በሰባት ዓመቷ ተሰርቃ በ16 ዓመቷ ከአጋቾቿ ያመለጠችው ታዳጊ

ሙምባይ ከሚገኝ ትምህርት ቤቷ ደጃፍ ነበር የተሰረቀችው።

የፎቶው ባለመብት, BBC AND MUMBAI POLICE

የምስሉ መግለጫ, ሙምባይ ከሚገኝ ትምህርት ቤቷ ደጃፍ ነበር የተሰረቀችው።

ፑጃ ጋውድ የጠፋችው የሰባት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር።

ከሕንዷ ሙምባይ ከሚገኝ ትምህርት ቤቷ ደጃፍ ነበር የተሰረቀችው።

ጥንዶች ‘አይስክሬም እንስጥሽ’ ብለው አታለው ሰረቋት።

በ2013 የጠፋችው ፑጃ በአስደናቂ ሁኔታ ከጠላፊዎቿ አምልጣ በ16 ዓመቷ ዳግመኛ ከቤተሰቧ ተቀላቅላላች።

እናቷ ፖናም ጋውድ ልጃቸውን ሲያዩ በደስታ የሚያደርጉት እንደጠፋቸው ያስታውሳሉ።

“ልጄን አላገኛትም ብዬ ተስፋ ቆርጬ ሳለ አማልክቶች በደግነታቸው ልጄን መለሱልኝ” ይላሉ።

ታዳጊዋ የተጠለፈችው ሀሪ ዳሶውዛ በተባለ ግለሰብና በባለቤቱ ሶኒ ዳሶውዛ እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።

ፑጃ ከመጥፋቷ በፊት ከቤተሰቦቿና ከሁለት ወንድሞቿ ጋር በተጨናነቀ የሕንድ መንደር ትኖር ነበር።

ከታላቅ ወንድሟ ጋር ወደ ትምህርት ቤት በሄደችበት ቀን ነው የተሰረቀችው።

የዚያን ቀን ከወንድሟ ጋር ይጣሉና ወንድሟ ጥሏት ክፍል ይገባል።

ከዚያም ጥንዶቹ ሰረቋት።

ጥንዶቹ ፑጃን መጀመሪያ ጎዋ ወደተባለ ግዛት ከዚያም ወደ ካርናታካ ግዛት ነበር የወሰዷት።

ሰዎች እንዲያስጥሏት ብታለቅስ ጥንዶቹ እንደሚደበድቧት ያስፈራሯት ነበር።

በ2013 የጠፋችው ፑጃ በአስደናቂ ሁኔታ ከጠላፊዎቿ አምልጣ በ16 ዓመቷ ዳግመኛ ከቤተሰቧ ተቀላቅላላች።

የፎቶው ባለመብት, RAFIQ

የምስሉ መግለጫ, በ2013 የጠፋችው ፑጃ በአስደናቂ ሁኔታ ከጠላፊዎቿ አምልጣ በ16 ዓመቷ ዳግመኛ ከቤተሰቧ ተቀላቅላላች።

“ይደበድቡኝ ነበር”

ለተወሰነ ጊዜ ትምህርቷን እንድትቀጥል ፈቅደውላት ነበር።

ጥንዶቹ ልጅ ሲወልዱ ግን ከትምህርት ቤት አስወጧት።

ልጅ ከወለዱ በኋላ ፑጃን የበለጠ ያሰቃዩዋት ጀመር።

“በቀበቶ ይደበድቡኝ ነበር። በቡጢ ይመቱኝ ነበር። አንድ ጊዜ በወፍራም መዳመጫ መተውኝ ጀርባዬ ደምቶ ነበር። ከ12 እስከ 24 ሰዓት ለሚደርስ ጊዜ ቤት ውስጥ ከምሠራው በተጨማሪ ውጪም እሠራ ነበር።”

ጥንዶቹ የሚኖሩት ቤተሰቦቿ ቤት አቅራቢያ ቢሆንም መንገዱን ስለማታውቀው ምንም ማድረግ አልቻለችም።

ጥንዶቹ ሁሌም ይቆጣጠሯት ስለነበር ሰዎች እንዲረዷት መጠየቅ አልቻለችም።

ስልክ፣ ገንዘብም አልነበራትም።

“ሰዎች እንዲረዱኝ ጠይቄ ለማምለጥ ወሰንኩ”

አንድ ቀን ግን ፑጃ ጥንዶቹ ተኝተው ሳለ ስልካቸውን ወሰደች።

ዩቲዩብ ከፍታ ስሟን ጻፈች።

የአፋልጉኝ ማስታወቂያ አገኘች።

ማስታወቂያው ላይ ስልክ ተጽፎ ነበር።

“ሰዎች እንዲረዱኝ ጠይቄ ለማምለጥ ወሰንኩ” ትላለች።

ለማምለጥ ብትወስንም ውሳኔዋን ለመተግበር ሰባት ወራት ወስዶባታል።

የ35 ዓመቷ ፓሚላ ዴቫንድራ በጥንዶቹ ቤት ሠራተኛ ነበረች።

ፑጃ ፓሚላ እንድትረዳት ተማጸነቻት።

ፓሚላ ሳታቅማማ ተስማማች።

የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ላይ የተጻፈውን ስልክ ቁጥር ሲደውሉ የፑጃ ቤተሰብ ጎረቤት የሆነው ራፊቅን አገኙ።

