የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የመሠረቱት ፋውንዴሽን ይፋ ሊደረግ ነው

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የመሠረቱት "የአዳም ፋውንዴሽን" የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ምሥረታውን ይፋ የሚያደርግበት ሥነ ሥርዓት ሊያከናውን ነው።
አቶ ደመቀ መኮንን በቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመሩት "የአዳም ፋውንዴሽን"፤ "በአፍሪካ መቀንጨርን ለመዋጋት" እንደሚሠራ ተገልጿል።
ለ11 ዓመታት ከቆዩበት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ባለፈው ዓመት ጥር 2016 ዓ.ም. በፈቃዳቸው የተሰናበቱ አቶ ደመቀ ያቋቋሙት ፋውንዴሽኑ ይፋዊ የማብሰሪያ ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወነው ሰኞ ታኅሣሥ 7/2017 ዓ.ም. ነው።
"በአፍሪካ መቀንጨርን መግታት" የሚል መሪ ቃል ያለው ፋውንዴሽኑ፤ ከኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የምዝገባ የምስክር ወረቀት ያገኘው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ እንደሆነ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ውሂብእግዜር ፈረደ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፋውንዴሽኑ መሥራች አቶ ደመቀ መኮንን የድርጅቱ የቦርድ ሊቀመንበር እንደሆኑ ዶ/ር ውሂብእግዜር ገልጸዋል።
በሥነ ምግብ ላይ በመሥራት የሚታወቁት የቀድሞዋ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ፍሬዓለም ሺባባው ደግሞ ምክትል የቦርድ ሊቀመንበር እንደሆኑ አስረድተዋል። የቀድሞ የትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ጥላዬ ጌጤም የፋውንዴሽኑ የቦርድ አባል ናቸው።
የአዳም ፋውንዴሽን በሥነ ምግብ ላይ እንደሚሠራ የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ መቀንጨርን ለመግታት የሚያስችሉ "ባለብዙ ዘርፍ" ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ተቋሙ እንደሚሠራ አመልክትዋል።

የፎቶው ባለመብት, FHL Trading PLC
ፋውንዴሽኑ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው የግብዣ ጥሪ ላይ "ሁሉን አቀፍ፣ መረጃ ላይ የተመሠረተ እና ባለ ብዙ ዘርፍ የሥነ ምግብ ሥርዓትን ተጠቅሞ ውጤታማ የሆኑ ተሞክሮዎችን በማሳደግ በአፍሪካ መቀንጨርን ለመግታት" እንደሚሠራ ተጠቅሷል።
የአዳም ፋውንዴሽን ሊያከናውናቸው የሚያቅዳቸው ፕሮግራሞች ይፋ የሚሆኑት ነገ በአዲስ አበባው ሸራተን አዲስ ሆቴል በሚካሄደው የማብሰሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሆነም አክለዋል።
የፋውንዴሽኑ ድረ ገጽ እንደሚያስረዳው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እንዲሁም የጤና እና የግብርና ሚኒስቴር የፋውዴሽኑ አጋሮች ናቸው።
ድርጅቱ ከአምስት በላይ የገንዘብ እርዳታዎችን ማግኘቱንም ድረ ገፁ ያስረዳል። አዲስ ለተመሠረተው አዳም ፋውንዴሽን የገንዘብ እርዳታ ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል ቢል ኤንድ ጌትስ ፋውንዴሽን አንዱ ነው።
ቢል ኤንድ ጌትስ ፋውንዴሽን በጥቅምት ወር ላይ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ገንዘብ ለየአዳም ፋውንዴሽን ለመስጠት ቃል እንደገባ የቢል ኤንድ ጌትስ ፋውንዴሽን ድረ ገፅ መረጃ ያመለክታል።
ገንዘቡ የሚሰጠው "በኢትዮጵያ ያለውን የምግብ እና የሥነ ምግብ ዋስትናን ለመደገፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ለማጠናከር" ነው ብሏል።












