የኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎች ዝውውር መጨመር የፈጠረው የተደራጀ ወንጀል

በአግቦብሎሺ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራ የኤሌክትሪክ ገመዶችን እና ፕላስቲኮችን የሚያቃጥሉ ወንዶች
የምስሉ መግለጫ, እንደገና ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ቁሳቁሶች ተደርገው ወደ በርካታ ድሃ አገራት የሚዘዋወሩ የኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎች የተቃጠሉ አሊያም ጠቃሚ ብረቶች ከወጡ በኋላ የተጣሉ ናቸው።

ከአግቦግብሎሺ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ወፍራም ጭስ ሲወጣ በርቀት ይታያል።

በጋና ዋና ከተማ አክራ ምዕራባዊ አካባቢ ከሚገኘው የቆሻሻ ክምር የሚወጣው አየር መርዛማ ነው። በቀረባችሁት ቁጥር መተንፈስ ይከብዳችኋል፤ ዕይታችሁም ቢሆን ይደበዝዛል።

በዚህ የቆሻሻ ቁልል ዙሪያ ታዲያ በርካታ ወንዶች ቆሻሻ ጭነው ከሚመጡ ተሽከርካሪዎች ላይ የኤሌክትሪክ ገመዶችን ለማራገፍ ሲጠባበቁ ይታያሉ። ሌሎቹ ደግሞ መርዛማ በሆነው የቆሻሻ ክምር ላይ ወጥተው የቴሌቪዥኖች፣ የኮምፒዩተሮች እና የማጠቢያ ማሽኖች ስብርባሪ አካላትን ወደ ታች በማውረድ ያቃጥላሉ።

ወንዶቹ ከተጣሉት የኤሌክትሪክ እና የኤሌክትሮኒክ ቁሳቁሶች እንደ መዳብ እና ወርቅ የመሳሰሉ ጠቃሚ ብረታ ብረቶችን ያወጣሉ።

እነዚህ የተጣሉ የኤሌክትሪክ ምርቶች በአብዛኛው ወደ ጋና የሚገቡት ከሃብታም አገራት ነው።

ዓይኖቹ ቀልተው እና በእንባ ተሞልተው የኤሌክትሪክ ገመዶች እና ፕላስቲኮችን ሲቃጥል የነበረው ወጣት አብዱላ ያኩቡ “ጤንነት እንደማይሰማው” ይናገራል።

“እንደምታየው አየሩ በጣም የተበከለ ነው፤ ግን በየቀኑ እዚህ መሥራት አለብኝ። ጤናችንን እንደሚያውከው ምንም ጥርጥር የለውም” ብሏል።

በአግቦግብሎሺ ያሉ የኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎች
የምስሉ መግለጫ, በአግቦግብሎሺ ያሉ አንዳንድ ደላላዎች የኤሎክትሮኒክ ቆሻሻዎችን እንደገና ጥቅም ላይ ማዋል ስለማይችሉ እንደሚያቃጥሏቸው አሊያም እንደሚጥሏቸው ተናግረዋል።

ሃቢባ አልሃሰን የተባሉ የአራት ልጆች እናትም በቆሻሻ ማቃጠያው አቅራቢያ ጥቅም ላይ የዋሉ የፕላስቲክ ኮዳዎችን ይሰበስባሉ። ከሚቃጠለው ቆሻሻ የሚወጣው መርዛማ ጭስ እርሳቸውንም አልበገራቸውም።

“አንዳንዴ ለመተንፈስ ራሱ በጣም ይከብዳል፤ ደረቴ በጭስ ተሞልቷል፤ ጤንነት አይሰማኝም” ብለዋል።

የሚጣሉ የኤሌክትሮኒክ ቁሳቁሶች ቆሻሻ (ኢ ዌስት) በዓለማችን እየጨመረ የመጣ ቆሻሻ ነው። እንደ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ከሆነ የእነዚህ ቁሳቁሶች ቆሻሻ መጠን እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 62 ሚሊዮን ቶን የደረሰ ሲሆን ይህም በ2010 ከነበረው 82 በመቶ ጨምሯል።

