የሶሪያ አማጺያን የበሻር አል አሳድ አባትን የመቃብር ስፍራ በእሳት አቃጠሉ

የበሻር አል አሳድ አባት የሆኑት የድሞው ፕሬዝዳንት ሐፊዝ አል አሳድ የሬሳ ሳጥን በአመጺኑ በእሳት ሲቃጠል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የበሻር አል አሳድ አባት የሆኑት የድሞው ፕሬዝዳንት ሐፊዝ አል አሳድ የሬሳ ሳጥን በአመጺኑ በእሳት ሲቃጠል

የበሻር አል አሳድን አስተዳደር የገረሰሱት የሶሪያ አማጺያን የቀድሞውን ፕሬዝዳንት አባት ሐፊዝ አል አሳድን የቀብር ቦታን በእሳት አወደሙ።

አማጺያኑ የመንግሥት ወታደሮችን በማሸነፍ ዋና ከተማዋን ሲቆጣጠሩ ከአገር የኮበለሉት የፕሬዝዳንት በሻር አል አሳድ አባት ሶሪያን ለ29 ዓመታት ገዝተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2000 ሐፊዝ አል አሳድ ሲያርፉ ልጃቸው በሻር መንበሩን ተረክበው ለ24 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሶሪያን በፈላጭ ቆራጭነት ሲመሩ ቆይተው ነው በአማጺያኑ ከሥልጣን የተባረሩት።

አማጺያኑ ያወደሙት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ሐፊዝ አል አሳድን የመቃብር ቦታ ብቻ ሳይሆን በመላዋ አገሪቱ ያሉ የሐፊዝ እና የልጃቸውን በሻር ሐውልቶች አፍርሰዋል እንዲሁም ፖስተሮችን አውርደዋል።

ከሃምሳ ዓመታት ሶሪያን አንቀጥቅጠው የገዙት አባት እና ልጅ የአሳድ ቤተሰብ በበርካታ ሶሪያውያን ላይ ከፍተኛ ግፍ እና ጭፍጨፋ መፈጸማቸው ይነገራል። ከዚህም የተነሳ አማጺያኑ ፕሬዝዳንት አሳድ በሽሽት ቢያመልጧቸውም የአባታቸውን የመቃብር ስፍራ በእሳት አቃጥለውታል።

በሰሜናዊ ምሥራቅ ሶሪያ ውስጥ በምትገኘው ቃርዳህ የሐፊስ አል አሳድ አስከሬን ያረፈበት ሳጥን በእሳት ሲነድ የሚያሳዩ በርካታ ቪዲዮዎች ተጋረተዋል።

ታረክ ናሲፍ የተባለ ሶሪያዊ ሐፊዝ አል አሳድ፣ ሚስታቸው አኒሳ እና ታላቁ ልጃቸው ባሴል የመቃብር ስፍር የተገኘው "መላውን የሶሪያን ሕዝብ ለዘመናት የጨቆኑትን" ሰዎች መቃብር ለመመልከት መሆኑን ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናገሯል።

በአሳድ ቤተሰብ የሥልጣን ዘመን በተፈጸመባቸው ግፍና በደል ምክንያት በተፈጠረባቸው ጥላቻ በርካታ ሶሪያውያን በእሳት የወደመውን የቀድሞውን መሪ እና ቤተሰባቸውን የመቃብር ስፍራ ለማየት እየመጡ መሆናቸው ተዘግቧል።

በመካከለኛው ምሥራቅ ረጅም ዘመናት በሥልጣን ላይ ከቆዩ አገዛዞች መካከል የሚጠቀሱት የአሳድ ቤተሰቦች ምንም እንኳን ንጉሣውያን ባይሆኑም አባት እና ልጅ ሥልጣን ተቀባብለው ከ50 ዓመታት በላይ አገሪቱን ገዝተዋል።

ሐፊዝ አል አሳድ ለሁለት ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፣ ከአውሮፓውያኑ 1971 ጀምሮ እስከ እስከ 2000 ድረስ በሥልጣን ላይ ቆይተው ሲያርፉ ሁለተኛ ልጃቸው በሻር ሥልጣኑን ተረክቧል።

የሐፊስን የመሪነት መንበር የታላቅ ልጃቸው ባሴል ይይዛል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ በመኪና አደጋ ሕይወቱ ሲልፍ ሁለተኛ ልጅ የሆኑት በሻር ወደ መሪነት መጥተዋል።

በሻር መሪ ሲሆኑ ጨቋኙን የአባታቸውን ሥርዓት ያሻሽሉታል ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን፣ እሳቸውም በሶሪያ ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ቃል ገብተው ነበር። ነገር ግን በአባታቸው የአስተዳደር መንገድ በመቀጠል በአምባገነን መሪነት ለ24 ዓመታት በሥልጣን ላይ ቆይተዋል።

ከ13 ዓመታት በፊት የአረቡን ዓለም ያንቀጠቀጠው የፀደይ አብዮት ሲቀጣጠል በሶሪያም የበሻር አል አሳድን መንግሥት ለመጣል ከፍተኛ ተቃውሞዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ ወታደሮቻቸውን እና ታንኮቻቸውን በከተሞች አሰማርተው በወሰዱት ጭካኔ የተሞላባቸው እርምጃ ሕዝባዊውን አመጽ አዳፍነውታል።

ነገር ግን ሕዝባዊው ተቃውሞ ወደ የትጥቅ አመጽ ተሸጋግሮ ለ13 ዓመታት ሲካሄድ ቆይቶ አሳድ በሩሲያ እና በ ሄዝቦላህ ድጋፍ ታጣቂዎቹን ለመቆጣጠር ችላ ነበር።

ነገር ግን ከሳምንታት በወዲህ የአማጺያኑ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሰፊ የአገሪቱን ቦታዎች እና ትላልቅ ከተሞችን በፍጥነት በመቆጣጠር ዋና ከተማዋ ደማስቆን ተቆጣጥረው አሳድን ከሥልጣን አባረዋል።