በምዕራብ ሸዋ ለ75 ዓመታት በትዳር የኖሩት ጥንዶች በሰዓታት ልዩነት ሕይወታቸው አለፈ

አቶ ጊሎ ቶሌራ የመቶ ዓመት፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ ጥሩ በንቲ ደግሞ 90 ዓመት አዛውንት ነበሩ

የፎቶው ባለመብት, Illu Gelan wereda communucation

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ለ75 ዓመታት በትዳር የኖሩት ባልና ሚስት በሰዓታት ልዩነት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ሃዘን እና ግርምትን ፈጥሯል።

ምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ገላን ወረዳ ሜታ ኪዳነ ምህረት ቀበሌ፣ ይኖሩ የነበሩት ጥንዶቹ አንድ ሙሉ ቀን ባልሞላ ጊዜ በ20 ሰዓታት ልዩነት ውስጥ ህይወታቸው ማለፉን ቤተሰቦቻቸውና የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

"እኔ ሞቼ አንተ ደግሞ ከአንድ ወር በኋላ ትከተለኛለህ/ትከተይኛለሽ. . ." ይባባሉ ነበር ሲሊ የጥንዶቹ ልጅ አቶ አበራ ጊሎ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባል አቶ ጊሎ ቶሌራ የመቶ ዓመት፤ ባለቤታቸው ወ/ሮ ጥሩ በንቲ ደግሞ የ90 ዓመት አዛውንት ነበሩ። ከ1939 ዓ.ም ጀምሮ ለ75 ዓመታት በትዳር አብረው እንደኖሩ ልጃቸው አቶ አበራ ጊሎ ይናገራሉ።

አቶ ጊሎ ቶሌራ እና ወ/ሮ ጥሩ በንቲ ከ70 ዓመት በላይ ባስቆጠረው የትዳር ዘመናቸው ስምንት ልጆች ማፍራታቸውን ሰምተናል።

በጥንዶቹ መካከል ጥልቅ ፍቅር እና መከባበር እንደነበረ ጎረቤቶቻቸው ይመሰክራሉ።

ልጃቸው አቶ አበራ አባት እና እናቱ ከጳጉሜ 05/2013 ዓ.ም ጀምሮ መታመማቸውን ይናገራሉ።

አቶ አበራ አክለውም "ሕመማቸው የጠና አልነበረም፤ እዚህ ቦታ ያመናል ብለው የገለፁት ነገር የለም። ምግብና መጠጥ ብቻ ከልክሏቸው ነበር። ሁለቱም በተመሳሳይ ጊዜ ነበር የታመሙት" ይላሉ።

"ቀላል ሕመም ስለሆነ ይድናሉ ብለን ጠብቀን ነበር" ያሉት አቶ አበራ፤ "በኋላ ግን እናቴ 'የእኔ አክትሟል' ስትል ነበር፤ ይድናሉ ብለን እየጠበቅን ሳለ፣ የጥሪያቸው ጊዜ ስለሆነ አርፈዋል" ብለዋል።

አቶ ጊሎ ቶሌራ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ጥሩ በንቲ በሃሳብና በአካል መራራቅ የማይሆንላቸው ጥንዶች እንደነበሩ ጎረቤቶቻቸው እና ልጆቻቸው ይመሰክራሉ።

"አንዳቸው ከሌላኛው መለየት አይፈልጉም። ለአንድ ጉዳይ ወደ አንድ ስፍራ ሲሄዱ፣ ወይንም ሐኪም ቤት ሲሄዱ አንዱ ከሌላው መለየት አይፈልግም" ብለዋል ልጃቸው አቶ አበራ።

"እኔ ሞቼ በአንድ ወር ውስጥ ትከተለኛለህ፤ ብቻዬን አልሆንም፤ ለእኔ አዝነህ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ትደርስብኛለህ" ሲባባሉ ኖረዋል ሲሉም ያክላሉ።

እነዚህ ጥንዶች ጳጉሜ 05/2013 ታመው አቶ ጊሎ ረቡዕ መስከረም 05/2014 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡05 ደቂቃ ላይ አርፈዋል።

ደክመው ራሳቸውን ስተው የነበሩት ባለቤታቸው ወ/ሮ ጥሩ ደግሞ ከአቶ ጊሎ 20 ሰዓታት ዘግይተው ሐሙስ ዕለት ከሰዓት 12፡00 ሰዓት ላይ ከዚህ ዓመት በሞት ተለይተዋል።

በኢሉ ገላን ወረዳ ሜታ ኪዳነ ምህረት ውስጥ ነዋሪ ሆኑት የ65 ዓመት አዛውንት አቶ በቀለ ጭምዴሳ የእነዚህ ጥንዶች ሞት የአካባቢውን ኅብረተሰብ እጅግ በጣም እንዳሳዘነ ይናገራሉ።

አቶ ጊሎ ቶሌራ የመቶ ዓመት፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ ጥሩ በንቲ ደግሞ 90 ዓመት አዛውንት ነበሩ

የፎቶው ባለመብት, Illu Gelan wereda communucation

"ባልና ሚስት በዚህ መልክ ህይወታቸው ማለፉ ለእኛም አዲስ ነገር ነው። አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ እርስ በእርሳቸው ስለሚዋደዱ እና ስለሚከባበሩ እግዚአብሔር በአንድ ላይ ወሰዳቸው" በማለት ለቢቢሲ ስሜታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ ረቡማ ሞሲሳ ደግሞ "ይህ ነገር ለእኛ አዲስ ነው በእድሜዬ እንደዚህ ዓይነት ነገር አይቼም ሰምቼም አላውቅም። ኅብረተሰቡንም በጣም አስገርሞታል" በማለት ይህ ክስተት በኅብረተሰቡ ውስጥ አግራሞትን መፍጠሩን ያብራራሉ።

አቶ አበራ በበኩላቸው "እንደ ቤተሰብ አንዱ ከሌላው እንደማይቀር ብናውቅም እንደዚህ ግን ይሆናል ብለን አልጠበቅንም ነበር። ይህም ድንጋጤ ፈጥሮብናል" ብለዋል።

"ታላቅን ማክበር፣ ሥነ-ምግባርን እና መደማመጥን" ከቤተሰቦቻቸው እንደተማሩ በመዘርዘር "ስምምነት ያላቸው፣ የሚከባበሩ እና የሚሰማሙ. . ." ጥንዶች እንደነበሩ ይገልጻሉ።

"ከተገናኙበት ቀን ጀምሮ ተጋጭተው ተራርቀው አያውቁም፤ ቅሬታ ቢኖራቸው እንኳ ሰው በመካከላቸው ገብቶ አያውቅም" በማለት የአባት እና የእናታቸውን ትዳር ይገልጹታል።

የአቶ ጊሎ ቶሌራ እና ወ/ሮ ጥሩ በንቲ የቀብር ሥነ ሥርዓት አርብ መስከረም 07/2014 ዓ.ም በአንድ ላይ ተፈጽሟል።