በሶሪያ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች እና ሚሳዔሎች ላይ ጥቃቶች መፈጸሟን እስራኤል አረጋገጠች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል በሶሪያ ያሉ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች እና ሚሳኤሎች 'ጽንፈኞች' እጅ እንዳይገቡ በሚል በአየር ጥቃት እያወደመች መሆኗን አረጋገጠች።
የበሻር አል አሳድ መንግሥት መውደቁን ተከትሎ በተለያዩ በሶሪያ ክፍሎች የሚገኙ ስትራቴጂያዊ የጦር መሳሪያዎችን ለማውደም በመቶወች የሚቆጠሩ የአየር ጥቃቶችን እስራኤል ፈጽማለች።
በተጨማሪም በአገሪቱ የባሕር ኃይል መርከቦች እና ይዞታዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ውድመት ማድረሷ ተገልጿል።
ከእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው 15 የጦር መርከቦች ቆመው የነበሩባቸውን አል ባይዳ እና ላታኪያ በተባሉ የሶሪያ ወደቦች ላይ የሚገኙ የባሕር ኃይል ትጥቆች ላይ ጥቃት ፈጽሟል።
ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ላታኪያ በተባለችው ወደብ በተፈጸመው ከፍተኛ ጥቃት የመርከቦች ቃጠሎን እና ወደቡ ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ቪዲዮ ተመልክቷል።
በመላው ሶሪያ ከ350 በላይ የአየር ጥቃቶችን መፈጸሙን የገለጸው የእስራኤል መከላከያ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ወደ ሆነው ቀጣና ኃይሎቹን ያስገባ ሲሆን፣ የጎላን ተራራ አካባቢዎችን ተቆጣጥሯል። ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚገኝ አንድ በሶርያ ዙሪያ የሚሠራ የሰብዓዊ መብት ተቋም ባሰባሰበው መረጃ መሠረት ባለፈው እሁድ የሶሪያ አማጽያን ወደ መዲናዋ ደማስቆ መግባታቸውን ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች 310 የአየር ጥቃቶችን ፈጽሟል ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ኢዝራኤል ካትዝ ጥቃቶቹ ለአገራቸው ስጋት የሆኑ ስትራቴጂክ የጦር መሣሪያዎችን ለማውደም መሆኑን ገልጸው፣ የሶሪያን የባሕር ኃይል ለማውደም የተካሄደው ዘመቻን "ትልቅ ስኬት ነው" ብለውታል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንዳስታወቀው በጥቃቶቹ የአየር ኃይል ሰፈሮች፣ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ ፀረ አውሮፕላን መሳሪያዎች እና የጦር መሳሪያ ማምረቻ ስፍራዎችን ጨምሮ በርካታ በዋና ከተማዋ ደማስቆ፣ ሆምስ፣ ታርቱስ እና ፓልሜራ ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
በተጨማሪም ጥቃቱ የጦር መሳሪያ ማከማቻ መጋዘኖች፣ የተተኳሽ ማከማቻዎች እና "በርካታ" ከባሕር ላይ የሚወነጨፉ ሚሳዔሎች ተመትተዋል ተብሏል።
እስራኤል በሶሪያ ላይ ይህንን ጥቃት የምትፈጽመው "መሳሪያዎቹ በጽንፈኞች እጅ እንዳይወድቁ" ለመከላከል ነው ብላለች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የበሻር አል አሳድን መንግሥት ለገረሰሰው ሃያት ታህሪር አል ሻም ቡድን በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት "ኢራን ሶሪያ ውስጥ ድጋሚ ለመቋቋም የምትሞክር ከሆነ ምላሽ ለመስጠት እንገደዳለን" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ አገራቸው የምትፈጽመው ጥቃት ራስን ለመከላከል መሆኑን በማስረዳት፣ ነገር ግን ከአዲሱ የሶሪያ ኃይል ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚፈልጉም ቀደም ሲል ገልጸው ነበር።
