'አልፀፀትም' በሚል ርዕስ መጽሐፍ የሚያስመርቀው ጃዋር መሐመድ የሚጸጽተው ነገር የለም?

በወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተጠቃሽ ከሆኑ የዘመኑ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆነው ጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን መጽሐፍ በቀጣይ ሳምንት በኬንያ መዲና ናይሮቢ እንደሚያስመርቅ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ አስታውቋል።
በዚህ ዙሪያ ከቢቢሲ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገው ፖለቲከኛው ጃዋር፣ በአማርኛ 'አልፀፀትም' ኦሮምኛ 'HIN GAABBU' የተሰኘውን መጽሐፍ በእስር ላይ ሳለ እንደጻፈው ተናግሯል።
ጃዋር ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ ከታሰረ በኋላ ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም. መፈታቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሚገኘው ኬንያ ውስጥ ነው።
የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የበርካታ ሰዎች ሕይወት ያለፈበት እና ከፍተኛ ንብረት የወደመበት ሁከት መከሰቱን ተከትሎ ጃዋር እና ሌሎችም ፖለቲከኞች ታስረው እንደነበር አይዘነጋም።
ጀዋር በሚቀጥለው ሳምንት የሚያስመርቀው በሁለት ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፉን እስር ቤት ሳለ ጽፎ ያጠናቀቀው መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
እስር ቤት የተጻፈው መጽሐፍ
ጃዋር አምስት መቶ ገጾች ያሉትን መጽሐፍ እስር ቤት ሆኖ ሲጽፍ፣ ገጽ በገጽ ከእስር ቤት በማስወጣት "የተባበሩ የእስር ቤት ፖሊሶች ነበሩ" ሲል ተናግሯል።
በዚህ ሂደት ወቅት "በውስጥም በውጭም፣ በቅርብም በሩቅም የረዳኝ ሰው ብዙ ነው" ብሏል።
መጀመሪያ አካባቢ የመጽሐፉን ገጾች ከማረሚያ ቤት ማስወጣት "ከባድ ነበር" ሲል የተናገረው ፖለቲከኛው ኋላ ላይ ግን "በእስር ቤት ቆይታ ከሚያስተምረው ዘዴዎች አንዱ ነገሮችን እንዴት ደብቆ ማስገባት እና ማስወጣት እንዲሚቻል ስለሆነ" መጽሐፉን ገጽ በገጽ ማስወጣት እንደተቻለ ተናግሯል።
"መጀመሪያ አካባቢ ወረቀት ስጠይቅ አልሰጡኝም ነበር። ባለሥልጣናቱን ስጠይቅ እምቢ ሲሉኝ የሰማ አንድ ፖሊስ የሆነ ደብተር አስገብቶልኝ እሱ ላይ መጻፍ ጀመርኩ። ወደ ቃሊቲ ከገባን በኋላ ግን [ወረቀት] አልተከለከለም ነበር። የሚከለከው ማስወጣት ብቻ ነበር" ሲል ገልጿል።
ጃዋር እና ሌሎችም ፖለቲከኞች ከእስር ሲለቀቁ የፍትሕ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕገ መንግሥት እና የሽብር ችሎት እየታየ ከነበሩት ተከሳሾች መካከል በነጃዋር ሲራጅ መሐመድ እና በእነ እስክንድር ነጋ ፈንታ መዝገብ ያሉ ተከሳሾች ክሳቸው በአዋጅ ቁጥር 943/2008 መሠረት እንዲነሳ ተደርጓል" ማለቱ ይታወሳል።
እነ ጃዋር ከእስር የተለቀቁት የገና በዓል ቀን የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ድላችንን ዘላቂ ለማድረግ እንድንችል በአሸናፊ ምህረት ግጭቱ የፈጠረውን ውጥረት እናረግባለን" ማለታቸው አይዘነጋም።
ጃዋር እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎችም የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባላት የሆኑ ፖለቲከኞች በእስር ላይ ሳሉ ከ15 ቀናት በላይ የረሃብ አድማ አድርገው እንደነበር ይታወሳል።
መጽሐፉ ለምን አሁን ወጣ? ለምንስ ናይሮቢ ይመረቃል?
