ለተሻለ ሕይወት አህጉራትን ያቆራረጠችው ዮርዳኖስ ያሳለፈችው ውጣ ውረድና አሟሟቷ

የፎቶው ባለመብት, Family
ዮርዳኖስ ብርሃነ ለተሻለ ሕይወት በሚል የተወለደችበትን ያደገችበትን ኤርትራን ጥላ ስትሰደድ የ15 ዓመት ታዳጊ ነበረች።
ከተሻለ ሕይወት በተጨማሪ ከቤተሰቦቿ ጋር ለመገናኘት ተስፋን በመሰነቅ ሁለት አህጉራትን፣ አፍሪካ እና አውሮፓን አቆራርጣለች።
ከዓመታት ረዥም እና አድካሚ ጉዞ በኋላ ሕይወት ዩናይትድ ኪንግደም ብታደርሳትም ከጥቂት ወራት በኋላ በአስከፊ ሁኔታ በስለት ተወግታ ተገደለች።
የዮርዳኖስ እህት የዚህች ታዳጊ ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተቀጨ ተናግራለች።
ጥልቅ ሃይማኖተኛ እና ለቋንቋዎች ፈጠን ያለ አቀባበል ያላት ዮርዳኖስ እንግሊዝ ከደረሰች በኋላ በበርሚንግሃም ከተማ ኑሮዋን መገንባት ጀምራ ነበር።
ዮርዳኖስ ከስድስት ወንድሞቿ እና እህቶቿ ጋር በመሆን በአፍሪካ ድሃ ከሚባሉ አገራት አንዷ ከሆነችው፣ በርካቶች በግዳጅ የብሔራዊ አገልግሎትን እንዲሳተፉባት በሚደረግባት እና ፖለቲካዊ ጭቆናን ለማምለጥ ከሚሰደዱባት ኤርትራ ነው ወደ አውሮፓ ያቀኑት።
“ዮርዳኖስ በጣም ዝምተኛ ነበረች፣ ትህትና የሞላት፣ ጨዋ እንዲሁም ንቁ ነበረች” ስትል ቅሳነት ብርሃነ ስለ ታናሽ እህቷ ተናግራለች።
“ደስተኛ ነበረች። ቋንቋን የመልመድ ያላት ችሎታዋ የሚገርም ነው። በፍጥነት እየተማረች ነበር። ከኤርትራ የመጡ ጓደኞችንም አፍርታ ኑሮን ጀምራ ነበር።”
ቤተሰቧ፣ ከሞተች በኋላ በኡኔት ጎዳና ወደሚገኘው የጋራ መኖሪያ ቤት ሲመጡ፣ የከተማዋን ቤተ መፃህፍት አባል መሆኗንና ጊዜያዊ የመንጃ ፍቃድ እንዳገኘች አወቁ።

የፎቶው ባለመብት, Family
በአቅራቢያዋ በሚገኝ ሱቅም ትሠራ ነበር። የሱቁ ሥራ አስኪያጁ ሶጊ አምራኒ ስለ ዮርዳኖስ ሲናገር ሁልጊዜ ደስተኛ፣ ፈገግታ የምታሳይ እና ቤተሰቦቿን ለመርዳት ደፋ ቀና የምትል ቆንጆ እና ቅን ሰው ነበረች ይላል።
“ጥሩ ሠራተኛ ነበረች፣ እዚህ ሱቅ የሠራችው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ቢሆንም ስትናገር በጣም ደስ የምትል፣ እንዲሁም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዋም በጣም ጥሩ ነበር” ብሏል።
“ሁሉም ደንበኞቻችን መሞቷን ሲሰሙ እያለቀሱ ነበር። እኔም አለቀስኩ በጣም መጥፎ እና አሳዛኝ ሁኔታ ነው” ብለዋል።
ቅሳነት ከዮርዳኖስ በሰባት ዓመት ብትበልጥም ሁለቱ በጣም የቀረበ ትስስር ነበራቸው።
“ኤርትራን ለቃ ከወጣችበት ዕለት አንስቶ ከመሞቷ ሁለት ቀን በፊት ድረስ በየቀኑ እናወራ ነበር። በጣም የቀረበ ግንኙነት ነበረን” ትላለች ቅሳነት።
“ከመሞቷ በፊት በነበሩት ሁለት ቀናት አላናገርኳትም” ብላለች ።
ቅሳነት ነዋሪነቷ በኖርዌይ ነው። ከኤርትራ በ19 ዓመቷ በአውሮፓውያኑ በ2014 ነው የወጣችው። በአውሮፓም ኑሯዋን ካደረገች በኋላ ትምህርቷን ቀጥላለች፣ በመንከባቢያ ማዕከል ውስጥ ሰርታለች እንዲሁም በቅርቡ ወልዳለች።
