ምን ያህል እንደምንኖር የሚያሳዩ ዘጠኝ እውነታዎች

በ195 ሃገራት ሴቶች ከወንዶች በተሻለ ብዙ ዓመታት ይኖራሉ። በሩሲያ ደግሞ ለተጨማሪ 11 ዓመታት ይኖራሉ። ኢትዮጵያውያን በ1990 ከነበራቸው የእድሜ ጣራ በተሻለ 19 ተጨማሪ ዓመታት እየኖሩ ነው። ከፍተኛ የእድሜ ጣራ ያስመዘገቡ ያደጉት ሃገራት ደግሞ ከዝቅተኞቹ ጋር ሲነጻጸር 34 ተጨማሪ ዓመታት ይኖራሉ።
ይህ መረጃ የተገኘው የዓለም አቀፉን የበሽታ ጫና ጥናት ከሚጠቀመው የቢቢሲ የእድሜ ጣራ መለኪያ ነው። እስቲ ሙሉ መረጃውን እናጋራዎ።
1. ብዙ እየኖርን ነው
ከ1990 በሁዋላ የዓለም- አቀፉ የእድሜ ጣራ ከ7 ዓመት በላይ ከፍ ብሏል። የዓለም ህዝብ ብዙ ዓመታት እየኖረ ያለበት ምክነያት፤ ባደጉት ሃጋራት በልብ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ስለቀነሰ እና በማደግ ላእ ባሉ ሃገራት ደግሞ የህጻናት ሞት በመቀነሱ ነው። የተሻለ የጤና አገልግሎት፣ ንጽህና እና የተራቀቁ የህክምና ግኝቶች ሳይረሱ ማለት ነው።
ጤናማ የእድሜ ጣራ- በጥሩ ጤና የምንኖረው እድሜም በ6.3 ዓመታት ጨምሯል።

2. ምሥራቅ አውሮፓውያን ብዙ እየኖሩ ነው
ምንም እንኳ ጃፓን እና ሲነጋፑር የተወለዱ ሰዎች 84 ዓመታት እንደሚኖሩ ቢገመትም በአህጉር ደረጃ ግን ከፍተኛ የእድሜ ጣራ ካስመዘገቡት 20 ሃገራት መካከል 14ቱ በምሥራቅ አውሮፓ ይገኛሉ።
እንግሊዝ በአማካይ 81 ዓመታት በማስመዝገብ 20 ሃገራትን ተቀላቅላለች።

3. የአፍሪካ ሃገራት ወደ መጨረሻ ናቸው
ከሁለት ሃገራት በስተቀር የመጨረሻዎቹ ቦታዎች በአፍሪካ ሃገራት የተያዙ ናቸው።
በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው በማዕከላዊ አፍሪካ እና በሌሴቶ በ2016 የተወለዱ ህጻናት ከፍተኛው የእድሜ ጣራቸው 50 ዓመታት ብቻ ሲሆን፤ በጃፓን ከሚወለዱት ህጻናት ጋር ሲነጻጸር በ 34 ዓመታት ያነሰ ነው።
በሌላ በኩል ጦርነት፣ ድርቅ እና ህግ አልባነት የሚያሰቃያት አፍጋኒስታን በ58 ዓመታት ብቸኛዋ እሲያዊ ሃገር በመሆን የመጨረሻውን ቦታ ይዛለች።

4. ሴቶች ከወንዶች በተሻል ብዙ እየኖሩ ነው
ከ198 ሃገራት በ195ቱ ሴቶች ከወንዶች በተሻለ በአማካይ ስድስት ተጨማሪ ዓመታት ይኖራሉ። በአንዳንድ ሃገራት እንዲያውም ልዩነቱ ወደ 11 ይሰፋል።
በምሥራቅ አውሮፓ እና ሩሲያ በእድሜ ጣሪያ ዙሪያ ከፍተኛ የጾታ ልዩነት ሲኖር፤ የአልኮል ሱሰኝነት እና አስቸጋሪ የሥራ ሁኔታ ወንዶች ቶሎ እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል ይላል ጥናቱ።
ወንዶች ከሴቶች በተሻል ብዙ ዓመታት ሚኖረሩባቸው ሦስት ሃገራት የኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ኩዌት እና ሞሪታንያ ናቸው።

5. ኢትዮጵያ ውስጥ የእድሜ ጣራ በ19 ዓመታት ጨምሯል
96 በመቶ በሚሆኑ ሃገራት ከ1990 በኋላ የእድሜ ጣራ ተሻሽሏል።
ከፍተኛ ለውጥ ካስመዘገቡት አስሩ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት ናቸው። በ1990 የኢትዮጵያ የእድሜ ጣራ 47 ብቻ የነበረ ሲሆን፤ ከ2016 በሁዋላ የተወለዱ ህጻናት ግን 19 ተጨማሪ ዓመታት እንደሚኖሩ ታውቋል። ይህ የሆነው በዋነኛነት የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች እና እንደ ኮሌራ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሳቸው ነው።

6. በስምንት ሃገራት ግን የእድሜ ጣራ ቀንሷል
ምንም እንኳን ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት ከፍተኛ የእድሜ ጣራ ቢያስመዘግቡም፤ ከስምንቱ አራቱ ሃገራት የእድሜ ጣራቸው ከ1990 በኋላ አሽቆልቁሏል።
ከፍተኛው መቀነስ የታየው በሌሴቶ ሲሆን፤ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምት ከሆነ በዚች ሃገር ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ በኤች አይቪ ኤድስ የተጠቃ ነው።

7. ድንበር ተሻጋሪ ልዩነቶች
የእድሜ ጣራ በሚገርም ሁኔታ በጎረቤት ሃገራት እንኳን የ20 ዓመት ልዩነት ያሳያል።
ለምሳሌ በጎረቤታሞቹ ቻይና እና አፍጋኒስታን መካከል የ18 ዓመታት ልዩነት አለ። አፍሪካ ውስጥ ደግሞ በሽብር እና በጦርነት የምትታወቀው ማሊ ከፍተኛው የእድሜ ጣራዋ 62 ሲሆን፤ ጎረቤቷ አልጄሪያ ግን 77 ዓመት አማካይ እድሜ አስመዝግባለች።

8. ጦርነት ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው
በ2010 የሶሪያ በአማካይ የእድሜ ጣራ ከዓለም ስድሳ አምስተኛ ላይ ተቀምጣ ነበር። ለዓመታት የቆየው ጦርነት ግን በ2016 ሃገሪቱ ወደ መቶ አርባ ሁለተኛ እንድታሽቆለቁል አድርጓታል።
በ1994 በተፈጸመው የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወቅት የተወለዱ ህጻናት ደግሞ አማካይ የእድሜ ጣራቸው 11 ዓመት ብቻ ነበር።

9. ረሃብ እና የተፈጥሮ አደጋዎችም ትልቅ ቦታ ይይዛሉ
ሰሜን ኮሪያ በ 1994 እና 1998 ባጋጠማት ከባድ ረሃብ ምክንያት አማካይ የእድሜ ጣራዋ እስከ 2000 ዓ/ም ድረስ አሽቆልቁሎ ነበር።
በ2010 በሄይቲ የ200 ሺህ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የመሬት መንቀጥቀጥ ሲደርስ የሃገሪቱ የእድሜ ጣራ የቀነሰ ቢሆንም በቀጣዩ ዓመት ግን ወደ ቦታው ተመልሷል።














