እነ አቶ ጃዋር ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤት መቅረብ እንደማይፈልጉ አስታወቁ

አቶ ጃዋር መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ከ20 በላይ ተከሳሾች ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ቀርበው እንደማይከታተሉ በትናንትናው ዕለት ግንቦት 18/2013 ዓ.ም አስታውቀዋል።

ተከሳሾቹ አቤቱታቸውን በአምስት ገጽ ደብዳቤ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ-ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት እንዳቀረቡም ቢቢሲ ከጠበቆቻቸው አንዱ ከሆኑት አቶ ከድር ቡሎ ተረድቷ።

ረቡዕ በዋለው ችሎት ላይ ተከሳሾቹ በዋነኝነት ያነሱትም የፍርድ ቤት ውሳኔ በማይከበርበትና በተደጋጋሚ በሕግ አስፈፃሚው አካል በሚጣስበት ሁኔታ የእነሱ ችሎት መምጣት ትርጉም እንደሌለው ማስረዳታቸውንም አቶ ከድር ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ ነፃ ቢያሰናብታቸው ሕግ አስፈፃሚው አካል "ከሕግ በላይ ሆኖ ስለማይለቀንና የፍርድ ቤቱም ውሳኔ በማይከበርበት ሁኔታ ችሎቱ የክብር ነው እንጂ መቀለጃ መሆን የለበትም" ብለዋል ይላሉ።

ለዚህም በርካታ ማጣቀሻዎች ማቅረባቸውን የሚናገሩት አቶ ከድር ከነዚህም መካከከል ፍርድ ቤት በነፃ ያሰናበታቸው እነኮሎኔል ገመቹ አያናና ሌሎች ግለሰቦችን ፖሊስ ለመልቀቅ ፈቃደኛ አይደለም፤ እንዲሁም ያሉበት አይታወቅም ብለዋል።

የጂማ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች እንዲሁ ፍርድ ቤቱ በነፃ ቢለቃቸውም ከቤተሰብም ሆነ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት አልቻሉም፤ እስከዛሬ የት እንዳሉም አይታወቅም።

እንዲሁም የኦነግ ሥራ አስፈፃሚ የነበሩ አመራሮችም እንዲሁ ፍርድ ቤቱ ነፃ ቢያወጣቸውም ያለ ፍርድ ቤቱ እውቅና ታስረው እንዳሉና ያሉበት ቦታም ግልፅ እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ባለፉት ሦስት ወራት ወደ አስር የሚጠጉ ግለሰቦች ከኦነግ ጋር በተገናኘ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በኦሮሚያ ፖሊስ ታስረው ይገኛሉ ብለዋል።

"ይህ የሚያሳየው የፍትህ መዛባትን ነው። የሕግ አስፈፃሚው አካል ሕግ አለማክበሩን ነው የሚያሳየው" ማለታቸውን አቶ ከድር ያስረዳሉ።

አቶ ከድር እንደሚናገሩት ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመከበር በተጨማሪ ግለሰቦች ያለ ፍርድ "በሚገደሉበት ሁኔታ" ያሉትን እንደ ምክንያት መጥቀሳቸውን አውስተዋል።

ተከሳሾቹ የፍርድ ቤት ውሏቸውን የጀመሩት በህሊና ፀሎት ሲሆን እነ አቶ ጃዋር መሐመድና ተከሳሾቹ በዶምቢዶሎ ከተማ "በአደባባይ በቤተሰቦቹ ፊት" የተገደለው አማኑኤል ወንድሙ እንዲሁም በትግራይ ጦርነት እየደረሰ ስላለው ግድያና የመብት ጥሰት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እነ ጃዋር አድርገዋል።

በትግራይ ካለው የመብት ጥሰት ጋር በተያያዘ የትግራይ ሕዝብ ፆም (የረሃብ አድማ) እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው እነሱም የሕዝቡ አካል ስለሆኑና ስለሚመለከታቸው ለሦስት ቀናት ከትግራይ ህዝብ ጋር የረሃብ አድማ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል ብለዋል።

በፀረ-ሽብር አዋጅ የተከሰሱት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ እነ ጃዋር መሐመድ ጠበቆቻቸው ጭምር ለእንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውንም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

የጠበቆቻቸው መኪኖች እንደተሰበሩና አካላዊ ድብደባም ደርሶባቸዋል በማለት "ሕግ በማይከበርበት ሁኔታ ችሎት መቅረብ የለብንም" ማለታቸውንም አቶ ከድር ያስረዳሉ።

ከዚህ ቀደምም ግንቦት 12/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት የፍርድ ቤት ቀጠሯቸው ከሁለት ዓመት በኋላ እንዲሆን ጥያቄ አቅርበው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ውድቅ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ከዚህ ቀደምም በነበረው ችሎትም ሆነ በአሁኑ የአቤቱታ ደብዳቤ ከምርጫውና አገር ከተረጋጋ በኋላ ወደ ፍርድ ቤቱ እንደሚመጡ ችሎቱን አስረድተዋል።