ቅሳነትም ቢሆን የስደት ጉዞዋ ረጅም ነው፤ ከኤርትራ ከወጣች በኋላ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን ሊቢያ ከዚያም የአውሮፓ አገራቱን ጣልያን፣ ጀርመን፣ ስዊድንን አቆራርጣ ነው ኖርዌይ የገባችው። ይህ ጉዞ አንድ ዓመት ፈጅቶባታል።
“ጉዞው መግለጽ በማልችለው ሁኔታ ፈታኝ ነበር። በተለይም በሊቢያ የሰሃራ በረሃን ሳቋርጥ በጣም ፈትኖኝ ነበር። ሕይወትን አደጋ ላይ ጥሎ የሚደረግ ጉዞ ነበር” ትላለች።
በአውሮፓውያኑ 2017፣ የ15 ዓመቷ ዮርዳኖስም ተመሳሳይ አድካሚ ጉዞ ጀመረች።
ጉዞዋ ከእህቷ ቅሳነት ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ረዘም ያለ ጊዜ ወሰደ። በሊቢያ ለሰባት ወራት የቆየች ሲሆን፣ ከዚያም በሕይወት የወጣችው በተአምር እንደሆነ ቅሳነት ትናገራለች።
“በጣም መጥፎና አደገኛ ነበር የሊቢያ ቆይታዋ። በጣም መጥፎ ነገሮችም አጋጥመዋታል” ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Family
ዮርዳኖስ እና አብረዋት የነበሩት መንገደኞች በመቶዎች በተጨናነነቁ መጋዘኖች ወለል ላይ ተኝተዋል። ሕይወታቸውን ለማቆየት አነስተኛ ምግብ ያገኙ ሲሆን፣ መድኃኒት እና ምንም አይነት የንጽህና መጠበቂያ እቃዎችን የማያገኙበት ሁኔታ ነበር።
ጥቃቶች እንዲሁም መጠነ ሰፊ መደፈሮች ነበሩ። ነገር ግን ዮርዳኖስ ደክማ እና ታማ ስለነበር እንዳልተደፈረች ቅሳነት ታምናለች።
ዮርዳኖስ ወደ አውሮፓ ስትገባም በእርግጥም በጠና ታማ ነበር፣ ጣሊያን የደረሰችውም በቃሬዛ ነበር።
በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የተሳፈረችበት ጀልባ በውቅያኖስ መካከል መስራት ማቆሟን ተከትሎ የአካባቢው ባለሥልጣናት ሕይወቷን ታድገውታል።
“ህመሟ በዋናነት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዲሁም በቆዳዋ ላይ የተከሰተው የእከክ ቁስለት ከፍተኛ ትኩሳትን አምጥቶባታል። በደረቷ ላይ ችግሮች የነበሩ ሲሆን ልቧ በጣም እየመታ ነበር” ስትል ቅሳነት ታስታውሳለች።
“ጣሊያን በደረሰችበት ጊዜ በጣም ደክማ ነበር። ወዲያውኑ ጣሊያን እንደገባች አላወቅንም ነበር። ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሆስፒታል እንደገባችና ህክምና እየተደረገላት መሆኑን ሰማን።”
ነገር ግን ጤንነቷን ለመመለስ ህክምናዋን እየተከታተለች ባለችበት ወቅትም የሌሎች ችግሮች ጅማሮም ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Family
ዮርዳኖስ ወደ ኖርዌይ መሄድ ችላለች። ሆኖም ቅሳነት በስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ እንድትኖርና ከእህቷም ጋር እንድትገናኝ ተፈቅዶላት ነበር።
ነገር በዚህ ሂደት ውስጥ እያለፈች ባለበት ወቅት በጣሊያን ‘የጣት አሻራ’ መስጠቷ ታወቀ።
