ለአንድ ወር የዘለቀው የሱዳን ጦርነት

 የሱዳን ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት አንድ ወር አስቆጠረ።

የአሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ መንግሥታት በጥምረት ሁለቱን ኃያላን ጦሮች ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የጀመሩት የማሸማገል ሁኔታም ፍሬ አላፈራም።

ብዙ የተባለለት ይህ ድርድርም ለአንድ ወር የዘለቀውን ጦርነት ሊያስቆመው አልቻለም።

በሱዳን ጦር መሪ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል ጦርነቱ የተቀሰቀሰው ሚያዝያ 7/ 2015 ዓ.ም ነበር።

ሁለቱ ጄነራሎች ለሶስት አስርት ዓመታት ሱዳንን የመሯትን ኦማር አልበሽርን በአውሮፓውያኑ 2019 ከስልጣን ካስወገዱ በኋላ አገሪቷንም ሲመሯት ቆይተዋል።

በቀጣናዊ እና አለም አቀፍ አጋሮች አማካኝነት የተደረሱ በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነቶችም በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ተጥሰዋል።

በጦርነቱ ቢያንስ 676 ሰዎች ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሱዳናውያን ተፈናቅለዋል።

ከአራት ቀናት በፊት የሁለቱ ጦር ተወካዮች በሳዑዲ አረቢያዋ የወደብ ከተማ ጅዳ ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለመጠበቅ እና የረድዔት ድርጅቶችም እርዳታን በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች እንዲያደርሱ የሚያደርግ ስምምነት ላይም ደርሰዋል።

ሆኖም የቀጠለው ጦርነት በባላንጣነት የተቀመጡት ሁለቱ ጄነራሎች ሱዳንንን ለመቆጣጠር ምን ያህል ርቀት እንደሚሄዱ ያሳየ ነው ተብሏል።

ጦርነቱ በምን ሁኔታ እየሄደ ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሱዳን የሲቪል መንግሥት ለመመስረት የተያዘው ቀነ ገደብ ሲቃረብም ነው በመደበኛው ጦር እና በፈጥሮ ደራሽ ኃይሉ መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ የመጣው።

ለዚህም ትርምስ ምክንያቱ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከዋናው ጦር ጋር እንዴት መልሶ ማዋቀር ይችላል በሚለውም ጉዳይ ላይ ከማተኮሩ ጋር የተያያዘ ነው።

በጦሩ እና በፈጥኖ ደራሹ መካከል የነበረው ወታደራዊ ፍጥጫም ለቀናት ከቆየ በኋላ ሚያዝያ 7 በመዲናዋ ካርቱም እና በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ቁልፍ የጸጥታ ተቋማት አቅራቢያ ጦርነቱ ተቀሰቀሰ።

ጄነራል ሄምቲ ፈጣን ድል እንደሚቀዳጁ ቃል የገቡ ሲሆን በካርቱም እና በሌሎች ቦታዎች ሰራዊታቸው ቀድሞ ድል ማስመዝገቡ ተዘግቧል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት፣ በካርቱም የሚገኘውን ዋና አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም በሰሜናዊ የሜሮዌ እና በደቡብ ኤል ኦቤይድ ከተሞች የሚገኙ የጦር ሰፈሮችን በመቆጣጠር ቁልፍ ተቋሟትን ይዣለሁ አለ።

ነገር ግን ጦሩ በሚግ 29 ጄቶች በመታገዝ ባደረሰው የአጸፋዊ ምላሽ ጥቃት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከሜሮዌ ገፍቶ ማስወጣት ቻለ።

እንዲሁም በካርቱም የሚገኙ የጦር ሰፈሮችን አወደመ። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የአየር መቃወሚያ መሳሪያዎች ቢኖሩትም የሱዳን አየር ኃይል ለጦሩ የበላይነትን አስገኝቶለታል። የሱዳን ጦር ጄቶች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኢላማዎችን በየቀኑ ኢላማ ማድረግ ቀጥለዋል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከማጥቃት ይልቅ በመከላከል ላይ ያለ ይመስላል። በካርቱም፣ ኦምደርማን እና ባህሪ መኖሪያ አካባቢዎች ውስጥ የሰፈሩ የሰራዊቱ አባላትም የአየር ጥቃቱ ኢላማ ሆነዋል። በመኖሪያ አካባቢዎቹ ላይ የደረሰው ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን በእጅጉ የጎዳ ሲሆን ሆስፒታሎችን ጨምሮ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል።

