በቲክቶክ ፍቺው ተፈጽሞ እስከ ግድያ የደረሰው ትዳር

የፎቶው ባለመብት, SANIA KHAN
ሳኒያ ካን ውጥንቅጥ የበዛበትን ጋብቻዋን በቃኝ ስትል አንዳንድ የደቡብ እስያ ሙስሊም ማኅበረሰብ አባላት “በሕይወቷ ያልተሳካላት” ሆኖ እንዲሰማት አድርገዋታል።
በቲክ ቶክ በኩል ደግሞ የማያውቋት ሰዎች ድጋፍ ሰጧት። አንዳንዶችም አጽናኗት። ይህ ግን የዘለቀው በቀድሞ ባልዋ እስክትገደል ብቻ ነው።
ይህ ታሪክ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊያበሳጭ የሚችል ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል።
ቦርሳዎቿ ተሞልዋል። በነጻነት ለመኖር ተዘጋጅታ ነበር።
ሳኒያ ካን ሐምሌ 21 ነበር ቺካጎ ኢሊኖይን ለቃ መውጣት የነበረባት ቀን። ወደ አገሯ ቻታኑጋ በማቅናት አዲስ ምዕራፍ የምትጀምርበት ቀን። ግን አልሆነም።
በምትኩ በዚያው ቀን በሬሳ ሣጥን ቴነሲ ወደ ሚገኘው ቤቷ ተመለሰች።
ከሦስት ቀናት በፊት የፖሊስ መኮንኖች ካንን ቺካጎ በሚገኘው ኮንዶሚኒየም በር አጠገብ ተዘርራ አገኟት። ቤቱ ከቀድሞ ባሏ የ36 ዓመቱ ራሂል አህመድ ጋር የምትኖርበት ነበር። ጭንቅላቷ በጥይት ተመትቶ ነው የተገኘችው። ሕይወቷም ወዲያው እንዳለፈ ተነግሯል።
ፖሊሶች በቦታው ደረሱ። አህመድ ሽጉጡን ወደ ራሱ በማዞር ጥይቱን ጠጥቶ የራሱንም ሕይወት አጠፋ።
ከቺካጎ ሰን-ታይምስ የተገኙ የፖሊስ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ጥንዶቹ “በፍቺ ላይ ነበሩ”። ከካን ተለይቶ በሌላ ግዛት ለመኖር የሄደው አህመድ ወደ ቀድሞ ቤታቸው 700 ማይል ያህል ተጉዞ ተመልሷል። መመለሱ ደግሞ ጋብቻቸውን ለማዳን በሚል ነው።
ካን በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተለይም በቲክ ቶክ እውቅና ካገኙ ወጣት ፓኪስታናዊ-አሜሪካዊ መካከል አንዷ ናት። በደቡብ እስያ ማኅበረሰብ ውስጥ ጋብቻን እና የፍቺ መገለልን ለሚዋጉ ሴቶች ድምጽ በመሆን የምታገለግል ፎቶግራፍ አንሺም ጭምር ናት። አሰቃቂው ግድያ ግን የሕይወቷ መጨረሻና አሳዛኝ ምዕራፍ ነበር።
ሞቷ ጓደኞቿን አስደንግጧል። ተከታዮቿ እና ጤናማ ባልሆነ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሌሎች ደቡብ እስያውያን ሴቶችም ክፉኛ ያዘኑበት ነው።
የዩኒቨርሲቲ ጓደኛዋ ብሪአና ዊልያምስ “29 ዓመት ሲሆናት ሁሉም እንደሚሳካ እና አዲስ ጅምሬ እንደሚሆን ትናገር ነበር። በጣም ጓጉታም ነበር” ትላለች።
ጓደኞቿ ከካን ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። ዋሾ ያልሆነች፣ ቅን አሳቢ እና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነች ይሏታል።
“ካን ምርጥ ጓደኛዬ ናት” የምትለው የ31 ዓመቷ መህሩ ሼክ “ያላትን የምትሰጥ ሰው ነበረች” ስትል ትገልጻታለች።
“በሕይወቷ ውስጥ አንዳንድ አስቸጋሪ ጊዜያት እያሳለፈች ጭምር መጀመሪያ ደውላ ቀንህ እንዴት እንደሆነ ትጠይቃለች።”
ተቀባይነቷን መጀመሪያ በገነባችበት ኢንስታግራም ላይ ለፎቶግራፍ ያላትን ፍቅር እንዲህ ስትል ገልጻለች- “ሰዎች ከካሜራ ፊት ለፊት ራሳቸውን እና እርስ በርስ እንዲዋደዱ እረዳለሁ” ትላለች።
ካን ሠርግ፣ ልደት እና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ በመገኘት ፎቶ ታነሳለች። ብዙ ደንበኞቿ ትልቅ ክፍያ ይከፍሏታል። ለብዙ ጓደኞቿም በነጻ ጭምር ሠርታለች።
