በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሠፈራቸውን የመሠረቱ ኃያላን አገራት

የቻይና የባሕር ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, CHINA NEWS SERVICE

የምስሉ መግለጫ, የቻይና የባሕር ኃይል በጂቡቲ

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን አንዳንድ ጊዜም ኬንያን የሚያካትተው የአፍሪካ ቀንድ የዓለማችችንን ትልቁን የባሕር ላይ የንግድ መስመርን ይዟል።

የአፍሪካ ቀንድን ወሳኝ ስፍራ እንዲሆን ያስቻለው የቀይ ባሕር፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ነዳጅ፤ ከእስያ ደግሞ የኢንዱስትሪ ምርቶች ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ የሚተላለፉበት በመሆኑ ነው።

ይህ ምክንያት ሆኗቸው ከዓመታት በፊት ጀምሮ ኃያላን አገራት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካሉ አገራት ጋር ወዳጅነትን በመመሥረት ተጽዕኗቸውን እና ቁጥጥራቸውን ማጠናከር ይፈልጋሉ።

በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ በሚገኘው የባብል ኤል-ማንደብ ሰርጥ ላይ ወታደራዊ ኃይላቸውን ለማሰማራት በርካታ አገራት ፍላጎት አላቸው።

አንዳንዶችም በቀጠናው የጦር ሠፈሮችን አቋቁመው ወታደሮቻቸውን አስፍረዋል።

በዚህም የተነሳ አካባቢው የኃያላን እና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚፈልጉ አገራት መካከል የሚደረግ የትግል ሜዳ ሆኖ ቆይቷል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአፍሪካ ቀንድ አገራት እንዲሁም ምዕራባውያኑ፣ ቱጃሮቹ የአረብ አገራት፣ ቱርክ፣ ሩሲያ እና ቻይና በአካባቢው በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የተጽዕኖ ለማሳደግ የቻሉትን ሁሉ ሲያደርጉ ነበር።

እንደ አሜሪካ እና ቻይና ያሉት አገራት ደግሞ አካባቢውን በሚመለከት ብቻ የሚሰሩ አምባሳደሮችን ሹመዋል።

ባለፉት ወራት የሩሲያ፣ የቻይና እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ተደጋጋሚ ጉብኝት አድርገዋል።

ከአገራቸው ውጭ የጦር ሠፈር ካቋቋሙ አገራት ውስጥ በአፍሪካ ቀንድ ጦር የሌላቸው ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። አንዳንዶቹ ከአገራቸው ውጭ ያላቸው ብቸኛው የጦር ሠፈር በአፍሪካ ቀንድ ይገኛል።

እነዚህም የጦር ሠፈሮች፣ የባሕር ኃይል ወደቦች፣ አየር ኃይል እና ማስልጠኛ ማዕከላትን ጭምር ያካትታል።

ለመሆኑ የትኞቹ አገራት በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሠፈራቸውን ገነቡ?

በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሠፈራቸውን የገነቡ አገራትን የሚያሳይ ካርታ
የምስሉ መግለጫ, በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሠፈራቸውን የገነቡ አገራትን የሚያሳይ ካርታ

አሜሪካ

አሜሪካ እአአ በ2011 ከደረሰባት የሽብር ጥቃት በኋላ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ሚና ከፍ ብሏል።

እአአ በ2001 ጂቡቲ ካምፕ ሌሞኒየርን ለአሜሪካ አከራይታለች። ቋሚ የጦር ሠፈር ለማድረግ ባለው ዕቅድም ከ39 ሔክታር ወደ 202 ሔክታር እንዲያድግ ተደርጓል።

እአአ በ2012 የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት የጦር ሠፈሩን ለማልማት የ14 ቢሊዮን ዶላር ዕቅድ አውጥቷል። የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የባራክ ኦባማ አስተዳደር የ30 ዓመት ሊዝ ከመስማማቱ በተጨማሪ ዓመታዊ ወጪው 63 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተገልጾ ነበር።

የጦር ሠፈሩ 2000 የሚጠጉ የአሜሪካ እና የሌሎች አጋር አገራትን ወታደሮች ይዟል።

4000 የሚጠጉ ወታደሮች እአአ በ2017 በጂቡቲ በጊዜያዊነት ከትመው እንደነበር ተነግሯል። የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል አባላትን ከመያዝ ባሻገር በአህጉሪቱ ላለው የአሜሪካ የድሮን እና የስለላ ማዕከልም ሆኖ ያገለግላል።

ቻይና

ከአፍሪካ አገራት ጋር ከፍተኛ የንግድ ትስስር መመሥረት የቻለችው ቻይና እአአ በ2008 ነበር በኤደን ባሕረ ሰላጤ የፀረ ባሕር ላይ ውንብድና ዘመቻ የጀመረችው።