ፑጃ ከእናቷ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በቪድዮ ተነጋገረች።

ከዚያም ለመገናኘት ተቀጣጠሩ።

እናትየዋ ልጃቸው ላይ የሚያውቁትን የሰውነት ምልክት ሲያዩ በደስታ ሲቃ መዋጣቸውን ያስታውሳሉ።

ፑጃ እና እናቷ

የፎቶው ባለመብት, DIPALI JAGTAP

የምስሉ መግለጫ, እናቷ ከልጃቸው ተለይተው የኖሩባቸውን ዓመታት ለማካካስ እየሞከሩ ነው።

“ልጄን እንዳገኘሁ አወቅኩ”

“ሰውነቷ ላይ ያለውን ምልክት ሳይ ልጄን እንዳገኘሁ አወቅኩ። መጠራጠር አቆምኩ” ይላሉ እናት።

ፓሚላ እናት እና ልጅ እንዲገናኙ በማድረጓ በጣም ደስተኛ ናት።

“ማንኛዋም እናት እርዳታ የሚፈልግ ልጅን መተባበር አለባት። ልጁ የእሷ ባይሆንም እናት መሆኗ ብቻ በቂ ነው” ትላለች።

ፑጃ ከእናቷ ጋር ከተገናኘች በኋላ ቤተሰቡ ወደ ፖሊስ አመራ።

“ለፖሊሶቹ ሁሉንም ነገር ነገርኳቸው። ያገቱኝ ሰዎች የት እንደሚኖሩም ጠቆምኩ” ትላለች ወጣቷ።

ጥንዶቹ ወዲያው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ።

የሙምባይ ዋና ኢንስፔክተር ሚሊንድ ኩርዴ፣ ጥንዶቹ በእገታ፣ በማስፈራራት፣ አካላዊ እንግልትና የሕጻን ጉልበት ብዝበዛ ነው የተከሰሱት።

ፑጃ ከቤተሰቧ ጋር ከተቀላቀለች በኋላ ቤተሰቡ ሰላም አግኝቷል።

ልጅ ሳለች የሚያውቋት ጎረቤቶቿም ደስታቸውን ገልጸዋል።

እናቷ ከልጃቸው ተለይተው የኖሩባቸውን ዓመታት ለማካካስ እየሞከሩ ነው።

ልጃቸው የምትወደውን ምግብ ያበስላሉ። ፀጉሯን ይሠራሉ። በቻሉት ሁሉ አብረዋት ጊዜ ያሳልፋሉ።

ፓሚላ እናት እና ልጅ እንዲገናኙ በማድረጓ በጣም ደስተኛ ናት።

የፎቶው ባለመብት, PRAMILA DEVENDRA

የምስሉ መግለጫ, ፓሚላ እናት እና ልጅ እንዲገናኙ በማድረጓ በጣም ደስተኛ ናት።

የፑጃ ቤተሰብ ትግል

የፑጃ አባት ከአራት ወራት በፊት ነበር በካንሰር የሞቱት።

ቤተሰቡ የሚተዳደረው በእሳቸው ደመወዝ ነበር።

እናትየዋ ልጆቻቸውን ለማሳደግ የባለቤታቸውን ሥራ መሥራት ጀምረዋል።

አሁን በባቡር ጣቢያ ምግብ ይሸጣሉ።

ገቢያቸው ለቤተሰቡ በቂ አይደለም።

“የልጄ ጉዳይ በሕግ ስለተያዘ ጉዳዩን ለማስፈጸም ገንዘብ አወጣለሁ። አንድ ቀን ባልሠራ የምንበላው እናጣለን” ይላሉ።

ፑጃ አሁንም በጥንዶቹ በደረሰባት ስቃይ ሳቢያ እንቅልፍ የላትም።

አዘውትራ ትቃዣለች።

አባቷን ማጣቷም ያሳዝናታል።

ለደኅንነቷ ስትል ብዙውን ጊዜ ቤት ውስጥ ታሳልፋለች።

ከቤት ከወጣችም ከቤተሰቦቿ ጋር ሆና ነው።

“እናቴን ማገዝ ብፈልግም ከቤት መውጣት አይፈቀድልኝም። መማርም እፈልጋለሁ።”

ቤተሰቡ በብዙ ችግር ቢሸበብም እናትየዋ ደስተኛ ናቸው።

“ሥራ አታካች ነው። ግን ፑጃን ሳያት ጉልበት አገኛለሁ። ከጠፋችበት በመመለሷ እጅግ ደስተኛ ነኝ።”