የቡና ዋጋ በዓለም ገበያ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጭማሪ አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock
በመላው ዓለም ተወዳጅ የሆነው የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ የምርት ግብይት መድረኮች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተዘገበ።
ኢትዮጵያ እና ሌሎች ጥቂት አገራት የሚያመርቱት ተፈላጊው የአረቢካ ቡና ዓይነት በዓለም ገበያ ላይ ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
ማክሰኞ ዕለት በዋለው ገበያ ተወዳጁ እና በዓለም በብዛት የሚመረተው የአረቢካ ቡና ዝርያ ዋጋ በኪሎ በዚህ ዓመት ከ80 በመቶ በላይ ማሻቀቡ ተዘግቧል። በተመሳሳይ ሌላኛው የቡና ዝርያ ሮቡስታ ዋጋም በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ አሳይቷል።
የአሜሪካ የእርሻ መሥሪያ ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ከፍተኛውን የአረቢካ ቡና ያመረቱት አገራት ብራዚል፣ ኮሎምቢያ እና ኢትዮጵያ ናቸው።
ይህ የዋጋ ጭማሪ የታየው የቡና ነጋዴዎች በዓለም ሁለቱ ታላላቅ የቡና አምራች የሆኑት ብራዚል እና ቬትናም በመጥፎ የአየር ሁኔታ በመመታታቸው እና የቡና ጠጪዎች ቁጥር እያደገ ስለሚሄድ የምርቱ አቅርቦት ይቀንሳል ብለው በመስጋታቸው ነው።
በዚህም ምክንያት በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት ታዋቂዎቹ የቡና ምርት ኩባንያዎች በአቅርቦታቸው ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ እያሰቡ መሆናቸውን አንድ የቡና ባለሙያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዋና ዋና ቡናን በመቁላት እና በማዘጋጀት ሥራ ላይ የተሰማሩት ተቋማት ደንበኞቻቸውን ለመያዝ እና የገበያ ድርሻቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የዋጋ ጭማሪውን እራሳቸው ሲሸፍኑ ቢቆዩም፣ ይህ ሊለወጥ የተቃረበ ይመስላል ሲሉ የቱዋን ሎክ የሸቀጦች ንግድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቪንህ ንጉየን ተናግረዋል።
"የተለያዩ ታዋቂ የቡና አቅራቢ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም የነበሩ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪዎችን ሲሸፍኑ ቢቆዩም አሁን ዋጋ ለመጨመር ከጫፍ ደርሰዋል፤ በ2025 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ እያሰቡ ነው።"
ባለፈው ኅዳር ወር ለባለሃብቶች በተካሄደ ዝግጅት ላይ አንድ ከፍተኛ የኔስሌ ሥራ አስፈፃሚ የቡና ኢንዱስትሪው "ፈታኝ ጊዜ" እያጋጠመው ነው በማለት፣ ኩባንያቸው በዋጋ እና በማሸጊያው መጠን ላይ ማስተካከያ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኔስሌ የቡና ምርቶች ኃላፊ ዴቪድ ሬኒ "በቡና ላይ የሚያጋጥመው የዋጋ ጭማሪ የማይነካን አይደለንም፤ በጣም ቅርብ ነን" ሲሉ የቡና ዋጋ መናር ተጽእኖው እንደሚመለከታቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የቡና ዋጋ የተመዘገበበት ወቅት የአውሮፓውያኑ 1977 ታይቶ የማይታወቅ በረዶ የብራዚልን የቡና ምርት ባወደመበት ጊዜ ነበር።
ከዋጋ ጭማሪ አንጻር "በብራዚል ውስጥ በ2025 የቡና ምርት ላይ ያለው ስጋት ዋነኛው ሰበብ" የሚሉት የሳክሶ ባንክ የሸቀጦች ስትራቴጂ ኃላፊ ኦሌ ሃንሰን ናቸው።
ብራዚል "ባለፈው ነሐሴ እና መስከረም በ70 ዓመታት ውስጥ የከፋ ነው የተባለ ድርቅ አጋጥሟታል፣ በመቀጠል ደግሞ በጥቅምት ወር ከባድ ዝናብ በመጣሉ ምርቱን ሊያወድመው ይችላል የሚለውን ስጋት አበርትቶታል።"
በአብዛኛው አረቢካ ቡናን የምታመርተው የብራዚል የቡና እርሻ ብቻ አይደለም በመጥፎ የአየር ጠባይ የተመታው።
ሌላኛውን የቡና ዓይነት ሮቡስታን በከፍተኛ መጠን የምታመርተው የቬትናም የቡና እርሻዎችም በድርቅ እና በከባድ ዝናብ ጉዳት አድርሶባቸዋል።
ቡና ከድፍድፍ ነዳጅ በመቀጠል በዓለም ላይ በከፍተኛ መጠን ለግብይት የሚቀርብ ሁለተኛው ሸቀጥ ሲሆን፣ ታዋቂነቱም እየጨመረ ነው። ለምሳሌ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በቻይና ያለው የቡና ፍጆታ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።
የኤስ ኤንድ ፒ ግሎባል ኮሞዲቲ ኢንሳይትስ የቡና ዋጋ ተንታኝ ፌርናንዳ ኦካዳ እንደሚሉት "በቡና አምራቾች እና በአቀናባሪዎች የተያዙ ምርቶች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኙበት ጊዜ ለሸቀጦች ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ይሆናል" በማለት የዋጋ ጭማሪው አይቀሬ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም "የቡና ዋጋ መጨመር ለተወሰነ ጊዜ እንደሚቀጥል ይጠበቃል" ስትል ተናግረዋል።












