ትዳር ፡ የጃፓን ወንዶች በሚስቶቻቸው ላይ ለምን ሰላይ ይቀጥራሉ?

ጥንዶች በጃፓን የባሕር ዳርቻ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንደው ነገር ለማድመቅ ነው እንጂ ነገሩስ ወንዶች ብቻ አይደለም ሰላይ የሚቀጥሩት። በጃፓን ሴቶችም ባሎቻቸው ላይ ሰላይ ይልካሉ።

ወጣቶች ፍቅረኞቻቸውን ያሰልላሉ።

ቀላል ብር እንዳይመስልዎ ታዲያ የሚከፈለው። የአንድ ሰላይ ዋጋ እስከ 400 ሺህ የን [የጃፓን ብር] ሊደርስ ይችላል።

እርግጥ ነው ይህ ብር እንደ ዜሮዎች ብዛት አስደንጋጭ አይደለም። ይህን ጽሑፍ አንብበው እስኪጨርሱ የምንዛሬ ዋጋ እንዳይጨምር እንጂ በአገር ቤት ይህ ገንዘብ ስንት እንደሚሆን ቆየት ብለን እንነግርዎታለን።

በቅድሚያ ይቺን ታሪክ ያንብቧት።

ሰላዩ ፍቅር ያዘው

ነገሩ 2010 (እንደ አውሮፓዊያኑ) የሆነ ታሪክ ነው።

ሰላዩ ፍቅር ያዘው። የሰው ሚስት ለመሰለል ተቀጥሮ በዚያው ፍቅር ያዘው ነው የምንልዎት። ከዚያ ሴቲቱ የገዛ ባሏ የቀጠረው ሰላይ እንደሆነ ደረሰችበትና ተጣላችው። ከዚያ በቃ አንተንም ባሌንም አልፈልጋችሁም አለች። ከዚያ በሲባጎ አንቆ ገደላት።

ይህ ታሪክ ትንሽ ግነት ያለበት የቦሊውድ ፊልም ከመሰላችሁ ይቅርታ። ነገር ግን እውነት ነው። እንዲያውም ሰላዩ ወንጀለኛ በ15 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጥቷል።

ታሪኩ ትንሽ እንዲብራራ ፈለጋችሁ? እነሆ፡-

ታኬሺ ኩዋምባራ ይባላል ሰላዩ። ሰላይ ታኬሺ ኢሶሃታ የምትባል ቆንጆ እመቤት እንዲሰልል በኢሶሃታ ባል ይቀጠራል።

ከዚያም ኢሶሃታን ተከታትሎ ተከታትሎ አንድ ቀን ሱፐርማርኬት ውስጥ አማለላት።

ሲተዋወቃት ብቻውን የሚኖር የኮምፒውተር ባለሙያ ነኝ ብሎ ነበር። ደግሞ ይመስላል።

ቀጭን ፊቱ፣ በሰልካካ አፍንጫው ላይ መነጽሩ ሲታይ ፈረንጆች (ነርዲ) የሚሏቸውን እነዚያ የኮምፒውተር አባዜ የተጠናወታቸውን ወጣቶች ይመስላል።

ብቸኛ ነኝ ሲላት አመነችው። ሚስትና ልጆች አሉት እኮ፤ ውሸቱን ነው ላጤ ነኝ የሚላት።

"አንቺስ?" አላት። "እኔማ ባለትዳር ነኝ" አለችው። የደነገጠ መሰለ። "ውይ! ምን አስቸኮለሽ ግን? ምነው ሳታገቢ አውቄሽ ቢሆን?" አላት። አውቆ እኮ ነው። ውሸቱን ነው። ሲያማልላት…

በሰላዩ ታኬሺ ማለለች። ባለትዳርነቷ ከሰላዩ ታኬሺ ጋር የደብብቆሽ ፍቅር ከመጀመር አላገዳትም።

እራት በሉ፣ እያመሸች ከእሱ ጋ መሳቅ መጫት ጀመረች። ደስ አላት። ተሳሳተች። ተሳሳቱ።

የሚገርመው ሰላዩ ታኬሺ ሥራውን ረስቶ እሱ ራሱ ፍቅር ከእሷ ጋር አይዘውም መሰላችሁ!

