የ11 ዓመቷ ታዳጊ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ለሦስት ቀናት ከተንሳፈፈች በኋላ በሕይወት ተገኘች

የፎቶው ባለመብት, Compass Collective
የአስራ አንድ ዓመቷ ሴራሊዮናዊት ታዳጊ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ በአየር በተሞላ የጎማ የውጥ ክፍል (ከመነዳሪ) ላይ ተንጠልጥላ ለሦስት ቀን ስትንሳፈፍ ከቆየች በኋላ በነፍስ አድን ሠራተኞች ተገኘች።
ኮምፓስ ኮሌክቲቭ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የነፍስ አድን ሠራተኞች በባሕሩ ላይ ወደ ደረሰ ሌላ ድንገተኛ አደጋ በማቅናት ላይ ሳሉ ነበር የታዳጊዋን የአድኑኝ ጥሪ ሰምተው የደረሱላት።
ስሟ ያልተገለጸው የሴራሊዮናዊቷ ታዳጊ ቱኒዚያ ውስጥ ከሚገኘው ስፋክስ ከተባለው የባሕር ዳርቻ ከ44 ሰዎች ጋር ጉዞ እንደጀመረች ተናግራለች።
እሷ እና ሌሎች ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረችው ጀልባ አደጋ ደርሶባት ከተገለበጠ በኋላ ስትሰጥም ሌሎቹ ስደተኞች በሙሉ ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገምቷል።
በአስቸጋሪው የሜዲትራኒያን ባሕር በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አብዛኞቹ አፍሪካውያን የሆኑ ስደተኞች በየዓመቱ ለሞት ይዳረጋሉ።

የፎቶው ባለመብት, Compass Collective
የነፍስ አድን ቡድኑ ኮምፓስ ኮሌክቲቭ ቃል አቀባይ ካትያ ቴምፕል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ትሮታማር 3 በተባለችው መካከለኛ መርከብ ላይ ሲጓዙ የነበሩት ነፍስ አድን ሠራተኞች ናቸው ታዳጊዋን ያገኗት።
ሴራሊዮናዊቷ ስደተኛ በወቅቱ እንደነገሩ የሚባል የነፍስ አድን ጃኬት ለብሳ እና ሁለት የጎማ የውስጠኛ ክፍል (ከመነዳሪ) ወገቧ ላይ አስራ ባሕሩ ላይ ስትንሳፈፍ የተገኘችው ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ነው።
ታዳጊዋ እንደተናገረችው ከሌሎች ጋር የተሳፈረችባት ከብረት የተሠራችው ጀልባ 3.5 ሜትር ከፍታ ባለው ኃይለኛ ማዕበል በመመታቷ በሰከንዶች ውስጥ መስጠሟን እና እሷ እና ሌሎች ሁለት ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ በውሃ ውስጥ አብረው ቆይተው ተጠፋፍተዋል።
ታዳጊዋን ከባሕር ላይ ያወጧት የነፍስ አድን ሠራተኞች በላምፔዱዛ ደሴት ለሚገኙ የጣሊያን ባለሥልጣናት አሳልፈው ሰጥተዋታል።
የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ከ10 ዓመታት በፊት ጀምሮ በሜዲትራኒያን በኩል የሚያቋርጡ ስደተኞችን መመዝገብ ከጀመረ ወዲህ 30,955 ስደተኞች ባሕሩን ለማቋረጥ ሙከራ ሲያደርጉ ሕይወታቸውን አጥተዋል ወይም የደረሱበት አልታወቀም።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችአር) ባወጣው መረጃ መሠረት እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ ከ63,000 የሚበልጡ ስደተኞችን ጣልያን ተቀብላለች።
ቢሆንም ግን ወደ ጣልያን ባሕር አቋርጠው የሚገኡ ስደተኞች ቁጥር ቀንሷል። ለዚህም ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ የቀኝ ክንፍ መንግሥት በሚያራምደው ጠንካራ ስደተኞችን የተመለከተ ፖሊሲ አንዱ ነው።












