ኤርትራ፡ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ እየተጣራ ያለው የኤርትራዊው አባት ረዥም እድሜ ጉዳይ

127 ዓመት እንደኖሩ የሚነገርላቸው ኤርትራዊ እድሜ ባለፀጋ፣ አቶ ነታባይ ትንሳኤው

የፎቶው ባለመብት, Zere Netanay

በኤርትራ አንድ ክፍለ ዘመን እና ከዚያም በላይ የሚኖሩ የዕድሜ ባለጸጎች እንዳሉ ሲነገር መስማት የተለመደ ነው።

በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አባት ታሪክ ግን ለየት ያለና ምናልባትም በዓለም ደረጃ ከፊት ሊቀመጥ የሚችል ሳይሆን አይቀርም።

በዕድሜያቸው ላይ እየተደረገ ያለው የማጣራት ስራ በሰነድ ከተረጋገጠ በዓለማችን ረዥሙን ዕድሜ የኖሩ የዕድሜ ባለጸጋ ሊሆኑ ይችላሉ።

የ 'አቦይ' ነታባይ ታሪክ

አቶ ነታባይ ትንሳኤው ከአባታቸው አቶ ትንሳኤው ታይብ እና እናታቸው ወይዘሮ ክብድ ዓይብ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በግንቦት 1/1894 ዓዘፋ በሚባል ትንሽ ቀዬ ተወልደው እንዳደጉና እንደኖሩ ቤተሰቦቻቸውና የመንደሯ ቤተክርስትያን ቄስ የነበሩት አባት ይመሰክራሉ።

ይህ ደግሞ ከልደታቸው እስከ ህልፈታቸው ከ127 ዓመታት በላይ በዚህች ዓለም እንደቆዩ ያሳያል።

ዓዘፋ በዓንሰባ ዞን ከአስመራ ወደ ከረን በሚወስድ መስመር ላይ የምትገኝ ትንሽ መንደር ናት።

በ2014 የአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ ወር ላይ በታተመው መንግሥታዊ ጋዜጣ 'ሐዳስ ኤርትራ'፤ እኚህ አባት በዓለም ረዥሙን ዕድሜ የቆዩ ሰው ሳይሆኑ እንደማይቀሩ የሚገልጽ ጽሑፍ አትሞ ነበር።

አቶ ነታባይ በወቅቱ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ 120ኛ የልደት በዓላቸውን እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።

ዓዘፋ በተባለችው ቀዬ ለሰባት ዓመታት ያገለገሉትና በ2014 በአቦይ ነታባይ 120ኛ የልደት እዩቤልዩ ዝግጅት ላይ የተሳተፉት የካቶሊክ ቤተክርስትያን ቄስ አባ መንታይ ናይር "በጥምቀታቸው መዝገብ ላይ ያለው ዓመተምህረት 1894 ነው የሚለው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በንጉስ ኃይለስላሴና በደርግ ስርዓት ዘመነ መንግሥታት በመኖሪያ ቤቶችና አብያተ ቤተክርስትያን ላይ በሚፈጸሙ የአየርና እንዲሁም ከባድ መሳሪያ ድብደባዎች ምክንያት ብዙ ሰነዶች መቃጠላቸው ይነገራል።

ቄስ መንታይ እንደሚሉትም የቤተክርስቲያኒቱ ሰነዶችና መረጃዎች ቶሮንኳ ከሚባል ቦታ ወደ ሽዕብ (ረብቶ) እንዲጓጓዝ ተደርጎ ከቆየ በኋላ ነው ወደ ዓዘፋ እንዲመለስ ተደርጓል። በአሁኑ ወቅትም እዛው እንደሚገኝ እኝህ ሃይማኖታዊ አባት ይናገራሉ።

"[መዝገቡ] ለኔ ዓዘፋ ላይ ነው የደረሰኝ" ሲሉም የዕድሜ ባለጸጋው መረጃ በሰነድ ላይ የሰፈረ መሆኑን ያረጋግጣሉ።

"ዓይናቸው ከመድከሙ በስተቀር ሙሉ ጤና ነበራቸው" ሲሉ ስለአቦይ ነታባይ የሚመሰክሩት አባ መንታይ፤ በመጨረሻ የዕድሜያቸው ጊዜያት ግን ምርኩዝ በመደገፍ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ይናገራሉ።

127 ዓመት እንደኖሩ የሚነገርላቸው ኤርትራዊ እድሜ ባለፀጋ፣ አቶ ነታባይ ትንሳኤው

የፎቶው ባለመብት, Zere Netanay

'ዕድያቸው 127 ብቻ አይለም'

አቶ ነታባይ ትንሳኤው ታይብ ነሐሴ 20/2021 ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። በዚህም መሰረት ዕድሜያቸው 127 ዓመት ከ4 ወር ከ20 ቀን መሆኑ ማስላት ይቻላል።