የሰላዩ ሁናቴ ያልጣመው ባል በሰላይ ላይ ሰላይ መቅጠር። የሆነ ቀን ከሆቴል ሲወጡ አዲሱ ሰላይ በፎቶ አነጣጥሮ ቀለባቸው። ጉድ የፈላው ከዚህ በኋላ ነበር።

ባልየው የሚፈልገውን መረጃ አገኘ።

ባልየው ድሮም ሰላይ የቀጠረው ሚስቱን ስለሚወዳት ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። መፋታት ፈልጎ ነበር።

በጃፓን መፋታት ቀላል አይደለም። መረጃ ያስፈልጋል። የፎቶ መረጃ። የቪዲዮ መረጃ። ሚስት መማገጧን የሚያሳይ ፍርድ ቤትን የሚያሳምን ሁነኛ መረጃ።

በመጨረሻ ፍቺው ተሳካና ተፋቱ። እድሜ ለአዲሱ ሰላይ።

ነገር ግን ሚስት ከባሏ ጋር ብትፋታም ከመጀመርያው ሰላይ ጋር ፍቅር ላይ ነበረች። የታኬሺን ሰላይነት ግን ዘግይታ ደረሰችበት። በጣም አናደዳት። ካንተ ጋር አልኖርም አለችው። ቢል፣ ቢሰራት፣ ተንበርክኮ ቢለምን…ወይ ፍንክች ያባ ቢላ ልጅ።

ሰላዩ በዚህን ጊዜ አመረረ። ምክንያቱም እሱ ራሱ ትዳር አለው፤ ልጆች አሉት። ሁሉን ትቶ ነበር ፍቅር የያዘው። እሷ እሄዳለሁ ስትል "አንቺ ከሄድሽ የእኔ መኖር ታዲያ ምን ትርጉም አለው?" በሚል በሲባጎ አንቆ ገደላት።

ጃፓናዊያን ደነገጡ። በዚህ የተነሳ የትዳር ሰላዮች ቢዝነስ ቀዘቀዘ። ሰላይ ታኬሺም ለወንጀሉ በ15 ዓመት ፍርድ ዘብጥያ ወረደ።

ስፋኒ ስኮት

የፎቶው ባለመብት, Julius Honnor

የምስሉ መግለጫ, ስቴፋኒ ስኮት በዚህ የስለላ ተግባር ላይ ሰፊ ጥናት አድርጋ መጽሐፍ ጽፋለች

"በአዲስ መልክ ባልና ሚስት መሰለል ጀምረናል"

የኢሶሃታ ሞትን ተከትሎ በጃፓን የትዳር ሰላዮች ጉዳይ መነጋገርያ ሆነ። ለጊዜው የተዳፈነ መሰለ። ለጊዜው ባለትዳሮች በሰላዮች እምነት ያጡ መሰሉ።

ከዓመታት በኋላ ግን የስለላ ቢዝነስ ዛር ቆመ። ጃፓኖች የትዳር ሰላዮችን ዋካሬሳሴያ ብለው ነው የሚጠሯቸው። ቢዝነሱም ዋካሬሳሴያ ነው የሚባለው።

ቢዝነስ ብቻ አይደለም ታዲያ። ኢንዱስትሪ ሆኗል ማለት ይቻላል፤ ለጃፓን።

ለምሳሌ 270 የሚሆኑ ኩባንያዎች ሕጋዊ ፍቃድ አውጥተው ትዳር ይሰልላሉ። ይፋ ድረ ገጽ አላቸው። ሚሊዮኖችን ይከሰክሳሉ፤ ለማስታወቂያ። ይህ በጣም ብዙ ቁጥር አይደለም ታዲያ?

