የጂቡቲው መሪ በቀጣዩ ምርጫ እንዲወዳደሩ የዕድሜ ገደብ ከሕገ መንግሥቱ እንዲነሳ ተወሰነ

ኢስማኤል ኦማር ጊሌ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጂቡቲን ለ25 ዓመታት የመሩት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ

የጂቡቲ ፓርላማ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ለስድስተኛ የሥልጣን ዘመን እንዲወዳደሩ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ የተቀመጠውን የዕድሜ ገደብ በሙሉ ድምጽ አነሳ።

የ77 ዓመቱ አዛውንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ መካከል ባለው ቁልፍ ቦታ ላይ የምትገኘውን ትንሽዬ አገር ጂቡቲን ላለፉት 25 ዓመታት መርተዋል።

የጂቡቲ ሕገ መንግሥት አንድ መሪ ዕድሜው 75 ዓመት ካለፈው ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር እንደማይችል ይከለክላል። ይህም የሕገ መንግሥቱ ገደብ ፕሬዝዳንት ጊሌ በሚቀጥለው የአውሮፓውያን ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ላይ እንዲሳተፉ አይፈቅድም።

ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ለተጨማሪ የሥልጣን ዘመን እንዲወዳደሩ ለማስቻል የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተዘጋጅቶ ለአገሪቱ ፓርላማ እሁድ ዕለት ቀርቦ በሁሉም አባላት ተቀባይነት አግኝቶ መጽደቁን አፈ ጉባኤው ለፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ተናግረዋል።

የፓርላማውን ውሳኔ ፕሬዝዳንቱ ተቀብለው ማጽደቅ ወይም ሕዝበ ውሳኔ እንዲሰጥበት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ካጸደቁት ደግሞ ፓርላማው ከሳምንት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ድምጽ ይሰጥበታል።

አሁን በጂቡቲ የፓርላማ አባላት እንዲሻሻል የተወሰነበት ለፕሬዝዳንትነት በሚወዳደሩ ዕጩዎች ላይ የዕድሜ ገደብ የሚጥለው አንቀጽ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ውስጥ እንዲካተት ያደረጉት ራሳቸው ፕሬዝዳንት ኦማር ጊሌ ነበሩ።

ይህ በአውሮፓውያኑ 2010 በፕሬዝዳንቱ የተደረገው ለውጥ የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን ገደብ እንዳይኖረው ከማድረጉ በተጨማሪ አንድ የሥልጣን ዘመን ከስድስት ዓመት ወደ አምስት ዝቅ እንዲል አድርጓል።

ከአገር ውጪ ያሉ የጂቡቲ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና የመብት ተከራካሪዎች ፕሬዝዳንቱ ለስድስተኛ የሥልጣን ዘመን ለመወዳደር እንዲችሉ የተደረገውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያን ነቅፈው በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ለውጥ እንዲመጣ ጥሪ አቅርበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ የፓርላማው ውሳኔ በአገር ውስጥ እና በውጪ ከሚኖሩ ጂቡቲያውያን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞታል።

የ24 ዓመቱ ተማሪ ሃኪም "ስድስተኛ ዙር የሥልጣን ዘመንን በመቃወም ጂቡቲ የምትነቃበት ጊዜ አሁን ነው። የማዳጋስካር ወጣቶች እንዳደረጉት ማድረግ እንችላለን" ሲል የጻፈ ሲሆን፣ ሃዋ የተባለች አክቲቪስት ደግሞ "ዲሞክራሲያዊ የመንግሥት ግልበጣ በማድረግ አገራችንን ከዚህ ቅዠት ልንታደጋት ይገባል፤ ሰልችቶናል" በማለት በኤክስ ላይ ጽፋለች።

የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ሶኒያ ለ ጉሪሊች "በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተቃውሞዎች አሉ፤ ነገር ግን ሃሳብን በነጻነት መግለጽ እና የፕሬስ ነጻናትን በምትጨቁነው ጂቡቲ ውስጥ መሬት ላይ ተቃውሞው ቦታ አይኖረውም" ብለዋል።

የጂቡቲ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት አገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ የሆነው "ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ በሚገኙበት ያልተረጋጋው የአፍሪካ ቀንድ የምትገኘውን ትንሽ አገር መረጋጋትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ ነው" ብለዋል።

አክለውም "እንደማስበው ከአገሪቱ ሕዝብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሕገ መንግሥት ማሻሻያውን ይደግፈዋል።"

ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ለአምስተኛ ጊዜ ተወዳድረው የነበሩት ፕሬዝዳንት ጊሌ ከመራጮች የ97 በመቶዎቹን ድምጽ በማግኘት ነበር ያሸነፉት።

ፕሬዝዳንቱ የሚመሩት ፓርቲም የጂቡቲ ፓርላማን የብዙኃን መቀመጫን በመያዝ ውሳኔዎችን ያሳልፋል።

ኢስማኤል ኦማር ጊሌ በአውሮፓውያኑ 1999 ወደ ሥልጣን የመጡት የጂቡቲ መሥራች መሪ ከነበሩት እና አገሪቱን ለ22 ዓመታት ከመሩት ሐሰን ጉሌድ ኦፕቲዶንን በመተካት ነው።

ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ በሥልጣን ላይ አርባ አመት ሊሞላቸው የተቃረቡትን የኡጋንዳውን ዩዌሪ ሙሴቪኒን እና ኤርትራን ወደ 30 ዓመት የመሩትን ኢሳያስ አፈወርቂን ተከትለው በምሥራቅ አፍሪካ አገራት በሥልጣን ላይ ረጅም ጊዜ በመቆየት ሦስተኛው ናቸው።

አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እንዳላት የሚነገርላት ትንሿ ጂቡቲ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር አካባቢ ቁልፍ በሆነ ቦታ ላይ መገኘቷ ከመጠኗ በላይ እንድትገዝፍ አድርጓታል።

ጂቡቲ ዋነኛዋ የኢትዮጵያ ወጪ እና ገቢ ምርት መተላለፊያ ስትሆን የአሜሪካን፣ የፈረንሳይ እና የቻይና ጦር ሠፈሮችን ስታስተናግድ የሌሎች በርካታ አገራት ባሕር ኃይሎች መተላለፊያ ናት።