ለእነዚህ ቆሻሻዎች መጨመር ዋነኛው ምክንያት ማኅበረሰቡ ከዘመናዊ ስልኮች እና ኮምፒዩተሮች ጀምሮ እንደ ቴሌቪዥን እና ተፈላጊነታቸው እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ መሣሪያ የተገጠመላቸው የቤት መኪናዎችን ጭምር የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶችን የመጠቀም ባህሉ በመጨመሩ ነው።

ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ሪፖርት ባወጣው ሪፖርት ወደ አገሪቷ የሚገቡ ዘመናዊ ስልኮች ቁጥር በ2010 ከነበረው በእጥፍ ጨምሮ በ2023 ወደ 1.2 ቢሊዮን ደርሷል።

በድሮን የተነሳ የአግቦግብሎሺ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራ
የምስሉ መግለጫ, ጠቃሚ ብራታ ብረቶችን ለማግኘት ሲባል የሚቃጠሉ የኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎች በፕላስቲክ ከተሰራው አካላቸው መርዛማ ጭስ ይወጣል።

በተደጋጋሚ የሚያዙ ቁሳቁሶች

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ተመድ እንዳለው በዓለም ከሚጣሉ የኤሌክትሮኒክ ቁሳቁሶች እንደገና አገልግሎት እንዲሰጡ (ሪሳይክል) የሚደረጉት 15 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው። በመሆኑም ኃላፊነት የማይሰማቸው ኩባንያዎች ባገኙት ቦታ ሁሉ ቆሻሻቸውን ያራግፋሉ። ይህንን ለማድረግም በአብዛኛው ቆሻሻዎቹን ከአገር የሚያስወጡላቸውን ደላሎች ይጠቀማሉ።

ምክንያቱም እንደዚህ ያሉ ቆሻሻዎች በውስጣቸው በያዙት መርዛማ ኬሚካሎች፣ ብረታ ብረቶች፣ ፕላስቲኮች እንዲሁም በቀላሉ በማይለዩ እና ፈርሰው የማይሠሩ ንጥረ ነገሮችን ጨምሮ ውስብስብ ሥሪት ስላላቸው እንደገና ጥቅም ላይ ማዋል አስቸጋሪ ነው።

ያደጉት አገራትም ቢሆኑ እንደዚህ ያሉ የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎችን የሚያስተዳድሩበት መሠረተ ልማት የላቸውም።

የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች እንደሚሉትም ካደጉ አገራት በፍጥነት በማደግ ላይ ወዳሉ አገራት የሚደረገው የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች ዝውውር ጨምሯል።

አሁን ላይ በድንበር እና በወደብ ባለሥልጣናት በብዛት ከሚያዙ ቁሳቁሶች መካከልም አንዱ ሆኗል።

በዓለም ላይ ከሚያዙ ስድስት ሁሉም ዓይነት ቆሻሻዎች መካከል አንዱ የኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ መሆኑን የዓለም ጉምሩክ ድርጅት ገልጿል።

በጣልያን ኔፕልስ ወደብ ባለሥልጣናት የቆሻሻ አዘዋዋሪዎች በሐሰተኛ ማስረጃ እና በድብቅ እንዴት ለማጓጓዝ እንደሚሞክሩ ለቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት ከሚይዟቸው ቁሳቁሶች መካከል 30 በመቶ የሚሆነው የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች መሆናቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

ባለሥልጣናቱ ለቢቢሲ እንደገለጹት አንድ ወደ አፍሪካ ሊጓዝ የነበረ መኪና የጫነ ኮንቴኔር ሲከፈት በውስጡ የመኪና አካላት እና የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች በውስጡ ታጭቀው የነበረ ሲሆን፣ የተወሰኑት የነዳጅ ዘይት ያፈሱ ነበር።

ከአውሮፓ የወደብ ባለሥልጣናት ጋር በትብብር በሚሠራው የአውሮፓው ፀረ ማጭበርበር ቢሮ ውስጥ መርማሪ የሆኑት ሉዊጂ ጋሩቶ ክስተቱን አስመልክተው ሲናገሩ “የራስህን ቁሳቁስ መቼስ እንደዚህ አትጭንም፤ አብዛኛው የሚጣል ቆሻሻ ነው ማለት ነው” ብለዋል።