ቀጥለው ባሉት አስር ዓመታት 26 ሺህ ሠራዊቷን ወደ አካባቢው አሰማርታለች። የቻይና ጦር በተለይም እአአ ከ2009 እስከ 2013 ድረስ የሎጂስቲክ ድጋፍ የሚያገኘው ከጂቡቲ ወደብ ነበር።

ቻይና የጦር ሰፈር ጅቡቲ ላይ ያቋቀመችው እአአ በ2017 ነው። የጦር ሰፈሩ የሎጂስቲክ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ አገሪቱ በፀረ የባሕር ላይ ውንብድና፣ ሠላም ማስከበር እና ሌሎች ዘመቻዎች ያላትን ተሳትፎ ያጠናከረችበት ነው።

በተጨማሪም ቻይና በተለያዩ አገራት ውስጥ ካላት ተሳትፎ አንጻር፣ የፀጥታ ችግሮች ሲያጋጥሙ ዜጎቿን ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች ከማውጣት ባለፈ በሌሎች አገራት ያላትን ሃብት ለመጠበቅም ትጠቀምበታለች።

በጂቡቲ የሚገኘው የቻይና የጦር ሠፈር ከዶራሌህ ወደብ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ይገኛል። በ36 ሄክታር ላይ ለተንጣለለው የጦር ሠፈር የ10 ዓመት ሊዝ ተፈራርማለች። በዓመትም 20 ሚሊዮን ዶላር እንደምትከፍል መረጃዎች ያሳያሉ።

ፈረንሳይ

ፓሪስ ከግዛቷ ውጭ ያለው ትልቁ ቋሚ የጦር ሠፈሯ በጂቡቲ የከተመው ነው። ፈረንሳይ ከፈረንጆቹ 1970 መጨረሻ ጀምሮ ቅኝ በገዛቻት ጂቡቲ የጦር ሠፈሯን አስጠብቃ ቆይታለች።

የፈረንሳይ ወታደሮች በተለያዩ የጂቡቲ ከተማ አካባቢዎች ከመስፈር ባለፈ በምሥራቅ አፍሪካ፣ የሕንድ ውቂያኖስ ወይንም በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሰማራ በተጠንቀቅ ቆሟል።

ሁለቱ አገራት ባላቸው ስምምነት መሠረት የፈረንሳይ ጦር የጂቡቲን ድንበር እና የአየር ክልል የመጠበቅ ኃላፊነትም አለበት። የፈረንሳይ ጦር የጀርመን እና የስፔን ጦርን ጨምሮ የአውሮፓ ፀረ የባሕር ላይ ውንብድና ቡድንንም ያስተናግዳል።

ጦሩ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጋርም ወታደራዊ ልምምድ ያደረጋል።

የፈረንሳይ ጦር በአካባቢው ያለው ተሳትፎ በአገሪቱ ፓርላማ ጥያቄ ቢነሳበትም በተልዕኮው ላይ ግን ለውጥ አላመጣም።

በጂቡቲ ከሚገኘው የፈረንሳይ ጦር ጋር ተዳብለው ከሚገኙ አገራት መካከል አንዱ የጀርመን ጦር ነው።

ጀርመን በአፍሪካ ቀንድ ጦሯን ያሰማራችው ከፈረንጆቹ 2001 ጀምሮ ነው። ጀርመን በአውሮፓ ኅብረት ዘመቻ ውስጥም ጥቂት ወታደሮቿን አካታለች።

ከጀርመን በተጨማሪ ስፔን በፈረንሳይ የጦር ሠፈረ 50 የሚደርሱ ወታደሮቿን አሰማርታለች።

ስፔን ከ2008 ጀምሮ በአውሮፓ ኅብረት ጥላ ስር ለጥበቃ እና ለስለላ ሥራ መርከቦቿን እና አውሮፕላኖቿን አሰማርታለች።

ጅቡቲ ቁልፍ ቦታ ላይ ያለች አገር በመሆኗ በርካታ ኃያላን አገራት የጦር ሰፈራቸውን ከትመውባታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጂቡቲ ቁልፍ ቦታ ላይ ያለች አገር በመሆኗ በርካታ ኃያላን አገራት የጦር ሰፈራቸውን ከትመውባታል

ቱርክ

ቱርክ የባሕር ኃይሏ ፀረ የባሕር ላይ ውንብድና ዘመቻ ላይ መሰማራት የሚያስችለውን የመጀመሪያውን ሕግ በ2009 አውጥታለች። በኋላም በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ ፀረ የባሕር ላይ ውንብድና ዘመቻን ተቀላቅላለች።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የባሕር ኃይሏን ወደ ቀይ ባሕር፣ የኤደን ባሕረ ሰላጤ እና የአረብ ባሕር በተደጋጋሚ አሰማርታለች።