በምዕራቡ ዓለም የግል ወንጀል ምርመራ ቢሮዎች የተለመዱ ናቸው። በጃፓን ደግሞ ዋካሬሳሴያ።

"የትዳር ሰላዮች ዋጋ የሚቀመስ አይደለም" ይላል ሞሺዙኪ። ሞሺዙኪ ቀድሞ ሙዚቀኛ ነበር። አሁን የግል መርማሪ ሆኗል። የትዳር ስለላ ቢሮም አለው።

ለአንድ ስለላ እስከ 400 ሺህ የን ያስከፍላል። ይሄ ወደ ዶላር ሲመነዘር 3 ሺህ ዶላር ይጠጋል። ወደእኛ ብር ስንመታው ወደ አንድ መቶ ሺህ ብር አካባቢ ነው።

ነገር ግን ይሄ ትንሹ ክፍያ ነው። ሚስቱ ወይም ባሏ እንዲሰለልለት የፈለገ በጣም ብዙ መረጃ ከሰጠ/ከሰጠች ነው ይህ ዋጋ የሚሰጠው። በታላቅ ቅናሽ። የዘመድ ዋጋ ነው ይሄ።

ለምሳሌ ሚስቱ የት እንደምትውል፣ ምን እንደምትወድ፣ የጓደኞቿ አድራሻና ማንነት፣ የፌስቡክ ማለፊያ የምስጢር ቃል እና ደካማ ጎኗ ወዘተ. . .

ይሄ ዋጋ አንዳንድ ጊዜ እስከ 20 ሚሊዮን ከፍ ሊል ይችላል። መቼ ከተባለ የሚሰለለው ባል/ሚስት/ፍቅረኛ ለምሳሌ እውቅ፣ ስመ ጥር፣ ዝነኛ ሰው ከሆነ/ከሆነች፣ ፖለቲከኛ ከሆነ/ከሆነች ዋጋው ይወደዳል።

የሚጠየቀው ክፍያ ከመቶ ሺህ ዶላር በላይ ይዘላል። በጣም ብዙ ብር ነው ይሄ። አንዱ ምክንያት በጣም ብዙ ሰላዮችና በጣም ውስብስብ ቴክኖሎጂን ማሰማራት ስለሚያስፈልግ ነው።

ጥንዶች በጃፓን የባሕር ዳርቻ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በለንደን መቀመጫዋን ያደረገችው ስቴፋኒ ስኮት የልቦለድ ሥራዎቿ ብዙዎቹ በዚህ በጃፓኖቹ ስለላ ላይ ያተኮሩ ናቸው። "ዋት ኢዝ ሌፍት ኦፍ ሚ ኢዝ ዩርስ" የሚል መጽሐፍ ጽፋለች። ታሪኩ በአመዛኙ በሰላዩ ታኬሺ የተገደለችው በቆንጅየዋ በኢሶሃታ ላይ ያተኮረ ነው።

ደራሲ ስኮት ለቢቢሲ እንደተናገረችው ከሆነ የትዳር ሰላይ መቅጠር ከትዳር አጋር ጋር የሚኖረውን የተንዛዛ ፍጥጫና የተራዘመ ፍቺ ያሳጥራል።

አንደኛ ሰላይ የተቀጠረባት ሚስት ሰላዩ ተሳክቶለት ፍቅር ካስጀመራት ፍቺ ስትጠየቅ ደስ ብሏት ትፈጽማለች። አለበለዚያ ግን ፍቺው ቀላል አይሆንም።

ፍቺ ሲራዘም ደግሞ ባልና ሚስት ጊዜና ጉልበታቸው ይሟጠጣል። በስሜት ይጎዳሉ። ሕይወት ይቃወሳል። አንዳንድ ጊዜ ሰላዮች የሚቀጠሩት ፍቺን ለማፋጠን ብቻ ሳይሆን ሕይትን ለማቅለል ነው።