“ከካሜራው ጀርባ ነው ብዙ ሕይወቷ ያለው። ሰዎች በካሜራ ፊት እንዲመቻቸው በማድረግ ጥልቅ ስሜትን እና ደስታን የመፍጠር ችሎታ ነበራት” ትላለች ሼክ።
በሕይወቷም ተመሳሳይ ደስታን ፈለገች። ከአህመድ ጋር ለአምስት ዓመታት ያህል በጓደኝነት ቆይተው እአአ ግንቦት 2021 ተጋቡ። ወደ ቺካጎ አቅንተው ጎጆ ቀለሱ።
አንድ የልጅነት ወዳጇ “አስደናቂና ትልቅ የፓኪስታን ሠርግ ነበር። ነገር ግን ትዳሩ የተመሰረተው በውሸትና በማታለል ላይ ነው” ትላለች።
አህመድ ለረጅም ጊዜ የቆየ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ነበረበት ይላሉ የካን ጓደኞች። ጥንዶቹ ከመጋባታቸው በፊት ብዙውን ጊዜ የረዥም ርቀት ግንኙነት ነበራቸው። ይህም ተጣጠጥሞ አብሮ መኖር ላይ ያላቸውን ክፍተት እንዳያውቁ ሳያደርግ አይቀርም ይላሉ እኚሁ ጓደኞቿ።
ችግሮቹ ባለፈው ታኅሣሥ ትልቅ ደረጃ መድረሳቸውን ጓደኛዋ ትናግራለች። ካን አህመድ የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለበት ነገራት። ካን የደኅንነት ስጋት ተሰማት። ቢቢሲ ከአህመድ ቤተሰብ አስተያየት ለማግኘት ሞክሮ አልተሳካለትም።
የካን ቤተሰብ አባላት በካን ጓደኞች በኩል ለቀረበላቸው ጥያቄ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
አሜሪካ ውስጥ በየሳምንቱ በደርዘን የሚቆጠሩ ራስን ከማጥፋት ጋር የተያያዙ ግድያዎች ይፈጸማሉ። እንደ ‘ቫየለንስ ፖሊሲ ሴንተር’ ከሆነ ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት በፍቅር አጋሮች የሚፈጸሙ ናቸው ይላል።

የፎቶው ባለመብት, SANIA KAHN
ከግንኙነቶች ችግሮች ውስጥ በአጋሮች ለሚደርሰው ጥቃት የአዕምሮ ህመም ከዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች አንዱ ነው። የቤት ውስጥ ጥቃት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ሴቶች ትዳራቸው ለቀው በሚወጡበት ጊዜ በአጋራቸው ለመግደል በጣም የተጋለጡ ይሆናሉ።
ካን እስከ ታኅሣሥ ድረስ ስላለችበት ግንኙነት ምንም አልተነፈሰችም። በኋላ ግን ትዳሯ ከደስታ የራቀ መሆኑን ገለጸች ሲሉ ጓደኞቿ ተናግረዋል።
ካን በትዳሯ ውስጥ ስላጋጠማት ፈተናዎች ይፋ አደረገች። ባለቤቷ ቤቷ እንደማይተኛ እና ብዙ ጊዜ እንግዳ ነገር እንደሚያደርግ ገለጸች።
ድጋፍ እንዲያገኝ ወይም ወደ ህክምና እንዲሄድ ያቀረበችለትን ልመናዋን እንዳልተቀበለው በመንገር እና የአዕምሮ ጤና ችግሩ ሸክም እንደሆነባት ይሰማታል ነበር ብለዋል።
ካን ትዳሯን እንድትፈታ አንዳንድ ጓደኞቿ ሲነግሯት፣ ሌሎች ደግሞ በትዳሯ እንድትቀጥል መክረዋታል።
የ26 ዓመቷ ዊሊያምስ የድሮ ጓደኛዋን ለመጨረሻ ጊዜ በግንቦት ወር ቺካጎ ውስጥ ስታገኛት በነበራቸው በቆይታ ወቅት ተሰብራ እንደነበር ተመልክታለች።
“ፍቺ አሳፋሪ እንደሆነ እና በጣም ብቸኝነት እንደሚሰማት ነገረችኝ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። ካን “ሰዎች ምን ይላሉ?” የሚሉትን ቃላት በተደጋጋሚም ትጠቀማለች። በኡርዱ እና በሂንዲ ‘ሎግ ኪያ ካሄንጌ’ ይባላል።
የካን እናት እና አባት ሰማንያቸውን ቀደዋል። በፍቺ ውስጥ ያደደገች ልጅ የሆነችው ካን አንዳንድ የደቡብ እስያ ማኅበረሰቦች ትዳራቸውን ለቀው በሚወጡ ሴቶች ላይ የሚያደርሱትን መገለል በዐይኗ እንዳየች ተናግራለች።
