ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ጥንዶች ስናይ ለምን ይጎረብጠናል?

ኅብረተሰብ የምንለው የሰዎች ውቅር መብረቃዊ ለውጥ እያሳየ ነው። ትላንት 'አበስኩ ገበርኩ' ያሰኘው ድርጊት ዛሬ ከቁብ የሚቆጥረው ጠፍቷል።
ይህ ይኹን እንጂ ሰዎች፣ አሁንም ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ጥንዶች ሲያዩ ይበረግጋሉ።
ይህ ለምን ሆነ?
በፈረንጆቹ 2019 ሌዎናርዶ ዲካፕሪዮ የተሰኘው ዝናው ተዋናይ የፍቅር አጋሮቹ ያደረጋቸው ሴቶችን የሚያሳይ አንድ ሰንጠረዥ የበይነ መረብ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በወቅቱ ይህ ስሙ የከበደ ተዋናይ ዕድሜው 44 ነበር። ነገር ግን የፍቅር አጋር ያደረጋቸው ሴቶች እድሜ 25 አሊያም ከዚያ በታች ናቸው።
26 ዓመት ሲሞላቸው በቃኝ ብሎ ከግንኙነቱ ራሱን ያገላል።
አንዳንዶች ይህ ጉምቱ ተዋናይ ወጣት ሴቶችን የሚስብ አፈጣጠር አለው ሲሉ ያደንቁታል። ሌሎች ደግሞ "ኧረ እኩያህን ፈልግ" ይሉታል።
ይህ የሆሊውድ አርበኛ ግን አሁንም ከመርሁ ንቅንቅ አላለም። የዘንድሮ የፍቅር አጋሩ ካሚላ ሞሮን ዕድሜዋ 24 ነው።
የዲካፕሪዮ የፍቅር ሕይወት አንድ ሃሳብ እንድንጭር ያደርገናል። የዕድሜ ልዩነት።
አንዳንዶች በጥንዶች መካከል ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ሊኖር ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ። የተቀሩቱ ደግሞ ይህ ሐሳብ ይሰቀጥጣቸዋል።
ደሚ ሙር የተባለችው ሌላኛዋ ነባር የሆሊውድ ተዋናይት አሽተን ኩቸር የሚባል ወጣት ተዋናይ የፍቅር አጋሯ አድርጋ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆና ነበር።
ኮለምቢያዊቷ የሙዚቃ ኮከብ ሻኪራም በ10 ዓመት ከሚያንሳት የባርሴሎናው ተከላካይ ዤራርድ ፒኬ ጋር ጎጆ ስትቀልስ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆና እንደነበር ይታወሳል።
በፈረንጆቹ 2014 አሜሪካ ውስጥ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው በጥንዶች መካከል ያለው የዕድሜ ልዩነት 2.3 ዓመት ነበር።
ይህ ጥናት ጨምሮ እንደሚጠቁመው አንድ በመቶ የሚሆኑ አሜሪካዊያን ባልና ሚስት የ28 ዓመት ልዩነት አላቸው።
ምዕራባዊያን በጠቅላላው በአማካይ የስምንት ዓመት የዕድሜ ልዩነት ትዳራቸው ላይ ይንፀባረቃል።
በጥንዶች መካከል ስላለው የዕድሜ ልዩነት ያለን አስተሳሰብ የዘመናት ስነ-ልቡናዊ አሠራራችን፤ ወግና ባሕላችን ውጤት ነው።
ባለፉት ምዕተ አመታት እየተስተዋለ የመጣው የፆታ እኩልነት ሰዎች ትክክል ነው ብለው ወደሚያስቡት የዕድሜ ልዩነት ገፍቶናል።
ነገር ግን ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ጥንዶች አሁንም ብዙ ዓይን ያርፍባቸዋል። የዘርፉ አጥኚዎች ግን "ተዉት ይህ የሰዎች አስተሳሰብ እያዘገመ ይቀየራል" ይላሉ።
ዝግመታዊ ግፊት
ዲካፕሪዮ ከዕድሜው ግማሽ የሚያንሱትን ሴቶች እየፈለገ ማጥመዱ የጎረበጣቸው ሰዎች ምክንያት አላቸው።
በጥንዶች መካከል ሰፋ ያለ የዕድሜ ልዩነት መኖሩ ለዘመናት በበርካታ ማኅበረሰቦች ባሕል እንደ ሃጥያት ይቆጠር የነበረ አሁንም የሚታይ ድርጊት ነው።
"በርካታ ማኅበረሰቦች በዕድሜ ከሚበልጥ ወይም ከሚያንስ ግለሰብ ጋር የሚደረግ የፍቅር ግንኙነትን ያወግዙታል" ይላሉ የስነ-ልቡና አማካሪዋ ዶ/ር ኤሌና ቱሮኒ።
ምንም እንኳ ሴቶች የማርገዝ ዕድላቸው በፍጥነት እየቀነሰ ቢመጣም ወንዶችም ዘር የሚያፈራው ተፈጥሯዊ ከረጢታቸው ከ35 ዓመት በኋላ እየነጠፈ ይመጣል።
ይህ ደግሞ ልጅ በልጅነት ወደሚባለው የሃገራችን ብሂል ያመጣናል።
ነገር ግን ልጅ የማሳደግ ብቻ ሳይሆን በዕድሜ ከሚቀራረብ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት መመሥረት አዋጭ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
ጥናት እንደሚለው በዕድሜ የሚቀራረቡ ጥንዶች በሕይወት የሚያጋጥሟቸውን ውጣ ውረዶች በተመሳሳይ መልኩ የመወጣት ኃይል አላቸው።
