በመድኃኒት እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ላይ ተአምር ይፈጥራል የተባለው የጉግል ፈጠራ

ዊሎው የተባለው አዲስ ቺፕ

የፎቶው ባለመብት, Google

የምስሉ መግለጫ, ዊሎው የተባለው አዲስ ቺፕ

አሁን ላይ ካሉ ኮምፒውተሮች እጅግ ፈጣኑ የሚባለው ኮምፒውተር አንድን ችግር ለመፍታት ወይም የሒሳብ ስሌትን ለማጠናቀቅ አሥር ስፒትልዮን ዓመት የሚወስድበት ቢሆን፣ ይህንኑ ስሌት በአምስት ደቂቃ ውስጥ የሚሠራ አዲስ ቺፕ መፍጠር መቻሉን ጉግል ገልጿል።

አሥር ስፒትልዮን ዓመት በቁጥር ሲጻፍ ከአስር በኋላ ሃያ አራት ዜሮዎችን የሚያስከትል ቁጥር ነው። ይህም ማለት 10,000,000,000,000,000,000,000,000 ይሆናል።

አንድን ስሌት ለማጠናቀቅ ፈጣል የሚባለው ኮምፒውተር ይሄን ሁሉ ዓመታት ቢወስድበትም የጉግል አዲስ ፈጠራ ግን ስሌቱን በአምስት ደቂቃ ውስጥ እንደሚጨርሰው ተነግሯል።

ጉግል የሠራው ቺፕ በኳንተም ኮምፒውቲንግ ዘርፍ አዲስ ፈጠራ ነው።

ለዚህ ቺፕ 'ዊሎው' የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

እጅግ አስደናቂ ፍጥነት ያለው እና አስገራሚ የሆነ ቺፕ ነው።

"በላቀ ደረጃ ለሚሠራ ኳንተም ኮምፒውተር መንገድ የሚከፍት አስደናቂ ፈጠራ" በሚል ነው የተገለጸው።

ይህ ፈጠራ አሁን ገና በሙከራ ደረጃ ነው የሚገኘው።

ውስብስብ ስሌቶችን መሥራት የሚችል ኳንተም ኮምፒውተር ለመሥራት አሁን ዓመታት ይቀራሉ። በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚጠይቅም ሥራ ነው።

ኳንተም ኮምፒውተር

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኳንተም ኮምፒውተር ከስልክ ወይም ከላፕቶፕ በተለየ መንገድ ነው የሚሠራው።

ኳንተም ማለት ከማንኛውም ቁስ አካል አንሶ የሚገኝ ወይም ቅንጣት ሊባል የሚችል ነው።

ኳንተም ሜካኒክስን በመጠቀም አሁን ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉ ኮምፒውተሮች እጅግ በፈጠነ ሁኔታ ማንኛውንም ነገር ማከናወን ላይ ምርምሮች እና ሙከራዎች ይደረጋሉ።

ይህ ዘዴ በአዲሱ ግኝት ሲቀላጠፍ ለምሳሌ አዲስ መድኃኒት የመሥራት ሂደት በከፍተኛ ሁኔታ ይፈጥናል።

በሌላ በኩል ደግሞ በውስብስብ ሁኔታ የተቆለፉ ወይም ኢንክሪፕቲድ የሆኑ ምሥጢራዊ መረጃዎችን በቀላሉ ለማለፍ ሊውል ይችላል የሚል ስጋትም አለ።

በአውሮፓውያኑ የካቲት 2024 አፕል በአይሜሴጅ የሚላኩ መልዕክቶችን ምሥጢራዊነት ለመጠበቅ ኳንተምን እንደሚጠቀም አስታውቆ ነበር።

ለወደፊት የኳንተም ኮምፒውተሮች የሚኖራቸውን ኃያልነት ለመቅደም ያለመ ውሳኔ ተብሏል።

ዊሎው የተባለውን አዲስ ቺፕ የፈጠረውን የጉግልን የኳንተም ቤተ ሙከራ የሚመራው ኸርተሙት ኔቫን፣ ፈጠራው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ይናገራል።

ዊሎው ምን ያህል ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ለቢቢሲ ቢገልጽም፣ ዝርዝር ጥቅሞቹን ከመጥቀስ ግን ተቆጥቧል።

ገበያ ላይ የሚሸጡ ቺፖች ዕውን የሚሆኑት በምዕተ ዓመቱ መጨረሻ እንደሚሆን ያስረዳል።

"ለምሳሌ በኒውክሌር ማብላያ ወይም በመድኃኒት ምርት ውስጥ ጥቅም ይሰጣሉ። የተሻሉ የመኪና ባትሪዎች ለማምረትም ይውላሉ" ይላል።

ባለሙያው እንደሚለው ዊሎው "እስካሁን ከተገነቡ የኳንተም ማብላያዎች እጅግ የተሻሻለው" ነው።

በሱሪይ ዩኒቨርስቲ የኮምፒውቲንግ ባለሙያ ፕሮፌሰር አለን ውድዋርድ ግን የተለየ ሐሳብ አላቸው።

አሁን ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉትን ኮምፒውተሮች "መተካት አይችሉም" ሲሉ ያስረዳሉ።