ከልጅ ልጆቻቸው አንዱ የሆነው ዘረዓ ተክለ ለቢቢሲ እንዳለው ምንም እንኳን ዕድሚያቸው 127 እንደሆነ መረጃ ቢኖርም አቶ ነታባይ ግን ከዛ በላይ እንደሆነ ነው የሚሞግቱት።

በ1894 እአአ መወለዳቸውን የሚገልጸውን የሰነድ ማስረጃ የልደታቸውን ቀን ሳይሆን የተጠመቁበትን ቀን እንደሚወክል አስረግጠው ይናገሩ ነበር።

አቶ ነታባይ የጥምቀት ስርዓት የተፈፀመላቸው ካደጉ በኋላ መፈጸሙን በሚገባ እንደሚያስታውሱትም ያስረዳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ዕድሚያቸው 127 ብቻ አይደለም። ከሚገለጸው በላይ ረዥም ዓመታት ኖረዋል። ይሁን እንጂ በውል ሊታወቅ አልተቻለም።

በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ እየተደረገው ማጣራት

የዕድሜ ባለጸጋው አቶ ነታባይ በዓለም ረዥሙን ዕድሜ በመኖር ክብረወሰን መያዝ እንደሚችሉ የሚናገሩት ቤተሰቦቻቸው፤ መረጃዎች ወደ ዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ(ጊነስ ወርልድ ሪከርድስ) መላካቸውን ለቢቢሲ አሳውቀዋል።

የዓለም ክብረወሰኖችን የሚመዘግበው ድርጅት የአቶ ነታባይ ዕድሜ ይመዝገብልን ጥያቄ መቀበሉን የሚናገረው የልጅ ልጃቸው አቶ ዘርአ "የማጣራቱን ስራ ካጠናቀቀ በኋላ ውጤቱን እንደሚያሰውቀን ገልጾልናል" ይላሉ።

ጊነስ በዓለም ረዥሙን ዕድሜ የኖሩትን ሰዎች የመመዝገብና የማሳወቅ ስራ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።

መዝገቡ እንደሚያመለክተው ረዥሙን ዕድሜ በመኖር የሚታወቁት ግለሰብ ፈረንሳዊት ጄን ሊዊስ ናቸው። በ1875 የተወለዱት ጄን በዚች ምስር ላይ 122 ዓመት ከ162 ቀናት በህይወት ቆይተዋል።

በኖሩበት የዕድሜ ዘመን 'ስፓኒሽ ፍሉ' [የስፔን ጉንፋን] በመባል የሚታወቀውን ገዳይ ወረርሺኝ እንዲሁም አንደኛውን የዓለም ጦርነትን ያዩት እኚህ የዕድሜ ባለጸጋ በዕድሜ ትልቋ የፊልም ተዋናይ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል።

100 ዓመት ሞልቷቸውም ብስክሌት መንዳት ያላቆሙት የዕድሜ ባለጸጋዋ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በነሐሴ 4/1997 ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

ጊነስ ሪከርድስ የአቶ ነታባይ ጉዳይ በመመርመር ማረጋገጥ የሚችል ከሆነ የፈረንሳዊቷ ጄን ክብረወሰን የሚሻሻል ይሆናል።

የረጅም ዕድሜ ምስጢር

አንዳንድ ሰዎች ከብዙዎች በተለየ ሁኔታ ረጅም ዕድሜ ሲቆዩ፤ 'ምስጢሩ ምን ይሆን ብሎ መጠየቅ?' አይቀርም። አብዛኞቹ ረጅም ዕድሜ የሚቆዩት ሰዎችም ሙሉ ጤንነት ኖሯቸው ነው የሚኖሩት። አካላዊ እንቅስቃሲያቸውም አጀብ ያስብላል።

አቶ ነታባይ የተወለዱባት ቀዬ በብዛት የብሌን ተወላጆች የሚኖሩባት ስትሆን ማሕበረሰቦቿም በእርሻና እንስሳ በማርባት ኑሯቸውን ይገፋሉ። ከብቶችና ፍየሎች በዋነኛነት ያረባሉ። አሸዋማ በሆነው ቀዬ ላይ በስፋት ማሽላና ኦቾሎኒ ያበቅላሉ።

እንደ ዘይቱን፣ ብርቱኳንና መንደሪን ያሉ ፍራፍሬ በዓንሰባ ወንዝ ዳርቻዎች ላይ ያበቅላሉ፤ የጎመን እና የተለያዩ የጎመን ዝርያዎች በስፋት ይተክላሉ።

አቶ ነታባይና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በስፋት የሚመገቡት ምግብ የማሽላ ገንፎ ሲሆን ወተት፣ ቅቤና ማርም ይዘወትራሉ።