ጦሩ ቀይ ባህር፣ ከሰላ፣ አልቃዳሪፍ፣ አልጃዚራ፣ የናይል ወንዝ ተፋሰስ አካባቢዎችን፣ ሲናር፣ ደቡብ ኮርዶፋን፣ ምዕራብ ኮርዶፋን ግዛቶች ውስጥ ወታደሮቹ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሉ ጠቅሶ ከ18 ግዛቶች ውስጥ 13ቱን ተቆጣጥሬያለሁ ብሏል።

በሰሜን ኮርዶፋን ግዛት ዋና መዲና በሆነችው ኤል-ኦቤይድም አልፎ አልፎ ጦርነት እየተካሄደ ስለመሆኑም ተነግሯል።

በአውሮፓውያኑ የርስ በርስ ጦርነት እንደ ጃንጃዊድ ሚሊሻ ሆኖ ከአማጺያን ጋር የተፋለመባት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጠንካራ ይዞታ በሆነችው ዳርፉር ያሉ ከተሞችን ኃይሉ መቆጣጠር ተስኖታል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የሱዳን ጦር የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከደቡብ ዳርፉር መዲና ኒያላ ማስወጣቱን እና በኤል ፋሺር የሚገኘው የጦር ሰፈሩ ላይም ጥቃት ማድረሱንም አስታውቋል። የሰሜኗ ዳርፉር መዲናም ጦርነት እያስተናገደች ትገኛለች።

በምስራቅ ዳርፉር እና በማእከላዊ ዳርፉር ምንም አይነት ጦርነት ሪፖርት ባይደረግም ሁለቱን ግዛቶች የሚቆጣጠረው ማን እንደሆነ ግልፅ አይደለም። በጦር ሰራዊቱ በኩል የላቀው የአየር ኃይል ሚዛን በምድር ጦር የተጠናከሩትን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ተዋጊዎች ከካርቱም እና ከአጎራባች ከተሞች ገፍቶ ማስወጣት አልቻለም።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች በፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት የሚያሳይ እና በቀጣይ ቀናትም በካርቱም እስረኞች መያዙን የሚያሳይ ቪዲዮ ለጥፏል። የሱዳን ጦር እስካሁን ድረስ ከዳርፉር እና ከኮርዶፋን ግዛቶች ያሉትን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የአቅርቦት መስመሮች መቁረጥ አልተሳካለትም።

የሱዳን ጦርነት ይራዘም ይሆን?

የሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ዋነኛ አላማ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባቸውን እና የአገሪቱ ቁልፍ መሠረተ ልማት ማዕከላት የሆኑትን ካርቱም፣ ኦምዱርማን እና ባህሪ ከተሞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተፋለሙ ይመስላል።

የሱዳን ጦር ሰራዊት አብዛኛዎቹን ድልድዮች እና በሦስቱ ከተሞች ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና የጦር ሰፈሮችን ተቆጣጥሯል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተወሰነውን የፕሬዚዳንቱን ቤተመንግሥት እንዲሁም በካርቱም እና ባህሪ ከተሞች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ስፍራዎችን መልሶ መቆጣጠሩ የሚታመን ሲሆን ተዋጊ ጄቶቹም በመዲናዋ የሚገኙትን ዋና ዋና የጦሩን ሰፈሮች አውድመዋል ተብሏል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከመኖሪያ ሰፈሮች ለማስወጣት ውጊያው የተፋፋመ ሲሆን ከሁለት ቀናት በፊት እንደገና በጂዳ የቀጠለውን ድርድርም እንዳያበላሸው ተሰግቷል።

ጦርነቱ በዳርፉር የፀጥታ ክፍተት እንዲፈጠር እንዲሁም የብሔር ግጭቶች እንደገና እንዲቀሰቀሱ ምክንያት ሆኗል።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ዕለት ጀምሮ በምዕራብ ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል-ጂኒና በተነሳ የብሔር ግጭት ወደ 500 የሚጠጉ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ታጣቂዎችም 7 ሺህ የሚደርስ መሳሪያዎችን ከፖሊስ ግምጃ ቤት ዘርፈዋል።

የተፋላሚዎቹ አሰላለፍ ምን ይመስላል?

ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የተቀዳጇቸውን ድሎች ለመንገር፣ እርስ ለመዘላለፍ እና የህዝብን ድጋፍ ለማግኘትም ማህበራዊ ሚዲያዎችን እየተጠቀሙ ይገኛል።

ጄነራል ሄምቲ በፖለቲካውና እና ዲፕሎማሲያዊ ግንባር ያላቸው ተቀባይነት እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ራሱን ከተራማጅ ድምጾች ጋር አጋርነት ለመፍጠር ሞክሯል።

ሆኖም በዳርፉር ጦርነት በተፈጸመው የዘር ፍጅት እንዲሁም የአልበሽርን ከስልጣን መገርሰስ ተከትሎ ሁለቱ ጄኔራሎች የመሩትን መፈንቅለ መንግሥት የተቃወሙ ሰልፈኞች ላይ በደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ጄነራል ሄምቲ ስማቸው ከግፎች ጋር ተያይዟል።

በተጨማሪም በአሁኑ ጦርነት ሰራዊታቸው ባንኮችን፣ ሱቆችን እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶችን በመዝረፍ በተደጋጋሚ ስሙ ተነስቷል። በሌላ በኩል ውጊያው ከቀጠለ ጦሩ የአቅርቦት መስመሮችን ክፍት እንደሚያደርግ በመታመኑም በአብዛኛው የአገሪቱ ግዛቶች ድጋፍ አለው።

የጄነራል ሄምቲ ኃይል በአገሪቱ የደህንነትና ስለላ ኤጀንሲ፣ በፖሊስ እንዲሁም በግጭቶች ወቅት እንዲንቀሳቀሱ ስልጠና የወሰዱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን የያዘው የፌደራሉ ተጠባባቂ ኃይል ይደገፋል።

ከሶስት ዓመታት በፊት ከሱዳን የሽግግር ባለስልጣናት ጋር የሰላም ስምምነት የተፈራረሙት እና በመፈንቅለ መንግሥቱ ወቅት ከሁለቱ ጄነራሎች ጎን የቆሙት የዳርፉር አማጺያን በአሁኑ ጦርነት ገለልተኛ መሆናቸው ተነግሯል።

ይሁን እንጂ በከተማዋ በሚገኙ የመኖሪያ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ መድረሱን ተከተሎም አንዳንድ አማጺ ቡድኖች ተዋጊዎቻቸውን በኤል ፋሺር አሰማርተዋል።

በሱዳን ምን አይነት ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ?

የሱዳን ጦር የበላይ ሆኖ ከቀጠለ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደ ዳርፉር ሊገፋ የሚችል ሲሆን ይህም የብሔር ግጭቶችን ሊያባብስ የሚችል አመጽ ሊፈጥር ይችላል።

በአጎራባች ቻድ ሰላማዊ ዜጎች እና የታጠቁ ተዋጊዎች መፈናቀላቸው ተዘግቧል፣ ይህም ሁኔታ ጦርነቱን ቀጣናዊ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋትን ደቅኗል።

ጦርነት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ጎረቤት ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳን እና የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን እየፈተናቸው ይገኛል።

ምንም እንኳን የሳዑዲና የአሜሪካ መንግሥት በተፋላሚዎቹ ጄኔራሎች ላይ ጫና ማሳረፍ ቢችሉም በውስጣዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አይችሉም።

ሁለቱ ጄነራሎች በአፍሪካ ህብረት እና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የሚደረጉትን የሽምግልና ጥረቶች ውድቅ አድርገዋል።

የጂዳ ስምምነት መፈረም በራሱ እንደ ስኬት ቢቆጠርም አፈጻጸሙን ለማሳካት ተጨማሪ ዙር ንግግሮች ያስፈልጋሉ።

አገሪቷ ከዚህ ቀውስ ለመውጣትም ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይቶችም ማድረግ አስገዳጅ ነው ተብሏል። ምናልባት አገሪቷ በመጨረሻም የተሻለ ያላት አማራጭ ሱዳንን ወደ ሲቪል የሚመራ የሽግግር መንግስት እና በመጨረሻም ወደ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ የሚመልስ ድርድር ይሆናል።