በህንድ የደቦ መድፈር የፈጸሙ ግለሰቦች ከእስር መፈታት ተቃውሞ አስነሳ

በህንድ የተነሳው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በህንድ አንዲት ሙስሊምን በቡድን የደፈሩ 11 ግለሰቦች ከአስራ አምስት አመት እስራት በኋላ እንዲፈቱ መወሰኑን ተከትሎ በመላው ህንድ ተቃውሞ ተነሳ።

ግለሰቦቹ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ነበር።

የመደፈር ጥቃት የተፈጸመባት ግለሰብ ቢልኪስ ባኖ የምትሰኝ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2002 በጉጅራት ግዛት በተፈጠረ የሃይማኖት አመጽ 14 የቤተሰብ አባላቷ ተገድለዋል።

መንግሥት እነዚህን ደፋሪዎች ለመፍታት የወሰደውን ውሳኔ እንዲቀለብስ በርካታ ወንዶች እና ሴቶች መፈክሮችን አሰምተዋል።

በህንድ የፊልም ተዋናይት እና የሴቶች መብት ተሟጋች ሻባና አዝሚ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገረችው “ቢልኪስ ባኖ የደረሰባት፣ በቤተሰቧ ላይ የደረሰው ግፍ በአገራችን ላይ ሲደርስ ቆመን ማየት አንችልም። ለዚህም ነው ሁላችንም በአንድ ላይ ድምጻችንን ከፍ አድርገን እየተቃወምን ያለነው” ብላለች

"ይህ የተሳሳተ አመለካከት እና የፆተኝነት መንፈስ በጥልቀት ሰርጾ መደበኛ በሆነ መልኩ መታየት ጀምሯል። በአሁኑ ወቅት መደፈር በሰዎች የተለመደ ተደርጎ መታየት ጀምሯል” በማለት አዲቲ የተባለች የተቃውሞ ሰልፈኛ ተማሪ ተናግራለች።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከ100 የሚበልጡ ጡረተኛ የመንግስት ሰራተኞች ለህንድ ዋና ዳኛ በፃፉት ደብዳቤ የደፋሪዎቹ መፈታት በሁሉም ሴቶች ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለዋል።

ህንድ 75ኛ የነጻነት በአሏን በምታከብርበት በዚህ ወር ወንጀለኞቹን ለመልቀቅ መወሰኑን የጉጃራት መንግስት አስታውቋል።

በዚያን ወቅት የወጣና በርካቶች የተጋሩት ቪዲዮ ግለሰቦቹ ከጎህራ እስር ቤት ውጭ ተሰልፈው ዘመዶቻቸው ጣፋጭ እየሰጧቸው እና ክብራቸውንም ለማሳየት እግራቸውን ሲነኩ ታይተዋል።

መደፈር የተፈጸመባት ግለሰብ ባኖ ደፋሪዎቹን ለመፍታት የተላለፈው ብያኔ “ፍትሃዊ ያልሆነ” በማለት በፍትህ ላይ ያላትን እምነት እንዳናጋው ገልጻለች።