‘ጠንቋይ’ በሚል ሲታደኑ የነበሩ ጋምቢያውያን ትውስታ

ጋምቢያዊት ሴት

የፎቶው ባለመብት, ANEKED

ለ22 ዓመታት ያህል ጋምቢያውያን ፈላጭ ቆራጭ በሆኑት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ያህያ ጃሜህ አስተዳደር ስር ነበሩ።

ፕሬዝዳንቱ በሥልጣን ዘመናቸው ግድያ፣ ጠንቋይ (አዋቂ) የተባሉትን በማደን እና የግዳጅ ሥራን ጨምሮ በሰፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ይወነጀላሉ።

እርሳቸው ግን ከደሙ ንጹህ ነኝ ይላሉ። ከአምስት ዓመታት በፊት ፕሬዝዳንቱ በምርጫ የተሸነፉ ሲሆን፣ አገሪቷም ካለፈችበት አስቸጋሪ ታሪክ ለማገገም በርካቶች ሥነ ጥበብን ጨምሮ ሌሎች መንገዶችን እየተጠቀሙ ይገኛሉ።

ፋጡ ቴሬማ ጄንግ ፎቶዎቿን 'ዘ ሜሞሪ ሐውስ' በተሰኘው ሙዚየም ውስጥ ተሰቅሎ ስትመለከት ሰውነቷን የሆነ ስሜት ወረረው።

ስሜቱ በያህያ ጃሜህ አገዛዝ ዘመን በቤተሰቧ ላይ የደረሰውን ስታስብ የሚሰማት የተለመደ ተስፋ መቁረጥ እና ሐዘን አልነበረም። ከእንባ ይልቅ ፈገግታ ቀደማት።

“ፎቶዎቼን ስመለከት በጣም ተደሰትኩ። በጣም ቆንጆ ናቸው። የዚያን ቀን ፈገግታዬን ማቆም አልቻልኩም” ብላለች።

የሬድዮ ቴክኒሻን የነበረው ባለቤቷ ሳንኩንግ ባላጆ በጃሜህ አስተዳደር ትዕዛዝ ‘ጠንቋይ ነው’ በሚል እንዲገደል ተደርጓል።

ሙሳ ካማራ አባቱ ጠንቋይ ተብሎ ሲገደል የ14 ዓመት ልጅ ነበር

የፎቶው ባለመብት, ANEKED

የምስሉ መግለጫ, ሙሳ ካማራ አባቱ ጠንቋይ ተብሎ ሲገደል የ14 ዓመት ልጅ ነበር

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለአክስታቸው ሞት ምክንያቱ ጥንቆላ ነው በሚልም በአውሮፓውያኑ 2009 መንግሥታቸው “ጠንቋዮችን” በማደን መግደል ጀመረ። ለሰባት ዓመታትም ይህ አደን የቀጠለ ሲሆን በአገሪቱም ውስጥ ከፍተኛ ሽብር እና መከፋፈል ፈጠረ።

በሙዝየሙ ላይ ለዕይታ የበቃው የፋጡ ፎቶዎች ከአውሮፓውያኑ 1994 - 2016 በሥልጣን ላይ በነበሩት ጃሜህ አሰቃቂ በደል የደረሰባቸው አስራ አንድ ግለሰቦች የፎቶ ታሪክ አካል ነው።

‘ዊ አር ኖት ደን’ (አልጨረስንም) የሚል ርዕስ የተሰጠው አውደ ርዕይ በጋምቢያ የመጀመሪያው መታሰቢያ ማዕከል በሆነው ዘ ሜሞሪ ሐውስ ለዕይታ ቀርቧል።

ማዕከሉን በበላይነት የሚያስተዳድረው ያለ ሕጋዊ ፍርድ ግድያ እና ሰዎች እንዲሰወሩ ማስገደድን የሚቃወመው (አኔኬድ) ሲሆን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉ ግለሰቦችን ወደ ፍርድ ለማቅረብ ግፊት እያደረገ ይገኛል።

ማዕከሉ የተመሰረተው በፊልም ባለሙያዋ እና የሰብዓዊ ተሟጋች በሆነችው ናና ጆ ዶው ሲሆን እሷም ግፍ ከደረሰባት ጥቂት ዓመታት በኋላ ነው ያቋቋመችው።

የማዕከሉ መስራች ናና ጆ ዶው

የፎቶው ባለመብት, JASON FLORIO

የምስሉ መግለጫ, የማዕከሉ መስራች ናና ጆ ዶው

በአውሮፓውያኑ 2013 ታዋቂ ነጋዴና ፕሬዝዳንት ጃሜህን በመቃወም የሚታወቁት አባቷ ሳውል ንዶ አብረዋቸው ወደ ሴኔጋል ይጓዙ ከነበሩት የቀድሞ ፖለቲከኛ ማሃዋ ቻም ጋር ደብዛቸው ጠፋ።

