ኮቪድ-19፡ በኮሮናቫይረስ መመሪያዎች ምክንያት በጣልያን ከፍተኛ ተቃውሞ ተነሳ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ጣልያን እንደ አዲስ ያገረሸውን ሁለተኛ ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት መመሪያዎችን ማሳለፏን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ተነስቷል።
በበርካታ ከተሞቿም ግጭቶች ተቀስቅሰዋል ተብሏል። በቱሪን ከተማም በቤት የሚሰራ ተቀጣጣይ ጠርሙሶች በፖሊሶች ተወርውሮባቸዋል ተብሏል።
በሚላን ተቃዋሚዎችን ለመበተን ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ የተጠቀመ ሲሆን በኔፕልስም እንዲሁ ግጭቶች መፈጠራቸው ሪፖርት ተደርጓል።
ለነዚህ ተቃውሞዎች መነሻ የሆነውም ማዕከላዊው መንግሥት ሬስቶራንቶች፣ መጠጥ ቤቶችና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች (ጂሞች) ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት በኋላ እንዳይሰሩ እግድ በመተላለፉ ነው።
ሌሎች ግዛቶችም እንዲሁ የምሽት ሰዓት እላፊ አዋጅ ማስተላለፋቸውም ተሰምቷል፤ ከነዚህም ውስጥ ሎምባርዲና ፔድሞንት ይገኙበታል።
ከሰዓት እላፊ በተጨማሪ ትምህርት በበይነ መረብ ወይም በርቀት እንዲሆን እንዲሁም ከከተማ መውጣትም ተከልክሏል።
ከነዚህም በተጨማሪ ሮምና ፓሌርሞም ከተሞችም ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ተነስቷል።
የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተነሳበት ወቅት አገሪቷ ወረርሽኙ ከመዛመት ለመቆጣጠር ያወጣቻቸው መመሪያዎችን በርካቶች ተቀብለውም ተግባራዊ አድርገውታል።
ክፉኛ በወረርሽኙ የተጎዳችው ጣልያንም ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ እግድ ጥላ ነበር።
በአሁኑ ወቅት የተላለፉት መመሪያዎችን ግን በርካቶች እየተቃወሙም ነው፤ በተለይም ትንንሽ የንግድ ቦታዎች ያሏቸው ጣልያናውን ከመጀመሪያው የእንቅስቃሴ እግድ ምክንያት ካጡት ገቢ በማገገም ላይ ነን ብለዋል። ሁለተኛ እግድ ከተደገመ ሙሉ በሙሉ እንከስራለንም እያሉ ነው።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ተቃውሞዎቹ በተወሰኑ ቦታዎችም ወደ ዝርፊያ መቀየራቸውም ተነግሯል። በማእከላዊ ቱሪን በሚገኝ የጉቺ የልብስ መደብር በተቃዋሚዎች ተዘርፏል ተብሏል።
በርካታ ተቃዋሚዎች ርችት በማፈንዳትም ከተሞቹን እንደሸፈኗቸው የሮይተርስ የዜና ወኪል የዘገበ ሲሆን ፖሊስም በምላሹ አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅሟል።
በሚላን የወጡ ሰልፈኞች "ነፃነት፣ ነፃነት፣ ነፃነት" እያሉ በመጮህና በመዘመር ተቃውሟቸውን የገለፁ ሲሆን ከፖሊስም ጋር ተጋጭተዋል።
ሚላን በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ የተመታቸው የሎምባርዲ ግዛት መዲና ናት።