የሶሪያ ሰብአዊ መብቶች ተካታታይ ቡድኑ መሥራች ራሚ አብዱል ራህማን የእስራኤል ጥቃት ዓላማ "ሁሉንም የሶሪያን ሠራዊት አቅም" ማውደም ነው፤ በማለት "የሶሪያ ግዛት ተጥሷል" ሲሉ ከሰዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር በወረራ ከያዛቸው የጎላን ተራራ አካባቢዎች በተጨማሪ በሶሪያ ግዛት ውስጥ ዘልቀው የገቡ ወታደሮች እንዳሉት ይፋ አድርጓል።
ነገር ግን ጦሩ ወታደሮቹ ወደ ሶሪያ ድንበር ዘልቀው መግባታቸውን ቢያምንም ታንኮቹ ወደ ዋና ከተማዋ ደማስቆ እየተጠጉ ነው መባሉን ግን "ሐሰት" በማለት የእስራኤል መከላከያ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።
የእስራኤል መከላከያ ቃል አቀባይ ናዳቭ ሾሻኒ ሁለቱን አገራት ከሚያዋስነው ድንበር የተወሰነ ርቀት ገባ ብለው ሠራዊታቸው መስፈሩን አረጋግጠዋል።
ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ቀጣና ከነበረው የጎላን ተራራ አካባቢ ባሻገር፣ ግማሽ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የሶሪያ ግዛት ውስጥ የእስራኤል ሠራዊት መግባቱን እና ክዋዳና የምትባል መንደር አካባቢ መስፈሩን አረጋግጧል።
ባለፈው ሰኞ የእስራኤል ጦር ወታደራዊ ነጻ ቀጠናውን አልፎ ወደ ሶሪያ ድንበር ሲገባ የሚያሳይ ፎቶ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አጋርቶ ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል ይህንን ርምጃ የወሰደችው ራስን ለመካለከል እና በጊዜያዊነት በሶሪያ ማዕከላዊ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ መሆኑን ገልጸዋል።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስራኤል ጦር ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ወደሆነው የሶሪያ ግዛት መግባቱን አጥብቆ ተቃውሟል።
"ከአዲሱ የሶሪያ ኃይል ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን እንፈልጋለን፣ ያ የማይሆን ከሆነ ግን የእስራኤልን እና እስራኤላውያንን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ።
እስራኤል በሶርያ ላይ ስለምትፈጸማቸው ጥቃቶች የተጠየቁት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌዲዮን ሳር፣ እስራኤል እያደረገች ያለችው ዜጎቿን መከላከል ነው ብለዋል።
"ለዚያም ነው የኬሚካል መሳሪያ እና ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን በአክራሪዎች እጅ እንዳይወድቁ ለይተን እያወደምን ያለነው" ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ።
ባለፈው ሰኞ የተባበሩት መንግሥታት በሶሪያ የሚገኙ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ አስጠንቅቆ ነበር።
በሶሪያ ምን ያህል እና የት የኬሚካል መሳሪያዎች እንዳለ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም። ነገር ግን የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሻር አል አሳድ የኬሚካል መሳሪያ ክምችት እንደነበራቸው ይታመናል።
እስራኤል በሁሉም የሶሪያ አካባቢዎች ጥቃት መፈጸም የጀመረችው የአገሪቱ አማጽያን የአሳድን መንግሥት ገርስሰው ወደ ዋና ከተማዋ ደማስቆ ከገቡ በኋላ ነው።
በሻር አል አሳድ እና አባታቸው ሐፊዝ አል አሳድ ከአውሮፓውያኑ 1971 ጀምሮ ሶሪያን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ መርተዋል።
ነገር ግን በ2011 (እአአ) ተቀሰቀሰው የአረብ አብዮትን ተከትሎ ሶሪያ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች።
ከ13 ዓመታት አስከፊ ጦርነት በኋላ ሃያት ታህሪር አል ሻም የተባለው እስላማዊ አማጺ ቡድን የአሳድን መንግሥት ገርስሶ ደማስቆን ጨምሮ አብዛኛውን የሶሪያ አካባቢዎች ተቆጣጥሯል።