ቱርክ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾም የጦር ሰፈር ገንብታለች። ከአገሯ ውጭ ያለው ትልቁ የጦር ሰፈሯ 50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ 200 ወታደሮቿንም ያስተናግዳል።

ቱርክ ለሶማሊያ ብሔራዊ ጦርም ሥልጠና ትሰጣለች።

ቱርክ ከሱዳን ጋር ለ99 ዓመት በሚዘልቅ የሊዝ ስምምነት በመፈራረም ሰዋኪን ደሴትን የቱሪስት ማዕከል ልታደርግ ወስናለች።

ይህ ስምምነት አንካራ በአካባቢው የጦር መርከብ ወደብ እንደሚያስገኝላት በሱዳን በኩል ተገልጿል። ነገር ግnእ ስምምነቱ በተለይ በግብፅ እና በባሕረ ሠላጤው አገራት መገናኛ ብዙኃን ጥሩ ምላሽ አላስተናገደም።

በኋላ ላይ ደግሞ ስምምነቱ ወታደራዊ አገልግሎትን እንደማያካትት ሱዳን እና ቱርክ በተናጠል አሳውቀው ነገሩን አብርደውታል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም የኢራንን እንቅስቃሴ ለመገደብ ስትል ከተለያዩ አገራት ጋር ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ግንኙነቷን በማጠናከር ላይ ትገኛለች።

አገሪቱ ቀደም ሲል በጂቡቲ የጦር ሠፈር ልታቋቁም ሃሳብ የነበራት ቢሆንም በሁለቱ አገራት ግንኙነት መሻከር ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።

በመቀጠል ሃሳቧን ቀይራ የጦር ሠፈሯን በኤርትራ አሰብ ለመገንባት ወሰነች። በኋላም ግንባታውን አጠናቃ በየመን ለነበረው ጦርነት ተሳትፎ ተጠቅማበታለች።

የጦር ሰፈሩ አሥመራ ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ እገዳ በመተላለፍ የተቋቋመው ነው በሚል ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፊቷን የሶማሊያ ብሔራዊ ጦርን ለማሠልጠን በሚል የጦር ሠፈር በሞቃዲሾ አቋቁማለች።

በኋላ ግን በሁለቱ አገራት አለመግባባት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የጦር ሠፈሩን ለቅቃ ስትወጣ ሶማሊያ ቦታውን መረከቧ ታውቋል።

ከዚያም ፊቷን ራሷን ነጻ አገር በማለት ወደ አወጀችው ሶማሊላንድ በማዞር በበርበራ የጦር አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት ተስማማች።

ለ25 ዓመት የሚዘልቅ የጦር መርከብ ወደብ እና የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ተጀምሮ ነበር።

42 ኪሎ ሜትር ስኩዌር የሚሸፍነውን የጦር ሠፈር ለመገንባት 90 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረጋል ተብሏል።

ዩናይትድ ኪንግደም

በአፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ዩናይትድ ኪንግደም ጥቂት ቁጥር ያላቸው ወታደሮቿን በጂቡቲው ካምፕ ሌሞኒየር አስፍራለች።

ከየመን ወደ ባብ ኤል-ማንደብ ሰርጥ በሚደረገው የንግድ ልውውጥ ወቅት የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልም ልዩ ኃይሏን ወደ ጂቡቲ ልካለች።

ሩሲያ

እአአ በ2008 በራሷ ፀረ የባሕር ላይ ውንብድና ዘመቻ ያደረገች ሲሆን፣ ከዚያ በኋላም ተከታታይ ግን ቋሚ ያልሆነ ዘመቻ አካሂዳለች።

የጦር መርከቦችም በአካባቢው በተደጋጋሚ ተሰማርተዋል። የጂቡቲ እና ሌሎች ወደቦችን ደግሞ ትጠቀማለች።

ሩሲያ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ያላትን ኃይል ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ይገለጻል። ሱዳን ደግሞ ቀዳሚ ምርጫዋ ናት። ጂቡቲ ፈቃድ ከሰጠቻት በኋላ የውጭ ኃይሎች የግጭት ማዕከል ላለመሆን በማሰብ ቃሏን ማጠፏ ተዘግቧል።

በዚህ ጉዳይ ሱዳን እና ሩሲያ ተደጋጋሚ ውይይት ካደረጉ በኋላ ስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተዘግቧል። በ2018 ደግሞ ከኤርትራ ጋር የሎጂስቲክስ ወደብ ለማቋቋም ከስምምነት መድረሷ ተነግሮ ነበር።

