሰብ የመረጠላቸውን ባል አለማግባት
- ወሲባዊ ጥቃት ወይም መደፈር ሲፈፀምባቸው
- ከጋብቻ ውጭ ወሲባዊ ግንኙነት ቢኖራቸው ወይም ኖሯቸዋል ተብሎ የሚታመን ከሆነ
ከዚህም በተጨማሪ አለባበሳቸው 'ያልተገባ' ከሆነ፣ 'የማይሆን' ጠባይ ካሳዩ እንዲሁም 'ታዛዥ' ካልሆኑ ግድያው ይፈፀምባቸዋል ተብሏል።