ከሦስት ዓመታት በፊት ጀንግለርስ የሚል መጠሪያ ያለውና በጃሜህ የሚመራው ልዩ ፖሊስ አባል የነበረ ግለሰብ የአስተዳደሩን ጥሰት ለማጣራት በተቋቋመው ኮሚሽን ሳውል ንዶን በፕሬዝዳንቱ የኦቾሎኒ እርሻ ላይ እንደቀበረ አምኗል።

እንደ ኦማር ጃሎው ምስክርነት ሳውል ንዶ ከሴኔጋል ታፍነው የተወሰዱት እና የተገደሉት በወቅቱ ፕሬዝዳንት ትዕዛዝ ነው።

“የአባታችን መጥፋት ቤተሰባችንን በታተነው” ትላለች ናና።

“በርካቶች ፊታቸውን አዞሩብን። ተላላፊ የሆነ ነገር ያለብን ይመስል ራቁን። የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማንም ተደርጓል” በማለት ታስረዳለች።

ናና እንደምትለው በአብዛኛው ሴቶች ተመሳሳይ ነገር እንዳጋጠማቸው ትናገራለች። በሜሞሪ ሐውስ ያቀረበችው የፎቶ አውደ ርዕይም ትኩረቱን ያደረገው “የማይታየው እንዲታይ” በማድረግ ላይ ነው።

በዚህም በጃሜህ የሥልጣን ዘመን የተከሰቱ ጥሰቶችን ማጋለጥ፣ ታሪክን ማቆየትና በሂደቱም ፈውስ የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግ ነው።

የናና አባት ሳውል ንዶ

የፎቶው ባለመብት, Nana- Jo- Ndow

የምስሉ መግለጫ, የናና አባት ሳውል ንዶ

ሜሞሪ ሐውስ ፎቶዎችን ጨምሮ በዘፈቀደ ተገድለዋል እንዲሁም በግዳጅ ጠፍተዋል የተባሉ ሰዎች መታወቂያዎችን፣ አልባሳትን እና ሌሎች ቁሶችን ይዟል።

ትምህርት ቤቶች ስለአገራቸው ታሪክ እንዲያውቁም በሚል የጋምቢያ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲጎበኙ በዝርዝሩ ካስቀመጣቸው ስፍራዎች አንዱ ነው።

“አብዛኞቹ ተማሪዎች የተወለዱት በጃሜህ የአስተዳደር ዘመን ነው። ስለዚህ የሚያውቁት አምባገነንነትን ብቻ ነው” ስትል ከናና ጋር የምትሠራ የአጎቷ ልጅ ሲራ ንዶ ትናገራለች።

“እናም ተማሪዎቹ አምባገነንነት የተለመደ የመንግሥት ሥርዓት እንዳልሆነ እንዲያውቁ ማድረግ አለብን” በማለት ታስረዳለች።

ሲራ ንዶው “አምባገነንነትን መርሳት” ትለዋለች።

አውደ ርዕዩም ታዳጊዎች ስለሰብአዊ መብቶች እና ስለሽግግር ፍትሕ የሚማሩበት ሥልጠናዎችን ያካትታል።

‘ዊ አር ኖት ደን’ የፎቶ አውደ ርዕይ በእነዚህ ሥልጠናዎች ያለፉትን በሮሄይ ቻም፣ ፋጡ ንዱሬ እና ሴሲሊያ ዉዳይ ሳንያንግ በሞባይል ስልኮች የተነሱ ሥራዎችን አካቷል።

በዚህ ሥልጠና ወቅት፣ የ18 ዓመቷ ቻም እርሷም የሰብአዊ መብቶቿ እንደተጣሰ ተገነዘበች። በ10 ዓመቷ ወደ አንድ ታሪካዊ ቦታ ለትምህርት ቤት ጉዞ መሄድ ነበረባት። ይልቁንም ተማሪዎቹ በካኒላይ ወደሚገኘው የጃሜህ እርሻ ተወስደው በወታደሮች ቁጥጥር ስር በአስገዳጅ ሁኔታ የኦቾሎኒ ፍሬ እንዲለቅሙ ተደርገዋል።

“ይህ በግዳጅ የጉልበት ሥራ ነው ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ምክንያቱም በጣም ህፃን ነበርኩ” ትላለች።

ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

‘ጠንቋዮችን ማደን’