አቶ ዘርአ "የኑሮ ዘይቤና አመጋገብ" ለቅድመ አያታቸው ለረዥም ዕድሜ መኖር ምክንያት እንደሆናቸው በመግለጽ፤ ረጅም ዕድሜ ለመቆየት ህይወትን በእቅድ መምራትና ተፈጥሯዊ የሆኑ ምግቦችን ማዘውተር ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ያስረዳሉ።

አቶ ነታባይ እ.አ.አ በ2014 ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ላይ ማር የተጨመረበት ቅቤ ይጠጡ እንደነበር ተናግረዋል። በቤታቸው ንብ ያንቡ ስለነበር ማር ለማግኘት አይቸገሩም ነበር። ለገንፎ የሚጠቀሙት ዱቄትም በእጅ የሚፈጭ ነበር።

የዕድሜ ባለጸጎች የሚታወቁበት ሌላ ባህሪ በህይወት ዙሪያ ያለቸው አመለካከትና የአኗኗር ዘይቤ ነው። "አቦይ ነታባይ የተረጋጉና የማይጨነቁ ሰው ነበሩ" ይላሉ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ቄስ አባ መንታይ።

"ቅድመ አያቴ ለጋስ፣ ሰው ወዳድ፣ ለሰው ተቆርቋሪን እና ታታሪ ሰራተኛ ነበረ" የሚሉት የልጅ ልጃቸው አቶ ዘርአ በበኩላቸው ረዥም ዕድሜ የመኖራቸው ምስጢር ትዕግስት፣ ፍቅርና ሰላም ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ።

127 ዓመት እንደኖሩ የሚነገርላቸው ኤርትራዊ እድሜ ባለፀጋ፣ አቶ ነታባይ ትንሳኤው እና ባለቤታቸው

የፎቶው ባለመብት, Zere Netanay

ትዳርና ቤተሰብ - ድርብርብ ክብረወሰኖች. . .?

የአቶ ነታባይ ታሪክ በሙሉ ከተፈተሸ ረዥም ዕድሜ በመኖራቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ክብረወሰኖችም ሊያስመዘግቡ ይችላሉ።

በወንዶች ዘርፍ ብቻ ከታየ በአሁኑ ጊዜ በክብረወሰን ደረጃ የተመዘገበው 116 ዓመታት ከ54 ቀናት በህይወት የቆዩት ጃፓናዊ ጂሮሞን ከሙራ የሚመለከት ነው።

የዕድሜ ጉዳያቸው ተጣርቶ ሊረጋገጥ ከቻለ በወንዶችም በሴቶችም የተመዘገቡትን ክብረወሰኖችን በስማቸው መቀየሩ አይቀሬ ነው።

የትዳራቸው ጉዳይም ሌላ መመዝገብ የሚችል ልዩነታቸው ነው። በ2014 ከሓደስ ኤርትራ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ላይ የ40 ዓመት ጎልማሳ ሆነው በዚያን ጊዜ የ14 ዓመት ልጃገረድ ከነበሩት ባለቤታቸው ወይዘሮ ለተሩፋኤል ጋር በትዳር ተሳስረው ኖረዋል። ትዳር የመሰረቱትም እ.አ.አ በ1934 ነበር።

በትዳራቸው ለ85 ዓመታት የጸኑ በመሆናቸው ረዥሙን ጊዜ ከትዳር አጋር ጋር አብሮ በመኖርም ሊቀድማቸው የሚችል አይኖርም። ምክንያቱም እስከዛሬ የተመዘገበው ክብረወሰን 80 ዓመታት ነውና። ኢኳዶራውያኑ ጥንዶች ክብረወሰኑን መያዛቸው ይገለጻል።

የ14 ዓመት ልጃገረድ ሆነው ከአቶ ነታባይ ጋር ትዳር የመሰረቱት ወይዘሮ ለተሩፋኤል በ2019 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ባለቤታቸው ተከትሏቸው አልፈዋል።

ከጣልያን ወረራ ጀምሮ ያሉትን ሁንም መንግሥታት ማየት የቻሉት ጥንዶቹ በአጠቃላይ 10 ልጆች መውለድ ችለዋል። እስከ 2014 [እ.አ.አ] በነበረው ጊዜም ልጆቻቸውን ጨምሮ እስከ አምስተኛ ትውልድ ለማየት በቅተዋል።

በአጠቃላይም የቤተሰቦቻቸው ቁጥር 134 ሊደርስ መቻሉን መንግሥታዊ ጋዜጣ ሓዳስ ኤርትራ ጋዜጣ ላይ የሰፈረው ዘገባ ያመለክታል።

የአቶ ነታባይ የቤተሰብ ብዛት ከ2014 ወዲህ ባሉት 7 ዓመታት ጨምሮ ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም።