እነ አቶ እስክንድር ነጋ እና እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ከእስር ተለቀቁ

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የተከሰሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት አርብ ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም ከእስር መፈታታቸው ተገለጸ።
የእነ አቶ ጃዋር ጠበቃ የሆኑት አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እነ አቶ ጃዋር ከማረሚያ ቤት እንዲወጡ እንደተነገራቸው እና በመምሸቱ አንወጣም ማለታቸውን ገልጸው የነበረ ቢሆንም ምሽት ላይ ከአስር ቤት መውጣታቸው ተነግሯል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ደግሞ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ከፍተኛ አመራሮቹ ከእስር እንደተለቀቁ አመልክቷል።
ቢቢሲ ከባልደራስ ፓርቲ ምንጮች ያገኘው መረጃ እንዳመለከተው የባልደራስ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋና አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ሌሎች በእስር ላይ የነበሩ አመራሮች ከአስር ወጥተዋል።
አቶ ስንታየሁ ቸኮል ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አርብ ዕለት ስለመፈታታቸው ቀደም ሲል እንዳልተነገራቸውና እንዳልተዘጋጁ ገልጸዋል።
በዕለቱ አመሻሽ ላይ እቃቸውን እዘው እንዲወጡ በድንገት ተነግሯቸው ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት መውታጣቸውን እንጂ ስለተፈቱበት ሂደቱ ቀደም ያለ መረጃ እንደሌላቸው ከእስር ቤት ከወጡ ከደቂቃዎች በኋላ ለቢቢሲ በስልክ ተናግረዋል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ምሽት ላይ እንዳስታወቀው ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ አስር ላይ ቆዩት ከፍተኛ አመራሮቹ አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሴ ከእስር ተለቀዋል።
በተመሳሳይ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት የታሰሩት አቶ ጃዋር መሐመስ በስማቸው ባለ መዝገብ ላይ የተከሰሱት ከ20 በላይ ግለሰቦች ሲሆኑ፣ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ሁሉም ይለቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።
በእነ አቶ ጃዋር የክስ መዝገብ ውስጥ ከተካተቱት እና በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከሚገኙት መካከል ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ፣ ጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ እና የአቶ ጃዋር መሐመድ ጥበቃዎች ይገኙበታል።
የአቶ ጃዋር ጠበቃ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ስለተፈቱበት ሂደት በዝርዝር እንደማያያውቁ፣ ነገር ግን መፈታታቸውን በተመለከተ እንዲወጡ እንደተነገራቸው እንደሚያውቁ "ደብዳቤም ሳይሰጧቸው እንደማይቀርም" አመልክተው፤ በነገው ዕለት (ቅዳሜ) ያለውን ሁኔታ ወደ ስፍራው በመሄድ እንደሚያጣሩ ጠበቃ ቱሊ ገልፀዋል።
ይህ የፖለቲከኞቹ የመፈታት ዜና የተሰማው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገና ዕለት ከሰዓት በኋላ ይቀርታና ምህረትን በተመለከተ "ድላችን ዘላቂ ለማድረግ እንድንችል በአሸናፊ ምህረት ግጭቱ የፈጠረውን ውጥረት እናረግባለን" በማለት መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም "ያጠፋ እንዲቀጣ፣ የበደለ እንዲክስ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ ፍትሕ በሽግርር እና በተሃድሶ ፍትህ እይታ፣ አገራዊ ባህሎቻችን እና አሴቶቻችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ፍትህ እናሰፍናለን" ብለዋል።
የእነ አቶ ጃዋር ጠበቃ በምን አይነት ሁኔታ ይፈቱ ተብሎ እንደተወሰነ እንደማያውቁ ተናግረው "እስካሁን ጥፋተኛ አልተባሉም ስለዚህ የሚሆነው ክስ ማቋረጥ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ቱሊ ይህንን ሲያብራሩም በሕጉ መሰረት አንድ ተከሳሽ ይቅርታ የሚደረግለት ጥፋተኝነቱ ተረጋግጦ የተፈረደበት እንደሆነ ነው ይላሉ።
ነገር ግን በክስ ሂደት ላይ ያለን ሰው ደግሞ ክርክሩን ከማስቀጠል ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክሱን ማቋረጥ እንደሚቻል ሕጉ እንደሚደነግግ ያስረዳሉ።
ስለዚህ ከዚህ አንጻር ከታየ የእነ አቶ ጃዋር መለቀቅ ክስ ማቋረጥ እንደሚሆን ጨምረው አብራርተዋል። ነገር ግን አሁን መንግሥት "የትኛውን እንደተጠቀመ" እንደማያውቁ ገልፀዋል።
እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ እንዲፈቱ የተወሰነበት ሁኔታ ግልጽ አለመሆኑ የገለፁት አቶ ቱሊ፤ "መንግሥት ደንብና ሥርዓትን ተከትሎ መልቀቅ አለበት፣ ስለዚህ መለቀቃቸው ቢያስደስተንም ነገር ግን በአግባቡ ሂደቱን ተከትሎ አለመፈተታቸው ያሰጋናል" ሲሉ አክለዋል።
ጨምረውም "አሁን ዳኞች መዝገቡን እንዴት አድርገው እንደሚዘጉ ግራ የሚያጋባ ነው" የሚሉት አቶ ቱሊ "እንደዚያ ባይሆን ጥሩ ነው ግን ትልቁን ምስል ስናይ ያለ አግባብ ስለታሰሩ በነጻ መለቀቃቸው ያስደስተናል" በማለት አስረድተዋል።
አቶ ቱሊ እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ይፈቱ ተብሎ በመወሰኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፣ በተከሰሱበት ወቅት ክሳቸው ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል መግለጻቸውን ነገር ግን "ፍርድ ቤት እና ዳኛ ካለ" ነጻ እንደሚሆኑ ያውቁ እንደነበር ተናግረዋል።
እነ አቶ ጃዋርም ሆኑ ጠበቆቻቸው ከመጀመሪያ ጀምሮ ይህ ጉዳይ በፍርድ ቤት የሚፈታ አለመሆኑን ይናገሩ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ቱሊ፣ "በድርድር፣ በንግግር እና በፖለቲካዊ ውሳኔ መፈታት እንዳለበት" ይናገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
"ከፍርድ ቤት ውጪ ማለቁ እኛም ስንከራከርበት እነ ጃዋርም ሲከራከሩበት የነበረ ነው። ፍርድ ቤት አንሄድም ሲሉ የነበረበት ምክንያት ይኸው መጣ" ሲሉ ተናግረዋል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አስክንድር ነጋና ሌሎች የፓርቲው አመራሮች እንዲሁም የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ አባል የሆኑት ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ አመራሮችና አባላት ለእስር የተዳረጉት የታዋቂው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደልን ተከትሎ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ነበር።
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከአንድ ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ መኪናው ውስጥ ሳለ በጥይት ተመትቶ መገደሉን ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የበርካታ ሰዎች ህይወት ያለፈበትና ከፍተኛ ንብረት የወደመበት ሁከት መከሰቱ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ካለመረጋጋቱ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ጨምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል።
የፍትህ ሚኒስቴር ከአመሻሹ ባወጣው መግለጫ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕገ-መንግስት እና የሽብር ችሎት እየታየ ከነበሩት ተከሳሾች መካከል በነጃዋር ሲራጅ መሃመድ እና በእነ እስክንድር ነጋ ፈንታ መዝገብ ያሉ ተከሳሾች ክሳቸው በአዋጅ ቁጥር 943/2008 መሰረት እንዲነሳ ተደርጓል ብሏል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባሰፈረው መሰረት ክሱ እንዲነሳ የተደረገው" በቀጣይ የሚደረገውን ሃገራዊ የምክክር መድረክ ሂደት ውጤታማነት እና አካታችነት ከፍ ለማድረግ በማሰብ ነው።" ብሏል።












