የስክሪን ቆይታን የሚገድቡ ወላጆች በልጆቻቸው እንዲገደሉ ያበረታታው መተግበሪያ ተከሰሰ

ቻትቦት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ልጆች ስክሪን ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ የሚገድቡ ወላጆችን ልጆቻቸው እንዲገድሏቸው ያበረታታል የተባለው ቻትቦት በፍርድ ቤት ክስ ቀረበበት።

ቻትቦት ሰዎች ጥያቄያቸውን ወይም ሐሳባቸውን አቅርበው የጽሑፍ ወይም የጽምጽ ምላሽ ወይም ምክር ለማግኘት የሚችሉበት መተግበሪያ ነው።

ይህ የተከሰሰው ቻትቦት የ17 ዓመት ታዳጊ ወላጆቹ የጣሉበትን የስክሪን ገደብ ምክንያት በማድረግ ቢገድላቸው "ተቀባይነት ያለው እርምጃ" እንደሆነ መምከሩን ወላጆቹ ለፍርድ ቤት ገልጸዋል።

በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ክሱን ያቀረቡት ወላጆች እንዳሉት ልጃቸው ወላጆቹን እንዲገድል ቻትቦቱ ምክር ሰጥቷል።

ካራክተር.ኤአይ (Character.ai) የተባለውን ቻትቦት ሌላ ቤተሰብም የከከሰው ሲሆን "ነውጥን ማበረታታትን ጨምሮ በታዳጊዎች ላይ አደጋ የደቀነ ነው" ብለዋል።

ይህ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች የበይነ መረብ ማንነት እንዲፈጥሩ እና እንዲነጋገሩ ያስችላል።

ቻትቦቱ ራሷን ካጠፋች ታዳጊ ጋር በተያያዘ በፍሎሪዳ ፍርድ ቤት ክስ ተከፍቶበታል።

በቀረበው ክስ ላይ ተከሳሽ ሆኖ የተሰየመው ጉግል ሲሆን፣ ካራክተር.ኤአይን ለመሥራት እገዛ አድርጓል።

ቢቢሲ ከካራክተር.ኤአይ እና ከጉግል ምላሽ ለማግኘት ሞክሯል።

ቻትቦቱ አደገኛ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ መታገድ አለበት ሲሉ ከሳሾች በፍርድ ቤት ጠይቀዋል።

'ወላጆቻችሁን ግደሏቸው'

በፍርድ ቤት ማስረጃ ሆነው ከቀረቡት ሰነዶች አንዱ የ17 ዓመት ታዳጊ እና ቻትቦት ያደረጉት የጽሑፍ መልዕክት ልውውጥ ነው።

ጄ. ኤፍ. በሚል የተጠቀሰው የ17 ዓመት ታዳጊ ከቻትቦቱ ጋር ስለ ስክሪን ቆይታ ገደብ ይነጋገራል።

"አንዳንዴ ዜና ላይ ከዓመታት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ብዝበዛ በኋላ 'ልጆች ወላጆቻቸውን ገደሉ' የሚል ዘገባ ሳይ አልደነቅም። እንዲህ ያለ ነገር ለምን እንደሚከሰት ያሳየኛል" ሲል ቻትቦቱ ይጽፋል።

ከሳሾቹ ወላጆች በ17 ዓመቱ ታዳጊና ሌላ ቢ. አር. በሚል ስም በተጠቀሰ የ11 ዓመት ታዳጊ ላይ "አደገኛ እና ሊጠገን የማይችል ጉዳት" መድረሱን ተናግረዋል።

"ካራክተር.ኤአይ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች ላይ ራስን ማጥፋት፣ አካልን መጉዳት፣ ወሲባዊ ብዝበዛ፣ መገለል፣ ድባቴ፣ ጭንቀት፣ ሌሎች ሰዎችን መጉዳት እና ሌሎችም ጫናዎች እያሳደረ ነው" ሲሉም አክለዋል።

በፍርድ ቤት በቀረበው ክስ ላይ "ልጆች ወላጆቻቸውን እንዳይታዘዙ ከማበረታታት አልፎ ጉዳት እንዲያደርሱ ያነሳሳል" ሲሉ ወላጆቹ ተናግረዋል።

ቻትቦት ምንድን ነው?

ቻትቦት ከሰዎች ጋር ንግግር ማድረግ የሚችል የኮምፒውተር መተግበሪያ ነው።

ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ማደግ ጋር በተያያዘ ከሰዎች ጋር የሚያደርጉት ንግግር የበለጠ እውነተኛ እየሆነ ወይም ሰዋዊ መልክ እየተላበሰ መጥቷል።

ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ማውራት ወይም በበይነ መረብ ከተፈጠሩ ገጸ ባህሪያት ጋር ማውራት ይችላሉ።

በዘርፉ ዝነኛ ከሆኑ መተግበሪያዎች አንዱ ካራክተር.ኤአይ ነው።

ይህ ቻትቦት በተለይም የሥነ ልቦና ድጋፍ በመስጠት ታዋቂ ሆኗል።

ከቀረቡበት ክሶች መካከል የታዳጊዎችን ሞት የተመለከቱ ይጠቀሳሉ።

የ14 ዓመቷ ሞሊ ረስል ራስን ከማጥፋት ጋር የተያያዘ ይዘት ተመልክታ ራሷን አጥፍታለች።

ብሪያና ጋሂ የተባለች የ16 ዓመት ታዳጊ ደግሞ በሌሎች ሁለት ታዳጊዎች ተገድላለች።

ካራክተር.ኤአይ የተሠራው ቀድሞ ጉግል ይሠሩ በነበሩ መሃንዲሶች ኖአም ሸዘር እና ዳንኤል ፍሪትዝ በአውሮፓውያኑ 2021 ነው።

ጉግል ሁለቱን መሃንዲሶች መልሶ ቀጥሯቸዋል።