በቺካጎ ላይ የተመሰረተው እና በአብዛኛው የጓደኛ ጥቃት ለደረሰባቸው ለደቡብ እስያውያን ምስጢራዊ አገልግሎት የሚሰጠው የ‘አፕና ጋሃር’ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኔሃ ጊል “በተጎጂው ቤተሰብ ዙሪያ ብዙ የባህል ጫና አለ” ብለዋል።
ብዙ የደቡብ እስያ ማኅበረሰቦች ሴቶችን ዝቅ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ቁጥጥር እንደሚያስፈልጋቸውም ማሳየታቸውን ቀጥለዋል። “ባህሎቹ በጣም ተመሳሳይ ናቸው። ስለዚህ ከግለሰብ ደኅንነት ይልቅ ለቤተሰብ ወይም ለማኅበረሰብ ደኅንነት ቅድሚያ ይሰጣሉ” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, SANIA KAHN
ካን በጓደኞቿ ድጋፍ የፍቺ ጥያቄ አቀረበች። ሰማንያውን ለመቅደድ ፍርድ ቤት ለነሐሴ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
ባሏ እሷ ወዳላችበት እንዳይደርስ የሚያደርግ የእገዳ ትዕዛዝ አስገባች። የበሯንም ቁልፎች መቀየሯን ጓደኞቿ ተናግረዋል።
እናም ራሷ በማኅበረሰቧ ውስጥ ያላት ገጽታ እንደ “ጥቁር በግ” መሆኑን በመግለጽ ታሪኳን በቲክቶክ ላይ ማካፈል ጀመረች።
አንድ መልዕክቷ እንዲህ ይላል፡ “እንደ ደቡብ እስያ ሴት በፍቺ ውስጥ ማለፍ ማለት አንዳንድ ጊዜ በሕይወት ያለመሳካት ያህል ነው።”
“ባሌን ጥዬ ከሄድኩ ሰይጣን እንዲያሸንፍ መፍቀድ ነው፣ ሲሉ የቤተሰቤ አባላት ነግረውኛል። በወሲብ ንግድ እንደምትተዳደር ሴት እንድለብስ እና ወደ ትውልድ መንደሬ ከተመለስኩ ራሳቸውን እንደሚያጠፉ ተናግረዋል” ብላለች።
የአባቷ ስም እንዳይገለጽ የጠየቀችው የ28 ዓመቷ ናቲ የተባለች ሌላዋ የዩኒቨርስቲ ጓደኛዋ፣ ካን በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በስፋት መነጋገሪያ የሆነችበትን ጊዜ በደንብ ታስታውሳለች።
“እጅግ የተለየ ነገር ነበር የሠራችው። ላደርገው ያሰብኩት ይህንን ነው፣ ስለ ትዳሬ መረጃ ለማሰራጨት እና ሴቶች ከመርዛማ ትዳራቸው ለቀው እንዲወጡ መሪ ለመሆን ነው” አለችኝ።
አንዳንዴ መጥፎ መልዕክቶች ቢደርሷትም፣ እያንዳንዱን መልዕክቷን ካሳወቀች በኋላ ግን መጽናናትን እና ጥንካሬን ታገኝ ነበር።
ካን ህይወቷ ባለፈበት ወቅት ከ20,000 በላይ ሰዎች በቲክ ቶክ ይከተሏት ነበር።
ሙስሊሟ ፓኪስታናዊት-አሜሪካዊት እና የ35 ዓመቷ ቢስማ ፓርቬዝ ከተከታዮቿ አንዷ ነበረች።
“አስታውሳለሁ የእሷን የመጀመሪያ ቪዲዮ ካየሁት በኋላ ጸለይኩላት” ትላለች።
“በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሴቶች ‘ሳብር' [በአረብኛ ትዕግስት ማለት ነው] እንዲኖራቸው ይነገራቸዋል። ትዕግስት ግን መፍትሄ አይሆንም።”
ንግግሩ የከፋው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው።
አፕና ጋሃር በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ካን የሞተችበትን አንደኛ ወር ለማሰብ በበይነ መረብ ውይይት ለማድረግ ማቀዱን ገልጿል። የቻታኑጋ የሥነ ጥበባት እና ሳይንስ ትምህርት ቤት የቀድሞ ክፍል ጓደኞቿ በስሟ ስኮላርሺፕ አቋቁመዋል።
“ሁሉም ሰው ዝም ዝም ይላል። ማኅበራዊ ሚዲያው ግን ይህ ምን አይነት ዓለም አቀፍ ችግር እንደሆነ እንድትገነዘቡ ያግዛል” ስትል ፓርቬዝ ተናግራለች።
“ሁልጊዜም ሴቶች ራሳቸውን እንዲከላከሉ እንነግራቸዋለን። ሴቶችን የሚያከብሩ ወንድ ልጆችን ማሳደግም ግን አስፈላጊ ነው። ይህ ሥልጠና ከቤት ይጀምራል። እያንዳንዱ ቤተሰብ ይህን ለውጥ ማምጣት አለበት።”












