ሕንዳውያኑ ወላጆች የልጅ ልጅ አላሳየንም ያሉትን ልጃቸውን ከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜን ሕንድ በምትገኘው የኡታራካንድ ግዛት የሚኖሩ ሕንዳዊያን ወላጆች የልጅ ልጅ አልወለዱልንም ሲሉ ብቸኛ ልጃቸውን እና ባለቤቱን ፍርድ ቤት ገተሩ።
ሳንጄቭ እና ሳድሃና ፕራሳድ እንደሚሉት ልጃቸውን ለማሳደግ የነበራቸው አንጡራ ሃብት አፍስሰውበታል። የበረራ ትምህርቱን እንዲከታተል ከመርዳት ባለፈም ድል ባለ ድግስ እንደዳሩት አስታውቀዋል።
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የልጅ ልጅ ካላገኙ 650 ሺህ ዶላር ካሳ ከልጃቸው እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል።
ልጃቸውን እና ሚስቱ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡም።
ያልተለመደ ነው የተባለው ክስ "ስነ-ልቦናዊ ጉዳት" በማድረስ በሚል የቀረበ ነው።
አባት ፕራሳድ ያላቸውን ጥሪት በሙሉ ልጃቸው የአውሮፕላን አብራሪ እንዲሆን 65 ሺህ ዶላር ወጪ አድርገው አሜሪካ እንደላኩት ተናግረዋል።
እንደ ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ዘገባ ከሆነ ልጁ ወደ ሕንድ ከተመለሰ በኋላ ሥራ በማጣቱ ለሁለት ዓመት ያህል በወላጆቹ ሲደገፍ ቆይቷል።
የ35 ዓመቱ ሽሬይ ሳጋራ በኋላ ላይ ሥራ ለማግኘት ችሏል። እአአ በ2016 ሹብሃንጊ ሲንሃን ሲያገባም ወላጆቹ የልጅ ልጅ እናገኛለን በሚል ተስፋ እንደዳሩት አስታውቀዋል።
እንደ ወላጆቹ ከሆነ ሠርጉን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል መደገሳቸውን አስታውቀዋል። 80 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ቅንጡ መኪና እና ከሃገር ውጭ የጫጉላ ሽርሽር እንዳዘጋጁለትም ተናግረዋል።
"ልጄ ካገባ ስድስት ዓመት ቢሆነውም ልጅ የመውለድ ዕቅድ የላቸውም" ያሉት አባት "አብሮን የሚሆን የልጅ ልጅ ቢኖረን ሕመማችንን እንረሳ ነበር" ብለዋል።
ጠበቃቸው ኤኬ ስሪቫስታቫ ለዘ ናሽናል እንዳስታወቁት ጥንዶቹ ገንዘቡን የፈለጉት "በስነ-ልቦናዊ ጉዳት ምክንያት ነው።"
"የልጅ ልጅ ማየት የሁሉም ቤተሰብ ፍላጎት ነው። አያት ለመሆን ለዓመታት ጠብቀዋል።"
ሃሪድዋር የተከፈተው ክስ ከቀናት በኋላ ይሰማል።