ነገር ግን ሰላዮች ሁልጊዜ ፍቺን ለማሳለጥ አይደለም የሚቀጠሩት።

አንዲት ሚስት ባሏ በጣም እንዲጎዳ ስትፈልግ ሆን ብላ ሰላይ ቀጥራ ፍቅር እንዲይዘው ታደርግና ከዚያ ሰላይዋ ማንነቷን ሳትገልጽ ድንገት ግንኙነቷን በማቋረጥ ከፍተኛ የስሜት ጉዳት እንድታደርስበት ይከፈላታል።

በተመሳሳይ 'ሚስቴ አቃጥላ ልትደፋኝ ነው' ያለ ባል ጠንበለል የጃፓን ሰላይ ይቀጥራል።

ሰላዩ በዚህም በዚያም ብሎ የሰውየውን ሚስት ያጠምዳል። ፍቅር ያስጀምራታል። ከዚያ በድንገት ስሜቷ እንዲጎዳ አድርጎ ፍቅሩን ይቆርጠዋል። ለዚህ ተግባሩ ከፍ ያለ ገንዘብ ይከፈለዋል፤ ከቀጣሪ ባል።

"ይህ ቀላል ተግባር አይደለም፤ አንድ የስለላ ተግባር ከወራት እስከ ዓመታት ሊወስድ ይችላል" ይላል ሞቺዙኪ።

ሰላዮች በብዛት በሕግ የሰለጠኑ ናቸው። ሥራቸውን ሲሰሩ የጃፓንን ሕግ መጣስ አይኖርባቸውም። ለምሳሌ ዛቻ መፈፀም፣ ማስፈራራት፣ አካላዊ ጥቃት አይፈቀዱም።

እንደዚህ የሚያደርጉ የትዳር ሰላዮች ድርጅታቸው ከሥራ ሊያባርራቸው ይችላል።

ችግሩ ከሥራ ሲባረሩ በድብቅ ፍቃድ ሳያወጡ የሚሰማሩ ሕገወጥ ሰላዮች ሆነው መቀጠላቸው ነው፤ አሁን አሁን አሳሳቢ እየሆነ የመጣው።

እነዚህ ሕገወጥ ሰላዮች ቀይ መስመር በማለፍ ይታወቃሉ። ለምሳሌ ባለትዳር ሴትን ካማገጡ በኋላ የወሲብ ድርጊትን በድብቅ ቪዲዮ በመቅረጽ ለባል አሳልፎ መስጠት።

በጃፓን ይህ የትዳር አጋርን የማሰለል ቢዝነስ ሞቅ ያለ ገበያ አለው ማለት ማኅበረሰቡ በድርጊቱ ይኩራራል ማለት ግን አይደለም።

በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ ሆኖ መገኘት በጃፓን ባህል አሳፋሪ ነው። ሰዎች በፍጹም ከድርጊቱ ጋር ራሳቸውን ማቆራኘት አይሹም። ሆኖም አገልግሎቱን ይወዱታል።

በጃፓን የቲቪና የሬዲዮ ፕሮዲዩሰር ኒሺያማ ለቢቢሲ ስትናገር "በጃፓን ለሁሉም ነገር ገበያ አለ" ትላለች።

ለምሳሌ የውሸት ሙሉ ቤተሰብ አባል መከራየት የፈለገ ይህንኑ ማድረግ ይችላል። ለምሳሌ ልጁን ከሴት ፍቅረኛው ፈልቅቆ ለመውሰድ የሚፈልግ ወንድ ለዚህ ተግባር ሰላይ ሊያሰማራ ይችላል።

የትዳር ሰላይ ኩባንያዎች ሰዎችን በማለያየት ብቻ አይደለም የሚሰማሩት፤ አንዳንድ የተሰበረ ትዳርን በመጠገንም ይታወቃሉ።

የተሰበረ፣ የወለቀ፣ ወለምታ የገጠመው ትዳር ሲጠግኑ ታዲያ በነጻ አይደለም። ሞቅ ያለ ሒሳብ በማስከፈል እንጂ።