በኔፕልስ የወደብ ባለሥልጣናት የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ፣የተሽከርካሪ አካላት እና አገልግሎታቸው ያበቃ ተሽከርካሪዎችን የጫነ ኮንቴኔር በፍተሻ ይዘዋል።
የምስሉ መግለጫ, በአውሮፓ የወደብ ባለሥልጣናት እንደሚሉት አዘዋዋሪዎች ቆሻሻዎቹን ለማጓጓዝ ሲሉ ይፈጯቸዋል አሊያም ከሌላ የፕላስቲክ ቁርጥራጮች ጋር ይደባልቋቸዋል።

የተራቀቀው የዝውውር ስልት

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ ባለሥልጣናት የሚዘዋወሩ የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ይናገራሉ።

በፌሊክስቶው ወደብ የዩኬ አካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ የሆኑት ቤን ራይደር እንዳሉት ቆሻሻዎች ብዙውን ጊዜ በስህተት ‘እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶች’ ተብለው ፈቃድ ይሰጣቸዋል። ሆኖም እውነታው ሌላ ነው።

“ውድ የሆኑ ብረታ ብረቶችን ለማውጣት ከተሰባበሩ በኋላ መዳረሻቸው ላይ ሲደርሱ [እንደ ጋና ባሉ አገራት] በሕገ ወጥ መንገድ ይቃጠላሉ” ብለዋል።

የቆሻሻ አዘዋዋሪዎቹም እነዚህ ቁሳቁሶችን ለመደበቅ ሲሉ ይፈጯቸውና ወደ ሌላ ቦታ ለማጓጓዝ የሚረዳ የፈቃድ ወረቀት ለማግኘት ከሌሎች የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ጋር ይደባልቋቸዋል ብለዋል ቃል አቀባዩ።

በዓለም የጉምሩክ ድርጅት ቀደም ብሎ የወጣ ሪፖርት እንደሚያመለክተውም የሚጓጓዙ አገልግሎታቸው ያበቃ ሞተርሳይክሎች በ700 በመቶ ጨምረዋል።

ሆኖም እነዚህ የሚያዙ እና ሪፖርት የሚደረጉ ክስተቶች ጥቂቶቹ እንደሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ምንም እንኳን ከአደጉት አገራት የሚጓጓዙ የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎችን የሚከታተል ዓለም አቀፍ ጥናት ባይኖርም፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የ’ኢዌስት’ ሪፖርት የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራትም የእነዚህ ቆሻሻዎች ማራገፊያ መሆናቸውን ያሳያሉ።

የተወሰኑት እነዚህ አገራት ከፍተኛ ቁጥጥር እያደረጉ በመሆናቸው አብዛኛዎቹ ኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች ወደ አፍሪካ እንደሚላኩ የድርጅቱ መርማሪዎች እና ተሟጋቾች ይናገራሉ።

በማሌዢያ እየተገባደደ ባለፈው ዓመት ከግንቦት እስከ ሰኔ 106 ኮንቴይኔር አደገኛ የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች በባለሥልጣናት መያዛቸውን የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ምሥራቅ እስያ እና ፓስፊክ የአደገኛ እፅ እና ወንጀል ጉዳዮች ቀጠናዊ ተወካይ የሆኑት ማሱድ ካሪሚፖር ተናግረዋል።

ሆኖም አዘዋዋሪዎች ብዙውን ጊዜ በሚጠቀሙት አዲስ የማዘዋወሪያ ስልት ባለሥልጣናትን ስለሚያታልሉ መንግሥት ቶሎ እንደማይዛቸው የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች ይገልጻሉ።

“መርከቦች እንደ የኤሌክትሮኒክስ ያሉ አደገኛ ቆሻሻዎችን በተለመደው መዳረሻቸው በቀላሉ ማራገፍ አይችሉም። በመሆኑም በባሕር ላይ እያሉ መብራታቸውን ያጠፋሉ። በዚህም ምክንያት አይለዩም” ብለዋል ካሪማፖር ።

“በመሆኑም የተደራጀ የወንጀል ድርጊት የቢዝነስ ዘዴ ሆኖ ሕገ ወጥ ጭነት ባሕር ላይ ይራገፋል” የሚሉት ካሪሚፖር፣ ከዚህ ዓለም አቀፍ የወንጀል ድርጊት የሚያተርፉ በርካታ ቡድኖች እና አገራት እንዳሉ ይናገራሉ።