የስፔን የጦር መርከብ፣ ላ ጋልሲያ፣ በጅቡቲ በሚገኘው የፈረንሳይ የጦር መንደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የስፔን የጦር መርከብ፣ ላ ጋልሲያ፣ በጅቡቲ በሚገኘው የፈረንሳይ የጦር መንደር

ጣሊያን

የጣሊያን የጦር ሠፈር መቀመጫውን ከጂቡቲ-አምቡሊ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጎን ይገኛል።

የጦር ሠፈሩ በአካባቢው ያለውን የጣሊያን የባሕር ኃይል ለመደገፍ ተብሎ በ2013 የተቋቋመ ነው።

300 ወታደሮችን መያዝ የሚችለው የጦር ሰፈር 80 አባላት ብቻ አሉት።

ዓመታዊ የሊዝ ዋጋው ደግሞ 2.6 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ታውቋል።

ጃፓን

ጃፓን እአአ ከ2009 ጀምሮ የጦር መርከቦችን እና አውሮፕላኖችን ወደ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ለፀረ የባሕር ላይ ውንብድና ስትል ማሰማራት ጀምራለች።

ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ የጦር ሠፈሯን በጅቡቲ አቋቁማለች። 12 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የጦር ሰፈር 180 ወታደሮችን ይይዛል።

ለግንባታው 40 ሚሊዮን ዶላር መውጣቱም ተዘግቧል። ከቻይና በአካባቢው መጠናከር ጋር ተያይዞ የጦር ሠፈሩን ለማሳደግም ዕቅድ አላት።

ጃፓን በምሥራቅ አፍሪካ ላሉ አገራት ወታደራዊ ስልጠና ትሰጣለች። ከሕንድ ጋር ባደረገችው ስምምነት ደግሞ የጦር ሠፈሯን ከደልሂ ጋር ለመጋራት ወስናለች።

ሳዑዲ አረቢያ

በየመን ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ ሳዑዲ አረቢያ በአካባቢው ያላት ወታደራዊ ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

የሳዑዲ አረቢያ ወታደሮች መጀመሪያ ላይ በጂቡቲ ከተሙ። እአአ በ 2015 በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና በጂቡቲ መካከል ያለው ግንኙነት በመሻከሩ ጦሯ ሌሎች ቦታዎችን ማማተር ጀምሯል።

የኤርትራው የአሰብ ወደብ እና የሳዑዲው የጄዳ ወደብ ደግሞ ቀዳሚዎች ተመራጮች ነበሩ። በኋላም እአአ በ 2016 ሳዑዲ አረቢያ ከጂጅቡቲ ጋር የጦር ሰፈር ለማቋቋም ስምምነት ደርሳለች።

የየመን ግጭት ከተጀመረ ወዲህ ሳዑዲ አረቢያ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ትልቅ ቁጥር ያለው የባሕር ኃይል አሰማርታለች።

ጥምር የባሕር ኃይሎች

በሶማሊያ ውስጥ ለአስርታት የተካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ሰፍኖ በነበረው ሰፊ የጦር አበጋዞች ፍልሚያ የባሕር ላይ ዝርፊያ ተስፋፍቶ ነበር።

በዚህም ሳቢያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ለአጠቃላዩ የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ቁልፍ የሚባለው የቀይ ባሕር የባሕር መስመር ስጋር ውስጥ ገብቶ ነበር።

ይህንንም ስጋት ለመቅረፍ በአሜሪካ የሚመራው የ33 አገራት የጥምር የባሕር ኃይሎች ቡድን ከሕንድ ውቅያኖስ አንስቶ በቀይ ባሕር ላይ ተሰማርቶ ነበር።

ይህ ጥምረት በፀረ ሽብርተኝነት ላይ ትኩረት በማድረግ የባሕር ላይ ወንበዴዎችን መከላከል፤ ክልላዊ ትብብርን ለማበረታታት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የቀይ ባሕር አካባቢን ለመፍጠር የተፈጠረ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ አገራት በተለያየ ጥምረት እና ሽርክና በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሠፈር ከመመስረት ባለፈ ጦር በማሰማራት የፀረ የባሕር ላይ ውንብድናን እና ሽብርተኝነትን ለመከላከል ይሠራሉ።

የአውሮፓ ኅብረቱ “ኦፕሬሽን አትላንታ” እና የኔቶው “ኦፕሬሽን ኦሽን ሺልድ” በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ደኅንነት በመጠበቅ ረገድ ተጠቃሽ ተልዕኮዎች ናቸው።