በሄይቲ የአንድ የወሮበላ ቡድን ልጅ ታሞ በመሞቱ 'ጠንቋይ' የተባሉ 110 ሰዎች ተገደሉ

የአመጸኛ ወሮበላ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ዘገባ የሚረብሽ ይዘት አለው

ሄይቲ ውስጥ ቢያንስ 110 የሚጠጉ ሰዎች 'ጠንቋይ' ናቸው ተብለው አገሪቱን እያመሷት ባሉት የወሮበላ ቡድን አባላት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ተገለጸ።

በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት አው ፕሪንስ ከተገደሉት ሰዎች አብዛኞቹ አዛውንቶች እንደሆኑ የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅቶች አስታውቀዋል።

'ናሽናል ሂውማን ራይትስ ዲፌንስ ኔትወርክ' የተባለ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም እንዳለው ግለሰቦቹ ላይ ጥቃቱ የተከፈተው የአንድ ወሮበላ ቡድን መሪ ልጅ ታሞ ከሞተ በኋላ ነው መሆኑን አመልክተዋል።

የወሮበላ ቡድን መሪው ስለ ልጁ ህመም የዘልማድ ሕክምና አማካሪ እንደጠየቀ እና ልጁ በማይታወቅ ሁኔታ የታመመው 'በጠንቋዮች ምክንያት' መሆኑ እንደተነገው ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፣ በአመጸኞቹ የወሮበላ ቡድኖች እየታመሰች ባለችው ሄይቲ በአውሮፓውያኑ 2024 የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 5,000 ይጠጋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኃላፊ ቮልከር ቱርክ እንዳሉት አደገኛ በሚባለው የወሮበላ ቡድን በተቀነባበረው ጥቃት 'ጠንቋይ' ተብለው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 184 ይደርሳል።

ግድያዎቹ የተፈጸሙት በመዲናዋ ውስጥ በሚገኝ ሲቴ ሶለሊ በሚባል መንደር ነው። የወሮበላው ቡድን አባላት በበቀል ተነሳስተው ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸውን የአካባቢውን ነዋሪዎች ከቤታቸው በመውሰድ በቢላ እና በጨንቆራ ወግተው እና ቆራርጠው ገድለዋቸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት ይህንን ክስተት ተከትሎም በርካታ አስክሬኖች ሲቃጠሉ ታይቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሰብአዊ መብት ተቋሙ እንዳለው ባለፈው ሳምንት አርብ 60 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ በማግስቱ ቅዳሜ 50 ሰዎች ተገድለዋል።

የተገደሉት ሰዎች በዕድሜ የገፉ እና ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው እንደሆኑ አክሏል።

ሌላ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንዳለው ደግሞ አዛውንቶቹ እንዳይገደሉ ሲከላከሉ የነበሩ ወጣቶችም በተመሳሳይ ተገድለዋል።

የወሮበላ ቡድን መሪው ሞኔል ፍሊክስ ልጁ የታመመው በጠንቋዮች ምክንያት እንደሆነ ስለተነገረው ነው ይህ ዘግናኝ ግድያ እንዲፈጸም ያዘዘው።

ሚካኖ በሚባል ስም የሚጠራው የወንጀለኞች ቡድን መሪው በመዲናዋ ፖርት አው ፕሪንስ ውስጥ ቁልፍ ነው የሚባልለትን ዋርፍ ጀርሜን ተብሎ የሚታወቀውን አካባቢ ይቆጣጠራል።

በሄይቲ ወንጀልን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ የሚሠራው ሮሜይን ላ ኮር ግራንድሜሰን እንዳለው ወደ አካባቢው መግባት አስቸጋሪ ነው።

የአካባቢው ነዋሪዎችም እንዳይወጡ በወሮበላው ቡድን አባላት ተከልክለዋል።

የቀድሞው የሄይቲ ፕሬዝዳንት ጆቬኔል ሞይሴ በአውሮፓውያኑ 2021 መገደላቸውን ተከትሎ ሄይቲ በወሮበላ ቡድኖች ሰላሟን አጥታ የወንጀል መድረክ ሆናለች።

እነዚህ ቡድኖች የተኩስ አቁም ለማድረግ ከተስማሙ በኋላ በ2024 ከግንቦት እስከ መስረም ባሉት ወራት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል።

ሆኖም ግን ባለፉት ሁለት ወራት ወሮበሎቹ ይዞታቸውን ለማስፋፋት በሚያደርጉት ጥረት ነዋሪዎች እንዲሁም የተቀናቃኝ ቡድን አባላትም እየተገደሉ ነው።

የመዲናዋ ፖርት አው ፕሪንስ 85 በመቶው ክፍል በአመጸኛ ወሮበሎች ቁጥጥር ስር ይገኛል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሄይቲ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም እንዳለው ግማሽ ያህሉ ሕጻናት የሆኑ 700 ሺህ ሰዎች ግድያ እና ግጭቱን በመሸሽ ከአገሪቱ ተሰደዋል።

አመጸኛ ወሮበሎቹ መድፈርን እና ሌሎች ሰብአዊ ብዝባዎችን እንደ መሣሪያ በመጠቀም ነዋሪዎችን ያስፈራራሉ።

የሂውማን ራይትስ ዋች አጥኚ ናታሊ ኮትሪኖ "በሄይቲ የሕግ የበላይነት ስለሌለ አመጸኛ ወሮበሎች ልጃገረዶች እና ሴቶችን ይደፍራሉ" ብላለች።

ባለፈው ዓመት በሄይቲ የተሰማራው በኬንያ የፖሊስ ኃይል የሚመራው ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ኃይል እስካሁን ያመጣው ለውጥ የለም።

ይህ ቡድን ሄይቲ የደረሰው ያለፈው ሰኔ እንደነበር ይታወሳል።

ሰላም አስከባሪው የተላከው የሄይቲን ፖሊስ ለማጠናከር በሚል ቢሆንም የበጀት ውስንነት እና እስከ አፍንጫቸው የታጠቁትን ወሮበሎች ለመታገል በቂ መሣሪያ አለመኖሩ ሥራውን ፈታኝ አድርጎታል።

በሄይቲ ምርጫ እንዲካሄድ እና ሰላም እንዲሰፍን የተሰማራው ኃይልም እስካሁን ሥራውን በአግባቡ ማከናወን አልቻለም።

በሄይቲ ያለው መንግሥት በወሮበሎች ጥቃት የተዳከመ በመሆኑ ዜጎቹን ቀርቶ የራሱን ባለሥልጣናት ደኅንነት ለመጠበቅ ሲቸገር ቆይቷል።

በአገሪቱ ውስጥ በተለይም የዋና ከተማዋ አብዛኛው ክፍል በታጠቁ የወሮበላ ቡድኖች ቁጥጥር ስር ሲሆን፣ የምግበ እና የነዳጅ ማከማቻዎች እንዲሁም ዋና ዋና መንገዶች በእንዲሁ የወንጀለኛ ቡድኖች እጅ ውስጥ ነው የሚገኙት።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙት የወሮበላ ቡድኖች በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ሲሆን፣ በሕዝቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አላቸው።

ቡድኖቹ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ የበላይነት ለመያዝ እርስ በርስ ደም አፋሳሽ የሆነ ግጭት ውስጥ የሚገቡ ሲሆን፣ በዚህም የአገሪቱ ነዋሪ ዋነኛ ሰለባ ነው።