መጽሐፉን ለምን አሁን ማውጣት አስፈለገ? መጽሐፉ በናይሮቢ የሚመረቀውስ ለምንድን ነው? በሚል ከቢቢሲ የተጠየቀው ጀዋር "ኢትዮጵያ ለማስመረቅ ፍላጎት ነበረኝ" ብሏል።
ሆኖም ግን "ገዢዎቹ ደስተኛ አልነበሩም። አሁን አገራችን ካለችበት ሁኔታ አንጻር ለመጽሐፍ ብዬ አምቧጓሮ ውስጥ ለመግባት አልፈለግኩም" ሲልም በጎረቤት አገር መዲና መጽሐፉን ለማስመረቅ የወሰነበትን ምክንያት አስረድቷል።
መጽሐፉን አውሮፓ ለማስመረቅም አስቦ የነበረ ቢሆንም "ኬንያ ያለው ማኅበረሰብ ከእኛ መጀመር አለብህ" ብሎ እንደጠየቀው አክሏል።
በቀጣይ "መጽሐፉን ከማስመረቅ ባሻገር፤ አሁን በአገራችን ያለውን ሁኔታ ለመወያየት እና ወደፊት ምን መሠራት አለበት የሚለውንም ሐሳብ ለማቅረብ እንዲሁም ለማዳመጥም" ወደ አውሮፓ አገራት እንደሚጓዝ ተናግሯል።
"ጦርነቱ ትንሽ ጋብ ካለ በኋላ መጽሐፍ ቢቀርብ ሰው በተረጋጋ መንፈስ ለማንበብ ዕድል ይኖረዋል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ነገሮች እየተሻሻሉ ሳይሆን እየተባባሱ ነው የሄዱት። ከዚህ በላይ ብጠብቅም የመሻሻል ተስፋ ይኖረዋል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ስላልቻልኩ አሁን ለማቅረብ ወሰንኩ። መጽሐፉ ተጠናቆ እንዳለ የሚያውቁ ሰዎችም እንዲቀርብ ጫና ሲያደርጉብኝ ነበር። መጨረሻ ላይ ለማቅረብ ወሰንኩ" ሲልም ፖለቲከኛው ተናግሯል።

መጽሐፉ ምን ይዟል?
ጃዋር መሐመድ ወጣት ሳለ ከኢትዮጵያ የወጣው በአውሮፓውያኑ 2003 ላይ ሲንጋፖር ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ነበር።
ከሁለት ዓመት በኋላ አሜሪካ ሄዶ ከስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ 2013 ላይ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ በሰብዓዊ መብት ይዟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን ባመጣው ሕዝባዊ ተቃውሞ ወቅት ከኦሮሞ ወጣቶች 'ቄሮ' ንቅናቄ ጋር በተያያዘ ጃዋር የበለጠ ይታወቃል።
2013 ላይ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) የቴሌቭዥንን ጣቢያ የከፈተ ሲሆን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን መያዝ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመልሶ የኦኤምን ቅርንጫፍን በአዲስ አበባ ከፍቷል።
ኋላ ላይ ከኦኤምኤን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለቆ፤ አሜሪካዊ ዜግነቱን በመተው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በቀጥታ ለመሳተፍ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) ተቀላቅሏል።
ጃዋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በጽኑ ከመደገፍ በጽኑ ወደመተቸት ከተሸጋገሩ ፖለቲከኞች መካለል አንዱ ነው ሊባል ይችላል።
ስለ መጽሐፉ ይዘት እና ማስተላለፍ ስለፈለገው መልዕክት ከቢቢሲ የተጠየቀው ፖለቲከኛው፣ "መጽሐፉ ከትውልዴ አንስቶ እስከ 36 ዓመት ድረስ (እስከ ሁለት ዓመት በፊት ድረስ) ያለውን - በቄሮ ትግል ወቅት የተጓዝንበትን መንገድ፣ የነበሩ ክስተቶችን፣ የተሠሩ ሥራዎችን፣ የነበሩ ፍልሚያዎችን፣ ትግሉ እንዲሳካ የሠራነውን የስትራቴጂ ጥናት፣ ያን ጥናት ወደ ስልት ቀይረን የፈጸምንበትን ሂደት ከትውስታ የጻፍኩት ነው" ሲል አስረድቷል።
መጽሐፉ ስለ ትውልዱ፣ አስተዳደጉ እና ትምህርቱ እንደሚያትት ጠቅሶ "ከእኛ ትውልድ ውስጥ በፖለቲካው ላይ ወጣ ብለን ከምንታየው ውስጥ አንድ ሰው ስለሆንኩ፣ ከትውልዴ ጀምሮ በአስተዳደጌ እና በትምህርት ጉዞዬ ወቅት ያለፍኩበት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በኋላ ላይ ላራመድኩት የፖለቲካ አቋም፣ በኋላ ላይ ለተከተልኩት የፖለቲካ ስትራቴጂ፣ በኋላ ላይ ከሌሎች ጋር አብረን ሠርተን ላሳካነው ትግል የነበረውን አስተዋጽኦ የሚዳስስ ነው" ብሏል።