"በትዳር የመጀመሪያዎች 10 ዓመታት በዕድሜ የሚያንሳቸውን ሰው ያገቡ ሰዎች እፎይታን እንደሚያገኙ ይናገራሉ" የሚሉት ደግሞ በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ግሬስ ሎርዳን ናቸው።
"ነገር ግን እኝህ በመሃከላቸው ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ጥንዶች ከጊዜ ጊዜ ትዳርን ማጣጣም ያቆማሉ" ይላሉ ምሁሯ።
ምንም እንኳ እስካሁን ያለፍንበት ዝግመተ ለውጥ በዕድሜ ወደሚመሳሰለን የትዳር አሊያም የፍቅር አጋር ቢመራንም ማኅበረሰባዊና ምጣኔ ሃብታዊ ዑደቶቻችን ግን ይህን ሊጋፉት ይችላሉ።
በፈረንጆቹ 1990 በጥንዶች መካከል የነበረው የዕድሜ ልዩነት በ2000 ከነበረው እጥፍ ነበር። ይህም ማለት በዚያ ዘመን በዕድሜ የሚያንስ አሊያም እጅግ የሚበልጥ ሰው ማግባት ብርቅ አልነበረም።
ለዚህ ምክንያቱ ስነ ሕይወት እና ምጣኔ ሃብት ናቸው።
ለምሳሌ አንድ የ50 ዓመት ጎልማሳ ትዳር መያዝና ልጅ መውለድ ቢፈልግ የዕድሜ እኩያው የሆነች ሴት ከማግባት ይቆጠባል። አልፎም የቤቱ አባወራ ስለሆነ በዕድሜ የምታንሰውን ሴት የማግባት ዕድሉ የሰፋ ነው።
በ19ኛ ክፍለ ዘመን መገባደጃና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አካባቢ ሴቶች ከአብዛኛው ሥራ የተገለሉ ናቸው።
በዚያ ዘመን ሴቶች ከእነርሱ የተሻለ ገቢ ያለው ወንድ ማግባት ይመርጣሉ። ወንዶች ደግሞ በወጣትነት ዘመናቸው ገንዘብ ሰብስበው በጎልማሳነታቸው ዘመን ትዳር መያዝን ይሻሉ።

የፎቶው ባለመብት, Alamy
ፍርደ ገምድልነታችን ለምን?
ሴቶች ምጣኔ ሃብታዊ ኃይል እያገኙ ሲመጡ ግን በዕድሜ የሚበልጥ አጋርን የመፈለግ ፍላጎት እየወረደ መጣ።
ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ጥንዶችን ማየትም ያልተለመደ ሆነ። አልፎም ይወገዝ ጀመር።
ዘንድሮ ምንም እንኳ ብዙዎች ፍቅርን በሚመለከት ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸው ቢሆኑም በዕድሜ እጅግ የበለጠ አሊያም ያነሰ አጋር የሚፈልጉ ሰዎች ለሃሜት የተጋለጡ ናቸው።
ሰዎች ፍርደ ገምድል ናቸው። የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ጥንዶች ሲያዩ ፍቅር ነው ያገናኛቸው ማለት አይቀናቸውም። ከኋላው ሌላ ምክንያት እንዳለ ያስባሉ።
"ሹገር ማሚ" አሊያም "ሹገር ዳዲ" አልፎም "ጎልድ ዲገር" የተሰኙት ስያሜዎች የተፈበረኩትም ይህን ተከትሎ ነው።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በዕድሜ ከሚበልጧቸው ብሪጄት ጋር ትዳር ሲመሰርቱ ብዙ ተብጠልጥለው እንደነበር ልብ ይሏል።
በ1963 ዩኬ ውስጥ የተሠራ ጥናት 15 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በዕድሜ ከሚያንሳቸው አጋር ጋር ትዳር እንደመሠረቱ ያሳያል።
በ1998 ይህ አሃዝ ወደ 26 በመቶ አደገ። 2011 ላይ ደግሞ ከ1970ዎቹ ሲነፃፀር በሶስት እጥፍ አድጓል።
በዕድሜ የሚያንሳቸውን ወንድ የሚያገቡ ሴቶች ብዙ ፍርደ ገምድል አስተያየት ያስተናግዳሉ።
"ሰዎች ስንባል ፍርደ ገምድል ነን። ጎረቤታችን ከእኛ ባህሪ ወጣ ያለ ነገር ሲያደርግ ካየን ትኩረታችንን ይስበዋል" ይላሉ ሎርዳን።፥
ኪም ካርዳሺያን የተሰኘችው ታዋቂ የ41 ዓመት ሴት ከ28 ዓመቱ ኮመዲያን ፒት ዳቪድሰን ጋር የፍቅር ግንኙነት ስትጀምር ብዙ ተብላ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ይለመድ ይሆን?
አሁን አሁን ማኅበረሰቡ የተለያዩ የግንኙነት ዓይነቶችን መቀበል ጀምሯል።
ቱሮኒ እንደሚሉት የግንኙነት ዓይነቶች እየተለመዱ በመጡ ቁጥር ሁኔታው ተቀባይነት እያገኘ ይመጣል።
ነገር ግን ይህ ግምት ምሁሯ እንዳሰቡት ላይሆን ይችላል።
አደራው ያለው ወጣቶች ላይ ነው። ወጣቶች ይህን ባሕል እየተቀበሉት ከመጡ ሁኔታው ሊቀየር ይችላል።
"እኔ በጠቅላላው ሰዎች ሕይወትን በፈለጉት መንገድ መምራት እንዲችሉ መፍቀድ አለብን ባይ ነኝ" የሚሉት ደግሞ ሎርዳን ናቸው።