በደንቡ መሰረት ስደተኞች መጀመሪያ የገቡበበት አገር ውስጥ ነው የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረብ ያለባቸው።
በዮርዳኖስም ላይ የተፈጸመው ይህ ነው፤ ከአውሮፓ ኅብረት አገራት መጀመሪያ የገባችው ጣሊያን ስለሆነ ባለሥልጣናቱ ወደ ጣሊያን ሊመልሷት ወሰኑ።
እህትማማቾቹ በዚህ ውሳኔ በጣም ደነገጡ።
“በኖርዌይ ቆይታዋ ደስተኛ ነበረች። ሰብዓዊ መብት የሚጠበቅባት ደኅንነቱ በተጠበቀ አካባቢ ውስጥ ነበረች” ብላለች ቅሳነት።
“ለትምህርቷ ከፍ ያለ ስፍራ ነበራት። እናም ቋንቋዋን በደንብ አሻሽላለች። ከእርሷ ሁለት ዓመት ቀድሜ ብመጣም ከዮርዳኖስ የተሻለ ቋንቋ መናገር አልችልም።”
“ስለ ሕይወት በእውነት ተስፈኛ ነበረች፤ አዎንታዊ አመለካከትም ነበራት። ወደ ጣሊያን ይመልሱኛል ብላ አልጠበቀችም።”
ወደ ጣሊያን የመመለሷን ዜና ለሁለቱም መቀበል ከባድ ነበር።
“እድሜዋ ገና 16 ዓመቷ ነበር። በእድሜ ስለምበልጣት እሷን መንከባከብ እችል ነበር። እህቷ መላ ቤተሰቧ ነበርኩ። ያደረጉት ነገር ስህተት ነበር። በዚያ እድሜ ከቤተሰብ መለያየት አልነበረባቸውም።”
ለቤተሰቡ የይግባኝ ዕድል እንኳን ሳይሰጣቸው ዮርዳኖስ በሳምንቱ ውስጥ ወደ ጣሊያን እንድትመለስ ተደረገች።
ከተወሰኑ ቀናት የችግር ኑሮ እንዲሁም ምግብ እየለመነች ወደ ቤልጂየም ተጓዘች። በቤልጂየም ከተተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) ጋር ግንኙነት ፈጠረች። ተቋሙም በእድሜዋ ምክንያት ዮርዳኖስ ወደ ኖርዌይ መመለስ አለባት ሲል ተከራከረ።

የፎቶው ባለመብት, Family
ወደ ኖርዌይ የመመለሷ ጉዳይ ተቀባይነት አግኝቶ በስደተኞች መጠለያ ውስጥ ከወንድሟ ጋር መኖር ጀመረች።
“ከሦስት ወራት በኋላ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከጣሊያን መመለሷን የሚገልጽ ለፖሊስ የሚሰጥ ደብዳቤ ሰጧት። ይህም የጥገኝነት ጥያቄዋን እንዲከታተሉት በሚል ነበር” ትላለች ቅሳነት።
“ነገር ግን ፖሊሶች ለሁለት ወራት በእስር ቤት አቆይዋት። ሊለቋት ፈቃደኛ አልሆኑም። ወደ ጣሊያን እንድትመለስ ነገሯት። ዮርዳኖስ ወደ ጣሊያን እንድትመለስ ተገደደች።”
“በዚያ እድሜ ራሷን እንድትከላከል ሆነች፤ ለእሷ በጣም አስጨናቂ ነበር” ብላለች።
በኖርዌይ የሚኖር ጠበቃዋ አንድሬ ሞክልገርጄርድ፣ የትኛውም አገር የጥገኝነት ጥያቄን የማስተናገድ ኃላፊነት እንዳለበት የሚደነግገው ደብሊን የተሰኘው ደንብ ዮርዳኖስ ከዕድሜዋና ብቻዋን ከመሆኗ አንጻር እንዲሁም በኖርዌይም ቤተሰብ ስላላት ይህንን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ አንቀጾች አሉት ይላሉ።
“እንደ አለመታደል ሆኖ መከራከሪያዎቻችን ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻሉም። ብዙ ጊዜ በስደተኞች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆነው ይህም ሕግ ጥብቅ በሆነ መንገድ በዮርዳኖስ ላይ ተግባራዊ ሆኖባታል” ብለዋል።