አያይዞም መጽሐፉ "ሽግግር ከመጣ በኋላ የተሠሩ ስህተቶችን በሙሉ የሚዳስስ ነው" ብሏል።
"ዓለምን እኔ እንዴት እንደማያት እና ያንን ዕይታ ደግሞ እንዳዳብር ሚና የነበራቸውን ከልጅነቴ ጀምሮ ያለፍኩባቸውን ሁኔታዎች ለመረዳት ይረዳል" ሲል ነው መጽሐፉን የገለጸው።
አሁን በአገሪቱ ካለው ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል አንጻር በመጽሐፉ የተቀመጡ የመፍትሄ ሐሳቦች እንዳሉ ለቀረበለት ጥያቄ፣ በቀጣይ መጽሐፉ በዝርዝር የሚዳስሰው ጉዳይ መሆኑን ተናግሯል።
"ፖለቲካ ቋሚ አይደለም። ፖለቲካ ትላንት አለው፤ ዛሬ አለው፤ ነገ አለው። የትላንትን በደንብ ካልተረዳን፣ ትላንት ያለፍንበትን፣ የነበሩ ስኬቶችን እንዴት እንደተሳኩ፣ የነበሩ ስህተቶች እንዴት እንደተሠሩ ካልተረዳን በስተቀር የሚቀጥለውን ለማቃናት ይከብዳል" ብሏል።
መጽሐፉን በእስር ቤት ሲጽፈው በሁለት እንደከፈለው ጠቅሶ፣ "አንደኛው እስካሁን ያለፍኩበትን ያሳያል የወደፊቱ ደግሞ በቀጣይ ዓመት ይወጣል" ብሏል።
"ወደፊት ሕዝባችን እና አገራችን ምን ዓይነት አካሄድ፣ ምን ዓይነት ስትራቴጂና ምን ዓይነት መስተዳድር ብንከተል የተሻለ ማኅበራዊ፣ ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መፍጠር እንችላለን የሚለውን" በዝርዝር በቀጣይ መጽሐፉ እንደሚዳስስ ተናግሯል።
"በዚህኛው መፍሐፍ ወደ ማጠቃለያ ላይ አንድ ምዕራፍ ወደፊት ምን መሆን አለበት የሚል ጨምሬበታለሁ" ብሏል።
መጽሐፉ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ሰዎች ካላቸው የመግዛት አቅም አንጻር በተለያየ ዋጋ ለገበያ እንደሚቀርብም አክሏል።
ጃዋር ምንም አይጸጽተውም?
ጃዋር ባለፉት ዓመታት በተለይም በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱ አመጾችን ከጀርባም፣ ከፊትም ሆኖ በማስተባበር ይታወቃል።
ከአምስት ዓመታት በፊት ጃዋር "በፌደራል ፖሊስ ተመድበውልኝ የነበሩት ጠባቂዎች 'በአስቸኳይ መሣሪያችሁን ይዛችሁ ውጡ' ተባሉ" በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጻፈውን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ እና ንብረት መውደሙ አይዘነጋም።
የፌደራል ፖሊስ በወቅቱ በሰጠው መግለጫ "ጃዋር መሐመድ ለተከታዮቻቸው እና ለደጋፊዎቻቸው ልታሰር ነው፣ ጥቃት ሊደርስብኝ ነው በማለት ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት ነው" ሲል ማስተባበሉ ይታወሳል።
ጃዋር ለመጽሐፉ 'አልፀፀትም' የሚል ርዕስ መስጠቱን በመጥቀስ፣ በፖለቲካ ሕይወትህ የሚጸጽትህ ነገር የለም ወይ? በሚል ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦለታል።
ፖለቲከኛውም "በሕይወቴ ውስጥ ባደረግኩት የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ ብዙ ዋጋ ከፍዬበታለሁ። የግለሰብ ኑሮዬን፣ የቤተሰብ ኑሮዬን መስዋዕት አድርጌበታለሁ። ሆኖም ግን የተሳካ ጉዞ ስለነበረ፣ ያለፍኩበት ሕይወት ከከሰርኩት ያተረፍኩት ይበልጣል። ስለዚህ ልጸጸት አይገባም" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
አያይዞም "በሄድኩበት ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ስህተቶች የሉም ማለት አይደለም። በጣም ብዙ ስህተቶች ነው የሠራሁት። እነዚያ ስህተቶች ግን ያለኝን አላማ ለማሳካት፣ በውስን ሪሶርስ እና በከፍተኛ ጫና ሥር ሳደርጋቸው ስለነበር የተፈጸሙ እንጂ፣ አንድን ሰው ለመጉዳት፣ አንድን ቡድን ለመጉዳት አይደለም። ዓላማውን ለማሳካት ነው" ብሏል።
". . . በስተመጨረሻ ደግሞ ስትራቴጂ የመለወጥን ትግል ስላሳካን፤ ስኬቱ፣ የነበሩ ስህተቶችንም፣ የነበሩ ጉድለቶችንም፣ በእኔም ላይ የደረሱ ጉዳቶችንም የሚያካክስ ነው። ሁሉንም ነገር ዞር ብዬ ሳየው ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዘነ ሆኖ ስላየሁት፣ ለደረሰብኝም ለሁሉም ነገር አይቆጨኝም።"















