በአማራ ክልል በባለፈው ዓመት ብቻ 1 ሺህ 700 ሕፃናት ያለ እድሜያቸው ተድረዋል

የፎቶው ባለመብት, Eric Lafforgue/Art in All of Us
በአማራ ብሔራዊ ክልል በ2012 ዓ.ም ከ1 ሺህ 700 በላይ የልጅነት ጋብቻዎች መፈጸማቸውን የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ስማቸው ዳኜ ለቢቢሲ ገለፁ።
በአማራ ክልል የልጅነት ጋብቻ በስፋት የሚፈጸም መሆኑን ለቢቢሲ የገለጹት አቶ ስማቸው ዳኜ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ቁጥሩ ይበልጥ እንዲጨምር ማድረጉን አስረድተዋል።
ይህ መረጃ የተገኘው ስለጉዳዩ የሚቆረቆሩ ሰዎች በሚሰጡት መረጃ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ የተጠናከረ የመረጃ ስርዓት ስለሌለ ቁጥሩ ይህ ብቻ ነው ለማለት ያስችግራል ብለዋል።
አብዛኛው የልጅነት ጋብቻ የህግ ተጠያቂነትን ለመሸሽ በድብቅ የሚፈጸም መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው በዚህ ምክንያት ይፋ ሳይደረግ የሚቀር እንዳለም ጠቁመዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት /ዩኒሴፍ/ እኤአ 2019 ባደረገው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ የልጅነት ጋብቻ በስፋት ከሚታይበቸው 50 ወረዳዎች ውስጥ 23ቱ በአማራ ክልል ይገኛሉ።
እንደጥናቱ ከሆነ የልጅነት ጋብቻ ምጣኔ ሃብታዊ ተጽዕኖው ብቻ ቢታይ እንኳን የልጅነት ጋብቻ በማስቀረት 1.5 በመቶ ዓመታዊ የገቢ ጭማሪ ማግኘት ይቻላል።
በትምህርት ረገድ ከታየ ደግሞ የልጅነት ጋብቻውን በማስቀረት ልጆቹ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቢያጠናቅቁ በሃገር ኢኮኖሚ ውስጥ ከ10-20 በመቶ ሚና ይኖራቸዋል።
ሁለተኛ ደረጃን ካጠናቀቁ ደግሞ 15-25 በመቶ ከፍ ይላል። ይህ ደግሞ በየዓመቱ 646 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ የሚጨምር ነው ተብሏል።
የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች ከተዘጉ በኋላ የልጅነት ጋብቻ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ በግልጽ ታይቷል።
ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊት የልጅነት ጋብቻ በአማራ ክልል እየቀነሰ ነበር ያሉት አቶ ስማቸው "ይህ በጥናትም የተረጋገጠ ነው። የመቀነሱ ሁኔታም ፈጣን እንደነበረ ነው የሚያሳየው።
ግን ባለፈው በኮሮና ስርጭት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ህብረተሰቡ ትምህርት ሳይጀመር ሊቆይ ይችላል በሚል ትዳር ይያዙ የሚለው ነው እንጂ ጥሩ መሻሻል ነው የነበረው" ብለዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የልጅነት ጋብቻ ቁጥር ሲጨምር በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሲሠራ ነበረው ግብረሃይል ጎን ለጎንም ስለልጅነት ጋብቻ መረጃ ለህብረተሰቡ እንዲያደርስ መደረጉን ጠቁመዋል።
ከክልል እስከ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ግንዛቤ ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ውስጥ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችንም አሳታፊ ማድረግ ተችሏል።
ከኮሮና በተጨማሪ የማህበረሰቡ የግንዛቤ ደረጃ፥ ሥራ አጥነት እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለልጅነት ጋብቻ መኖር በተጨማሪነት በምክንያትነት ተነስተዋል።
ትምህርት ቤቶ ች በድጋሚ መከፈት መጀመራቸውን ተከትሎ ባለፈው ዓመት ትምህርት ላይ የነበሩ ተማሪዎች በሙሉ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ተማሪዎች ከተመለሱ በኋላ ደግሞ በልጅነት ጋብቻ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ እንደሚሰበሰብ አስታውቀዋል።
የልጅነት ጋብቻ በክልሉ የሚበዛባቸው አካባቢዎችን ለመለየት ጥናት እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ስማቸው የቅርብ ጊዜ ጥናት ባይኖርም ባላቸው መረጃ መሠረት " ሰሜንና ደቡብ ወሎ ምስራቅ ጎጃም እና ደቡብ ጎንደር አካባቢዎች ላይ ሰፊ እንደሆነ ነው የሚያሳየው" ብለዋል።
በምስራቅ ጎጃምም የልጅነት ጋብቻ ይበዛባቸው ተብለው ከተለዩት ወረዳዎች መካከል ደባይ ጥላት ወረዳ አንዷ ናት።
በወረዳው የልጅነት ጋብቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየየጨመረ ነው ያለው ያሉት የደባይ ጥላት ወረዳ የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነጻነት ዘለቀ ለቁጥሩ መጨመር አንደኛው ምክንያት ህብረተሰቡ ውስጥ ያለው "የአመለካከት ክፍተት" መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል በተማሪዎች እና መምህራን በኩል መረጃ ይገኝ እንደነበር ጠቁመው የትምህርት ቤቶች መዘጋት ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
የልጅነት ጋብቻ አንዳይፈጸም የግንዛቤ ማስጨበጫ በየጊዜው እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ቀደም ሲል ከነበረው አንጻር መቀነሱን አስታውቀዋል።
ከህብረተሰቡ የሚደርሳቸውን መረጃ መሠረት በማድረግ እንዲቋረጡ እና ወደ ሌላ ጊዜ እንዲዘዋወሩ የተደረጉ ጋብቻዎች አሉ ብለዋል።
በወረዳ በሚገኙ "ደጋማ ቀጠናዎች አካባቢ" የልጅነት ጋብቻ እንደሚበዛ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከ2012 እስከ 2017 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት የልጅነት ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት በሃገር ዓቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል።
እንደአማራ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ከሆነ በክልሉ በ2017 ዓ.ም የልጅነት ጋብቻን ለማስቀረት እየተሠራ ነው።
ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተገለጸ በኋላ በአማራ ክልል 500 በላይ ጋብቻ ተቋረጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 350ቱ ከተፈጸመ በኋላ ነው እንዲቋረጥ ተደረገው።












