በእስር ላይ ያሉት አቶ ክርስቲያን እና አቶ ዮሐንስ ከከፍተኛ መጉላላት በኋላ ቀዶ ህክምና እንደተደረገላቸው ጠበቃቸው ተናገሩ

አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያለው
የምስሉ መግለጫ, አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያለው

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የፌደራል እና የክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያለው "በተደጋጋሚ አቤቱታ" ባለፈው ሰኞ ቀዶ ጥገና ማድረጋቸውን ጠበቃቸው ተናገሩ።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋሉት የም/ቤት አባላቱ በእስር ላይ ሳሉ ለገጠማቸው የጤና እክል በጊዜ ህክምና ለማግኘት ሳይችሉ መቅረታቸውን ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ም/ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው አዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ በታሰሩበት ጊዜ ለ"አንጀት ድርቀት" ህመም እንደተዳረጉ ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የም/ቤት አባላቱ ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንዲታከሙ ቢደረግም ህክምናቸውን ሳይጨርሱ ወደ አዋሽ አርባ እንዲመለሱ መደረጉንም አክለዋል።

በዚህም "ህመሙ እንደባሰባቸው" ከስምንት ወራት እስር በኋላ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ መናገራቸውን የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፤ ለፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ህክምና እንዲያገኙ ማመልከታቸውን አስታውሰዋል።

ፍርድ ቤቱ ቀን እየቆረጠ ህክምና እንዲያገኙ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ ታሳሪዎቹ ወደ ህክምና እንዲወሰዱ የጠየቁበት አካባቢን "የፀጥታ ስጋት" በምክንያትነት በማቅረብ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለማክበሩን ተናግረዋል።

"በተለይ ባለፉት ሁለት፤ ሦስት ወራት በፍርድ ቤቱ እና በማረሚያ ቤቱ መካከል ከፍተኛ የሆነ እሰጣ ገባ ነበር። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ይሰጣል፤ [ቃሊቲ ማረሚያ ቤት] ማረሚያ ቤቱ [ደግሞ] ትዕዛዙን የማይፈጽምበትን ምክንያት ብዙ ጊዜ ያቀርብ ነበር" ብለዋል።

አቶ ክርስቲያን እና አቶ ዮሐንስ በግላቸው ለመታከም አዲስ አበባ ውስጥ መቅረዝ የተባለ ሆስፒታል እና ቀበና አካባቢ የሚገኝ ዲማ የተባለ የዓይን ክሊኒክ ቢጠይቁም መጉላላታቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"'[ማረሚያ ቤቱ] የፀጥታ ችግር አለ። የፀጥታ ችግሩ እስከሚቀረፍ እና አካባቢውን እስከምንቃኝ ድረስ መውሰድ አንችልም' በሚል ነበር ለፍርድ ቤቱ መልስ የሰጠው" ብለዋል።

የም/ቤት አባላቱን ወደ ህክምና ለመውሰድ "ረጅም ጊዜ የሚወስድ አይደለም" ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ከረጅም ጊዜ መስተጓጎል በኋላ ባለፈው ሰኞ ኅዳር 30/2017 ዓ.ም. ቀዶ ህክምና ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም ሐኪሞቻቸው ለጥቂት ቀናት ሆስፒታል ተኝተው ክትትል እንዲደረግላቸው ያቀረቡትን ምክር ማረሚያ ቤቱ ባለመቀበሉ፤ ቀዶ ህክምናው ከተደረገ ከሰዓታት በኋላ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መወሰዳቸውን ገልፀዋል።

"ሆስፒታሉ ኦፕራሲዮን ከተደረገላቸው በኋላ ክትትል ለማድረግ፤ የሚፈሰውን ደም ለማቆም ለተወሰነ ቀን እንዲቆዩ የሚል ፍላጎት ነበር። ሆኖም ማረሚያ ቤቱ ማቆየት ስላልፈለገ ኦፕራሲዮን እንደሆኑ ከሰዓት በኋላ ነው ወደ ማረሚያ ቤት የመለሷቸው" ብለዋል።

"[ሐኪሞች] ደም የሚፈሳቸው ከሆነ ይዛችኋቸው ቅረቡ የሚል ትዕዛዝ [ነው] የሰጡት። ከዚህ ውጪ ምንም አማራጭ ማግኘት አልቻሉም" ብለዋል።

አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ የደንበኞቻቸው ተደጋጋሚ የህክምና ጥያቄ በመዘግየቱ የጤናቸው ሁኔታ እንደተባባሰ ጠቁመዋል።

"ሁለት ወር በመቆየታቸው፤ [ህክምናው] በመዘግየቱ ይመስለኛል ህመሙ እንደገና እየባሰባቸው የመጣው። አቶ ክርስቲያን ረጅም ጊዜ በመዘግየቱ ዓይኔ የማየት [አቅም] ቀንሷል ብሎ ነግሮኛል። . . . ማረሚያ ቤቱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አክብሮ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ባለመውሰዱ ምክንያት አሁን የተፈጠረው ነገር ተከስቷል ማለት ነው" ሲሉ ህክምናቸው መዘግየቱን ዳፋ ገልፀዋል።

ግንቦት 2016 ዓ.ም. የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ፍርድ ቤት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ በፍርድ ቤት መታዘዛቸው ይታወሳል።

የምምክር ቤት አባላቱን ጉዳይ እየተመለከተ ያለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የሕገ መንግሥት እና ፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያለ ሲሆን፤ በሚቀጥለው ሳምንት ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።