አየርላንድ፡ ከ40 ዓመታት ትውውቅ በኋላ በ80ዎቹ እድሜያቸው የተጋቡት ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, RTE
በ80ዎቹ እድሜ ያሉ የእድሜ ባለ ፀጋ አየርላንዳውያን ከአርባ አመት ትውውቅ በኋላ ከሰሞኑ ተጋብተዋል።
የ86 አመቱ ጆን በርሚንግሃምና የ83 አመቷ ሜሪ ሎንግ ከሰሞኑ በአየርላንድ በሚገኝ የቱላሞር የጤና ማዕከል ጋብቻቸውን መፈፀማቸው ታውቋል።
"ልባችን አያረጅም" ያሉት ጥንዶች ጋብቻቸውን ለመፈፀም ለረዥም አመት አቅደው የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሲያራዝሙት ቆይተዋል።
በአሁኑ ወቅት የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የበለጠ ጋብቻቸውን እንዲያራዝመው አልፈቀዱም።
የጆን በርኒንግሃም ልጅ ካሮላይን ለቢቢሲ ጉድ ሞርኒንግ ፕሮግራም እንደተናገረችው መጋባታቸውን እንደ ትልቅ ድል እንደሚያዩት ነው።
ካሮሊን እንደምትለው ጥንዶቹ ቆየት ያሉ ባህላዊ እሴቶችም ስላሉዋቸው ነው መጋባትን እንደ አማራጭ ያዩት ብላለች።
ጥንዶቹ ትውውቃቸው በጎሮጎሳውያኑ 1976 ሲሆን በአንድ ሆቴል ውስጥ ነው። ከዚያም ለጥቂት ዓመታት በኋላ አልተገናኙም።
እንደገና ሲገናኙም ሜሪ "ወንዶች በቃኝ" ያለችበት ጊዜ ነበር፤ ነገር ግን በመጨረሻ ቡና አብራው ልትጠጣ ተስማማች።
ሆኖም በመጀመሪያው ቀን ምንም እንደማይፈጠር አሳውቃው ነበር ቡና አብራው ልትጠጣው መስማማቷን ለአይሪሹ ሚዲያ አርቲኢ ተናግረዋል። ከዚያ በኋላ ያለው ታሪክ ነው።
"በእድሜ ባለ ፀጋ እንደሆኑ ሰዎች ዓለምን አያይዋትም፤ ለየት ባለ መልኩ ነው ነገሮችን የሚረዱት" ትላለች ካሮላይን
ጋብቻቸውን ላለመፈፀም በርካታ ችግሮች ተደቅነውባቸው እንደነበር የምትናገረው ካሮላይን ዋነኛው ጉዳይም በአየርላንድ እስከ ጎሮጎሳውያኑ 1996 ድረስ ፍቺ መፈፀም ባለመቻሉ ነው።
ጆን በርኒንግሃም ከሌላ ሴት ጋር በጋብቻ ተሳስረው የነበረ ቢሆንም መፍታት ቢፈልጉም በህጉ ምክንያት አልተቻለም ነበር። ሜሪም በበኩላቸው ከቤተ ክርስቲያንና ከግዛቲቷ የፍቺ ፈቃድ ማግኘት ነበረባቸው።
እነዚህ ችግሮች ከተቀረፉ በኋላም ሁለቱም በእድሜ እየገፉ በመሄዳቸውና ዛሬ ነገ ሲሉም ጊዜው ማለፉን ካሮላይን ትናገራለች።
"ሁለቱም ማርጀታቸውን ያውቁታል እነሱም ይህንኑ ደጋግመው ይናገራሉ። ከመጋባታቸው በፊት አንዳችን እንሞታለን የሚልም ፍራቻ ነበራቸው። እናም ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው የሰርጉን ዝግጅት ለማድረግ የወሰንኩት" ብላለች ካሮላይን።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያትም ሰርጋቸው የደመቀ ባይሆንም የተወሰኑ ቤተሰቦችና ጓደኞቻቸው ሰርጋቸውን መታደም ችለዋል።












