በሶማሊያ እና በጁባላንድ ኃይሎች መካከል ውጊያ ተካሄደ

ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት ማቋረጡን ባስታወቀው የጁባላንድ ኃይሎች እና በሶማሊያ ወታደሮች መካከል ውጊያ መካሄዱን ሁለቱም ወገኖች አስታወቁ።
ዛሬ ረቡዕ ታኅሣሥ 2/2017 ዓ. ም. ማለዳ ላይ በሁለቱ ኃይሎች መካከል የተካሄደውን ውጊያ በተመለከተ የሶማሊያ መንግሥት የመከላከያ ሚኒስቴር እና የራስ ገዟ ጁባላንድ አስተዳደር አንዳቸው ሌላኛውን ጠብ ጫሪ በማለት ከሰዋል።
የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ራስካምቦኒ ውስጥ በጁባላንድ ኃይሎች የተሰነዘረበትን ጥቃት መክቶ መመለሱን አመልክቷል። የጁባላንድ አስተዳደርም በበኩሉ የመንግሥት ኃይሎች የክልሉ ታጣቂዎች ይዞታ ላይ ጥቃት መፈጸማቸወቅን ገልጿል።
ነገር ግን ከሁለቱም በኩል ግጭቱ መከሰቱን እና አንደኛው ወገን ሌላኛውን ጥቃት በመፈጸም ተጠያቂ ከማድረግ ባሻገር በውጊያው ስለደረሰ ጉዳት ያሉት ነገር የለም።
ምንጮች በሶማሊያ መንግሥት እና በክልላዊው ጁባላንድ አስተዳደር ኃይሎች መካከል የተካሄደው ውጊያ ከባድ እንደነበር ገልጸዋል።
በሶማሊያ የነበረውን የውክልና ምርጫ ሕግ ማዕከላዊው መንግሥት እንዲቀየር መወሰኑን ተከትሎ የጁባላንድ መሪዎች እና ፖለቲከኞች ተቃውሟቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ነበር በሁለቱ ወገኖች መካከል አለመግባባት የተከሰተው።
ከሳምንታት በፊት ደግሞ የማዕከላዊውን መንግሥት ውሳኔ በመቃረን ጁባላንድ ምርጫ አካሂዳ አሕመድ ማደቤ ድጋሚ ከተመረጡ በኋላ ግዛቲቱ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን ማስታወቋ ይታወሳል።
የሶማሊያ መንግሥት የክልሉን ውሰኔ ሕገወ ጥ በማለት ወታደሮቹን ወደ ራስካምቦኒ ካሰማራ በኋላ የጁባላንድ አስተዳደሮች ደግሞ ኃይሎቻቸውን ወደ ስፍራው በመላክ ፍጥቻ ውስጥ ከቆዩ በኋላ ነው አሁን ግጭቱ የተከሰተው።
የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስቴር የጁባላንድ ኃይሎች "በአሕመድ ማዶቤ ትዕዛዝ" በአገሪቱ ሠራዊት እና በአካባቢው ሚሊሻዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ሲል ከሷል።
ለጥቃቱ የጁባላንድ ኃይሎች ከአልሻባብ ጋር ትብብር ማድረጋቸውን የገለጸው የመከላከያ ሚኒስቴሩ፣ ያለ አል ሻባብ ትብብር የግዛቲቱ ኃይሎች የሶማሊያ ሠራዊት ከሰፈረበት ካምፕ ጋር ሊደርሱ አይቸሉም ሲል ከሷል።
ይህ ድርጊትም የአገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል እና የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚክድ ብርቱ ወንጀል መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ሁሉ "ከባድ ሕጋዊ ቅጣት" ይጠብቃቸዋል ሲል ዝቷል።
በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት እና በጁባላንድ መሪዎች መካከል ያለው አለመግባባት እየተካረረ ባለበት ጊዜ ከሳምንት በፊት የሶማሊያ መንግሥት በአሕመድ ማዶቤ ላይ በአገር ክህደት የእስር ትዕዛዝ ሲያወጣ፣ የጁባላንድ ባለሥልጣናትም በሶማሊያ መሪ ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፈዋል።
በተጨማሪም የጁባላንድ መሪዎች የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ሕገ መንግሥቱን እየጣሰ እንዲሁም የሕዝቡን አንድነት እያናጋ ነው በሚል ከሰው ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ያላቸውን ግንኙነትም ሆነ ትብብር ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል።