በአግቦግብሎሺ የቆሻሻ መጣያ ሠራተኛ
የምስሉ መግለጫ, አሁን ላይ የኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎች በዓለም ላይ በጉምሩክ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚያዙ ቆሻሻ ቁሳቁሶች ሆነዋል።

በጣም አስጊ የሆኑ ኬሚካሎች

የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ እንዳወጣው ሪፖርት ከሆነ የፕላስቲክ እና ብረታ ብረት የኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎች (ኢዌስት) ሲቃጠሉ ወይም ሲጣሉ በሰው ጤና እና በአካባቢ ላይ አሉታዊ ጉዳት ያስከትላሉ።

ድርጅቱ እንዳለው በርካታ የእነዚህ ቆሻሻዎች ተቀባይ አገራት መደበኛ ያልሆነ ኢዌስትን እንደገና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እያዩ ነው። እነዚህ ቆሻሻዎች እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረገው ግን ያለምንም የግል ጤና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ ያለ ትክክለኛ መሠረተ ልማት ሥራውን በሚሠሩ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ባልሠለጠኑ ሰዎች ሲሆን፣ እንደ ሊድ ላሉ መርዛማ ኬሚካሎች ይጋለጣሉ።

ዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅት እና የዓለም ጤና ድርጅት የወዳደቁ ቁሳቁሶችን እንደገና ጥቅም ላይ ለማዋል በሚሠሩ መደበኛ ያልሆኑ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች እና ሕጻናት ሠራተኞች በእርግዝና ወቅት እንዲሁም ሕጻናት ለአዕምሮ ዕድገት እና ለሌላ የጤና እክል እንደሚጋለጡ ገልጸዋል።

የአደገኛ ቆሻሻዎች አወጋገድ ስምምነት የሆነው ‘ባዜል ኮንቬንሽን’ ከመጪው የአውሮፓውያኑ ዓመት 2025 መጀመሪያ አንስቶ ላኪዎች ሁሉንም ቆሻሻዎችን ማሳወቅ እና ከተቀባይ አገራት ፈቃድ ማግኘት እንደሚጠበቅባቸው ይጠይቃል።

ይህም አዘዋዋሪዎች ቆሻሻዎችን በዓለም ዙሪያ ለማጓጓዝ የሚጠቀሙበትን የተወሰኑ ክፍተቶችን እንደሚሞላ መርማሪዎች ተስፋ አድርገዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች እና ፕላስቲኮች በጎርፍ እና ወንዞች ታጥበው ወደ ባሕር ይገባሉ።
የምስሉ መግለጫ, የኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎች እና ፕላስቲኮች በጎርፍ እና ወንዞች ተጠርገው ወደ ባሕር ከገቡ በኋላ በጊዜ ሒደት ዳርቻ ላይ ይከማቻሉ።

ሆኖም ከፍተኛ የኢዌስት ላኪ የሆነችውን እና ስምምነቱን ያልፈረመችውን አሜሪካንን ጨምሮ የተወሰኑ አገራት አሉ። ይህም የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች ዝውውር ለመጨመሩ ምክንያት መሆኑን ተሟጋቾች ይናገራሉ።

የኢዌስትን ጨምሮ መርዛማ የሆኑ ቆሻሻዎችን ንግድ ለማስቆም የሚሠራው የባዜል አክሽን ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር ጂም ፓኬት “በአሜሪካ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ስንጀምር በሜክሲኮ ድንበር ላይ በርካታ የማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ነበሯት” ብለዋል።

በጋና አግቦግብሎሼ ያለው ሁኔታም ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው።

ሃቢባ እንደምትለው ቆሻሻዎችን ሰብስባ ከምታገኘው ገንዘብ ግማሹን የምታጠፋው በቆሻሻ ሥፍራው በመሥራቷ ምክንያት ለሚያጋጥማት ህመም መድኃኒት ለመግዛት ነው።

“ሆኖም አሁንም እዚሁ ነው ያለሁት። ምክንያቱም ይህ የራሴን እና የቤተሰቤን ሕይወት ማቆያ ገንዘብ የማገኝበት ሥራ ነው” ብላለች።

የጋና ገቢዎች ባለሥልጣን እና የአካባቢ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ አስተያያት እንዲሰጡ በቢቢሲ ለቀረበላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።