ዮርዳኖስ ወደ ቤልጂየም ከሄደች በኋላ በአስከፊ ሁኔታ ለሰባት ወራት ቆየች። በዚህ ወቅት ቅሳነት ከአንዳንድ የቤልጂየም በጎ አድራጎት ድርጅቶች እርዳታ እንዳገኘች ትናገራለች።
በመጨረሻም ወደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በጭነት መኪና ተደብቃ ደረሰች። እነዚህ የበጎ አድራጎት ሠራተኞች ዩናይትድ ኪንግደም ከደረሰች በኋላ ግንኙነታቸውን ቀጠሉ።
“በጣም ጥሩ ሰዎች ነበሩ፤ ከዮርዳኖስ ጋር ቅርበት ነበራቸው። ደኅንነቱ ወደተጠበቀው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በመምጣቷ ተደስተው ነበር። ሁለት ጊዜም ሊጎበኟት መጥዋል።”
በዩኬ አንድ ዓመት ከቆየች በኋላ በስደተኝነት የመቆየት ፈቃድ ተሰጣት። ብሪታንያ ስትደርስ 18 ዓመቷ ነበር።
ቤተሰቦቿ መገደሏን የተረዱት ከማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Family
“ምን እንደተፈጠረ አላውቅም ነበር። እህቴ ደወለችልኝና ኢንስታግራም ላይ የሆነ ነገር አይተሻል ብላ ጠየቀችኝ።”
“'የምሰማው ምንድን ነው? ዮርዳኖስን አነጋግረሻታል?' አለችኝ እኔም አይ ለሁለት ቀናት አላናገርኳትም፤ ምን ተፈጠረ አልኳት” ብላለች።
ቅሳነት እና ባለቤቷ አንዳንድ የዮርዳኖስ ጓደኞች ጋር ደወሉ። እናም ዮርዳኖስ በሕይወት እንደሌለችና እንደተገደለች ሰሙ። በኋላም አካሏን ለመለየት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መምጣት ነበረባቸው።
“በጣም ነው ያስደነገጠን እናም እኔን ጨምሮ ሦስት ወንድሞች እና እህቶች አስከሬን ለመለየት በፍጥነት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መጣን።”
“እዚህ ስንደርስም በዚህ የሚኖሩ የኤርትራ ማኅበረሰብ ብዙ እርዳታ አድርገውልናል። ማረፊያ ሰጥተውናል እንዱሁም ሌሎች እርዳታ አድርገውልናል” ትላለች ቅሳነት።
ገዳይዋ ሃለፎም ወልደዮሐንስ ይባላል። በገዳይዋ የፍርድ ሂደት ላይ መገኘት ባትችልም 21 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ነገር ግን የዮርዳኖስ ቤተሰብ 21 ዓመታት በቂ አይደለም ይላሉ።
የዮርዳኖስ ታላቅ ወንድም ገዛኢ ብርሃነ ክበዶም “በፍርድ ሂደቱ ደስተኛ አይደለሁም። ዮርዳኖስ ጥሩ ልጅ ነበረች፣ እህቴን ጎዳት፣ ህይወቷን ነጠቃት፣ የተፈረደበት በቂ አይደለም” ብሏል።
ከመሞቷ ከሦስት ቀናት በፊት ዮርዳኖስ ጋር ተገናኝቶ የነበረ ሲሆን፣ መኪና መንዳት መማር እንደጀመረች እና እንዲሁም የወደፊት እቅዶቿን ነግራው ነበር።
“ወደ ትምህርት ቤት መመለስ እንደምትፈልግ፣ ዶክተር ወይም ነርስ መሆን ህልሟ እንደሆነ እና በመጨረሻም የመንግሥቱን ሁኔታ አይታ ወደ ኤርትራ በመሄድ ቤተሰባችን እና ሌሎች ወጣቶችን ለመርዳት እንደምትጥር ነግራኝ ነበር” ይላል።
“ዮርዳኖስ ልባም ነበረች። ዕድሜዋ ትንሽ ቢሆንም አስተሳሰቧ ከእድሜዋ በላይ ነበር” ይላል።