ለአውደ ርዕዩ ከቀረቡት 11 ታሪኮች ውስጥ ስድስቱ በጠንቋዮችን ማደን ላይ ያተኩራሉ።

ሰለባዎቹ ጠመንጃ በታጠቁ የፀጥታ ኃይሎች ተከበው ወደ ምስጢራዊ እስር ቤቶች ተወስደዋል። እርቃን መቅረት፣ መገረፍ፣ በጥንቆላ ግድያ መፈጸማቸውን እንዲናዘዙ ጫና እንደተደረገባቸው እንዲሁም ከዕፅዋት የተቀመሙ የሚያስቃዥ መድኃኒት እንዲጠጡ መገደዳቸውንም ያወሳሉ። 

አንዳንዶቹም ሕይወታቸው አለፈ። በአውደ ርዕዩ ላይ ከተካተቱት መካከል ብዙዎቹ አካላዊ ጉዳት፣ ከፍተኛ መረበሽ፣ ከጭንቀት እና ከመታወክ ጋር እየኖሩ ነው።

የፋጡ እናት ጠንቋይ ናት በሚል ክስ በወታደሮች ስትወሰድ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ነበረች። በዚያም ፅንሱን አጣች ከዚያም በኋላ ሁለት ፅንስ ጨንግፎባታል።

ፋጡ እናቷ ጠንቋይ ናት በሚል ውንጀላዎችም ምክንያት ትምህርት ቤት ውስጥ ከፍተኛ ትንኮሳና መጎሳቆል ደርሶባታል።

የ10 ዓመትም ልጅ እያለች ትምህርት ቤት መሄድ አቆመች። ያገባችውም ገና በልጅነቷ ነው። ባሏ በሥራ ላይ ሲሆን ቀኖቹን ብቻዋን ታሳልፋለች “ጓደኛ የለኝም” ትላለች። 

ፋጡ ማንነቷ እንዳይገለጽ በመጠየቋ አውደ ርዕዩ ላይ ሂጃብ ጠምጥማ ትታያለች።

ፋጡ

የፎቶው ባለመብት, ANEKED

ልክ እንደ ሌሎቹ ፋጡ ስለ ጠንቋይ ማደን ስትናገር በአውደ ርዕዩ ይህ የመጀመሪያው ነው።

ቀደም ሲል በእሷ እና በዘመዶቿ ላይ “ከዚህ የከፋ ነገር ይደርስ ነበር” በማለት ስለ ጉዳዩ ለመናገር እንደፈራች ታስረዳለች።

እሷ ብቻ አይደለችም። በአውሮፓውያኑ 2019 እና በ2021 አጋማሽ መካከል በፕሬዝዳንት ጃሜህ አስተዳደር ስለነበረው ጥሰትን ለሚመረምረው የእውነት፣ የዕርቅ እና ማካካሻ ኮሚሽን በርካታ ጋምቢያውያን አልመሰከሩም።

አንዳንዶች ምስክርነቶች በቀጥታ ፕሮግራሞች እየተሰራጩ ስለነበር በጣም የሚረብሹ ክስተቶችን ማውራት አልፈለጉም። ሌሎች ደግሞ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት በመፍራታቸው ነው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጃሜህ በኢኳቶሪያል ጊኒ በግዞት ላይ ናቸው፤ ነገር ግን አንዳንድ ጀሌዎቻቸው በመንደር፣ በመንግሥት፣ በጦር ኃይሉ እና በብሔራዊ መረጃ አገልግሎት የሥልጣን ቦታ ላይ ይገኛሉ።

ፋጡ ቴሬማ ጄንግ

የፎቶው ባለመብት, ANEKED

ጃሜህ ጋምቢያን ለቀው ወጥተዋል ነገር ግን በርካቶች አገዛዛቸው ያደረሰባቸው ስቃይ የማይሽር ቁስል ሆኖባቸዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕይወት ለፋጡ ቴሬማ እውነተኛ ትግል ሆናለች። የጠንቋይ ባለቤት ናት በሚል እንድትሸማቀቅና እንድታፍር ተደርጋለች። ልብስ በማጠብ ነው ትንሽ ገንዘብ የምታገኘው።

በርካቶች “አባታቸው ጠንቋይ ነው እያሉ ጎረቤቶቼ ልጆቼን እንዲቀላቀሉና አብረው እንዲበሉ አይፈቅዱላቸውም” ትላለች።

ነገር ግን በሜሞሪ ሐውስ ሙዝየም የእሷን ፎቶዎች እንዲሁም የባሏን ሃፍታን ለሙዚየሙ ያበረከተችውን የባህል ልብስ ማየት ከፍተኛ ደስታ እንዲሰማት አድርጓታል።

ማገገም እንደጀመረች ይሰማታል።

"ታሪኬን ሳካፍል ይህ የመጀመሪያዬ ነበር እና ፈውስ እንዳገኝ ረድቶኛል” ትላለች።