ዊሎው የሚኖረው ሚና በተጋነነ መንገድ እንዳይታይ ያሳስባሉ።

"ሁለት የማይነጻጸሩ ነገሮችን ማወዳደር ይከብዳል" ይላሉ።

ጉግል በበኩሉ ለኳንተም ኮምፒውተር የሚሆን የሒሳብ ስሌት አዘጋጅቶ አዲሱን ፈጠራውን ሞክሯል።

"ይህ ማለት ግን አሁን ካሉ ኮምፒውተሮች አጠቃላይ አሠራር አንጻር አዲሱን ቺፕ ፈጣን ያደርገዋል ማለት አይደለም" ሲሉ ፕሮፌሰር አለን ውድዋርድ ይናገራሉ።

ሆኖም ግን ዊሎው አስደናቂ ለውጥ ያሳየ ፈጠራ መሆኑን ይስማሙበታል።

በቺፑ ላይ የሚኖረው መረጃ መጠን በጨመረ ቁጥር ሊፈጠር የሚችለውን ስህተት ለማስወገድ እየሠሩ እንደሆነ የጉግል ተመራማሪዎች ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር አለን ውድዋርድ እንደሚሉት ይህ ፈጠራ "ለ30 ዓመታት ምርምር ሲደረግበት ለነበረ ጥያቄ" ምላሽ የሰጠ ነው።

"ለምሳሌ አንድ ሞተር ያለው አውሮፕላን ቢኖር አውሮፕላኑ ይሠራል። ሁለት ሞተር ሲኖረው ደግሞ አውሮፕላኑ የተሻለ ደኅንነቱ ይጠበቃል። አራት ሞተር ሲኖረው ደግሞ በጣም አስተማማኝ ይሆናል" ይላሉ።

በከፍተኛ መጠን የሚሠሩ ኳንተም ኮምፒውተሮችን በመገንባት ሂደት ውስጥ ፈታኝ የሚሆነው የሚፈጠረው ስህተት ነው።

ሆኖም ግን እየታየው ያለው ዕድገት "የተሻለ አገልግሎት የሚሰጡ ኳንተም ኮምፒውተሮች እንዲገነቡ" መንገድ ይከፍታል ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ጉግል እንደሚለው ጥቅም ላይ የሚውል ኳንተም ኮምፒውተር ዕውን እንዲሆን በዊሎው ላይ የታዩ ስህተቶች መወገድ ይኖርባቸዋል።

ዊሎው የተገነባው ካሊፎርኒያ በሚገኘው የጉግል ቅርንጫፍ ውስጥ ነው።

የተለያዩ አገራት በኳንተም ኮምፒውቲንግ ላይ ገንዘብ በማፍሰስ ጥናቶች ይሠራሉ።

ዩናይትድ ኪንግደም በቅርቡ ብሔራዊ የኳንተም ኮምፒውቲንግ ማዕከል ገንብታለች።

ኳንተም ኮምፒውተር

የፎቶው ባለመብት, Google

የማዕከሉ ዳይሬክተር ማይክል ከትበርት ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ ዊሎው ከፍተኛ የዕድገት ደረጃን የሚያሳይ ፈጠራ ነው።

የአውሮፕላን ካርጎ ላይ እንዲሁም በቴሌኮም ዘርፍም ኳንተም ኮምፒውተሮች የላቀ ሚና እንደሚጫወቱ ዳይሬክተሩ ይጠቅሳል።

በዩናይትድ ኪንግደም 50 ኳንተም ላይ ያተኮሩ ቢዝነሶች ያሉ ሲሆን፣ 1300 ሰዎች ቀጥረው በ800 ሚሊዮን ፓውንድ ይንቀሳቀሳሉ።

በቅርቡ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እና የኦሳካ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች አነስተኛ ስህተት ብቻ ያለው ኳንተምን የተመለከተ የጥናት ወረቀት አሳትመዋል።

ኳንተም ኮምፒውተር በአካባቢው ባለው የተመጣጠነ የአየር ሁኔታ ውስጥ እንዲሠራ ማድረግ የሚቻልባቸው መንገዶች እየተሞከሩ ነው።

ጉግል አዲስ የሠራው ቺፕ ግን የሚሠራው በጣም ቀዝቃዛ በሆነ ሥፍራ ውስጥ ነው።

ስለ ዊሎው የሚገልጽ ዘገባ በሳይንሳዊው መጽሔት ኔቸር በቅርቡ ታትሟል።